ምርጫ ቦርድ ለራያ ራዩማ ፓርቲ ህጋዊ ዕውቅና ሰጠ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ በምስረታ ሒደት ከአንዳንድ ወገኖች ቅሬታ የቀረበበትን የራያ ራዩማ ፓርቲ ጉዳይ መርምሮ ውሳኔ ሰጠ። በውሳኔው መሰረት ፓርቲው እንዲመዘገብ ፈቅዷል።
(የቦርዱ መግለጫ እነሆ)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የራያ ራዩማ ፓርቲን የምዝገባ ሂደት በሚያይበት ወቅት ፓርቲው እንዳይመዘገብ የሚል ተቃውሞ ቀርቦ እንደነበር ይታወሳል። ተቃውሞው የፓርቲው አርማ ግጭትን ያነሳሳል፣ የራያ ባህልን በሙሉ የሚገልጽ ምልክት ለአንድ ፓርቲ አርማነት ሊውል አይገባም የሚል ሲሆን በተጨማሪም የሚከተሉትን ዋና ዋና አቤቱታዎች ቀርበዋል።
- ጥላቻና ጠላትነት የሚያስፋፋ፣ ግጭትን የሚፈጥር ሰዎችን ከደጋፊነት ወይም ከአባልነት የሚያገል፣ መሠታዊ እና ስነሥርዓታዊ ሕገወጥነት ያለበት ፓርቲ መሆኑን፣
- ራያ – ማለትም በአማራ ክልላዊ መንግሥት የሚገኘውን የራያ ቆቦ ወረዳን፣ በትግራይ ክልል ያሉትን የራያ አላማጣ እና የራያ አዘቦን ወረዳ፣ እንዲሁም የአገው እና የኦሮሞ ሕዝብን ያላማካለ ፓርቲ መመስረቱ፣
- በትግራይ ክልል ስር ይኖር የነበረው የራያ ሕዝብ ያለፍላጎቱ በትግራይ ክልል ውስጥ ተካልያለሁ በሚል የዘመናት ቅሬታ እንዳለበት፣ የአከላለል ችግር በመንግሥት ይስተካከላል የሚል ተስፋ ቢኖርም የተወሰኑ ቡድኖች የብሔረሰብ ማንነት ጥያቄ እንዲይዝ በማድረግ በመጀመሪያ ኮሚቴ አዋቅረው አሁን ደግሞ የራያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ራዴፓ/ የሚባል ፓርቲ በማቋቋም ከሕዝቡ ፍላጎት በሚቃረን መልኩ ሕገ ወጥ የሆነውን ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ እየሠሩ እንደሆነ፣
- ራያ የተለየ ብሔረሰባዊ ማንነት አለው በሚል ጥያቄ ለትግራይ ክልል መንግሥት የማንነት እውቅና ይሰጠኝ የሚል ጥያቄ መቅረቡ፣ ራያ ብሔረሰባዊ ማንነቱ አማራ፣ አገው፣ የራያ ትግርኛ ተናጋሪ እና ኦሮሞ የሆኑ ብሔረሰቦች ይኖሩበታል እንጂ ሌላ ራያ የሚባል የተጠቀሱትን ማንነቶች የሚጨፈልቅ ብሔረሰባዊ ማንነት የለውም በሚል ተቃውሞ እያሰማ መሆኑ፣
- የፓርቲው ፕሮግራም ሕገወጥ አላማን ያነገበ መሆኑ፣ ይኸውም በሕገመንግሥቱ አንቀፅ 31 እና በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀፅ 69 ንዑስ አንቀፅ 1 /ረ/ ሂደቱን ያልጨረሰን የብሔረሰብ ማንነት ጥያቄ በአቋራጭ ፓርቲ በማቋቋም ሰበብ እውቅና ለማሰጠት መሄዱ፣
- ስያሜውና አርማው የታሪክና ባሕል ሽሚያ ላይ ያተኮረ መሆኑ፣ ራያና አማራነትን በመነጠል የራያ ብሔረሰባዊ ማንነት አቀንቃኞች የራያ ሁለንተናዊ ታሪክና የባሕል ባለቤትነት የካዱና ሽሚያ ውስጥ የገቡ መሆኑ፣ በሚሉ ምክንያቶች እውቅና ሊሰጣቸው አይገባም በማለት ጠይቀዋል።
ቦርዱ ከላይ የቀረበውን አቤቱታ በመመርመር
- አቤቱታ አቅራቢዎች የጠቀሱት በሕገመንግሥቱ አንቀፅ 31 “ማንኛውም ሰው ለማንኛውም አላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው፡፡ ሆኖም አግባብ ያለውን ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የተሰመረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የከለከሉ ይሆናሉ” እንዲሁም በአዋጁ አንቀፅ 69 ንዑስ አንቀፅ 1 /ረ/ “ሕገወጥ አላማን ለማካሄድ የተቋቋመ የፖለቲካ ድርጅት ከሆነ” አይመዘገብም በማለት ተደንግጓል፡፡ ይሁንና ፓርቲው የሕገመንግሥቱንና የአዋጁን ድንጋጌዎች በምን መልኩ እንደጣሰ በግልፅ ያላስቀመጡና ማስረጃም ያላቀረቡ መሆኑ፣
- ፓርቲው ጥላቻና ጠላትነት ስለማስፋፋቱ፣ ግጭትን የሚፈጥር፣ ሰዎችን ከደጋፊነት ወይም ከአባልነት ስለማግለሉ፣ መሠረታዊ እና ስነሥርዓታዊ ሕገወጥነት ያለበት ስለመሆኑ በግልፅ ያላስቀመጡ እና ማስረጃ ያላቀረቡ መሆኑ፣
- ስያሜውና አርማው የታሪክና ባሕል ሽሚያ ላይ ያተኮረና በጥቂት ግለሰቦች አማካይነት ለሚመሰረት ፓርቲ ዓርማነት ሊያገግል አይገባም በሚል ያቀረቡትን ተቃውሞ መሰረት በማድረግ ፓርቲው አርማውን የቀየረ በመሆኑ
- በአዋጁ አንቀፅ 69 መመዝገብ ስለማይችል የፖለቲካ ፓርቲ፣ በአንቀፅ 70 በፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ ስለማይችል ድርጅት ወይም ማኅበር እንዲሁም በአንቀፅ 86 የፖለቲካ ፓርቲ ስያሜና አርማን በተመለከተ በሕጉ በተደነገገው መሠረት ፓርቲው የትኛውን የሕግ ድንጋጌ እንደጣሰ በግልፅ ያልተቀመጠና ማስረጃ ያልቀረበ መሆኑ፤
በአጠቃላይ በፓርቲው የተጣሱት የሕገመንግሥቱና የአዋጁ ድንጋጌዎች በምን መልክ እንደተጣሱ በግልፅ ያልተቀመጠ እና ስለመጣሳቸው ማስረጃ ያልቀረበ በመሆኑ ግለሰቦቹ ያቀረቡት ተቃውሞ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡
በመሆኑም ፓርቲው ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች በማሰባሰብ ያቀረበው የመሥራች አባላት ናሙና ሲጣራ 64% በመቶ የመሥራች አባላት የተገኙ በመሆኑ እና ያቀረበው የምዝገባ ጥያቄ ሰነድ በሕጉ መሠረት ተሟልቶ የቀረበ በመሆኑ የፓርቲውንም አርማ በመቀየር ያቀረበ በመሆኑ ፓርቲው ህጋዊ ፓርቲ በመሆን ተመዝግቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ጥር 13 ቀን 2013 ዓ.ም