አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ
ትኩረት ለትግራይ !!!
ትኩረት ለአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ!
ትኩረት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር!
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
Solidarity Movement for a New Ethiopia
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ፤ መንግስት በትግራይ ክልል ሲያካሄድ የቆየውን ህግን የማስከበር እርምጃ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶች ማለትም የምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ የህክምና እና የመድኃኒት፣ የደህንነት፣ ባንክ፣ ትራንስፖርት የመሳሰሉት አገልግሎቶች አሁንም ያለመሟላት እና ከፍተኛ የሆነ የህግና ስርዓት ያለመከበር ስጋት እንዲሁም ጥቃት ያለባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ከታማኝ ምንጮች አረጋግጧል፡፡ ጊዜያዊው የክልሉ አስተዳደር ሁኔታዎችን ለማስተካከል እየጣረ ያለበትን ጥረት ብንረዳም ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነውና የሁላችንንም ኢትዮጵያውያን ርብርብ እና እገዛ እንደሚጠይቅ ተረድተናል፡፡ ሁኔታዎች ከእስከአሁኑም በላይ ተባብሰው ከቁጥጥር ውጭ ሳይሆኑ በፊት አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡
በመሆኑም
- በክልሉ ባለፈው ክረምት ወቅት በአዝርዕት ላይ በደረሰው የበረዶ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የጎርፍ አደጋ እና የበረሀ አንበጣ ወረርሽኝ የተነሳ ጉዳት የደረሰ እንደነበርና ከዚህም የተረፈውን በነበረው ጦርነት ምክንያት በበቂ ሁኔታ መሰብሰብ ባለመቻሉ እና በተያያዥ ምክንያቶች ከ3.5 ሚልየን በላይ ዜጎቻችን አስቸኳይ የህይወት አድን እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በመረዳታችን ነገ ዛሬ ሳይባል በአስቸኳይ የምግብና የመጠጥ እርዳታ የሚደርስበትን መንገድ እንዲመቻች ለዚህም ለሚመለከታቸው አካላትና መላው የኢትዮጵያ ዜጎችን ጥሪ እናቀርባለን፡፡
- ለህክምና ተቋማት የመድኃኒት፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ ባለሙያ እና ጥበቃ በማሟላት ማስቀረት የሚቻሉ የጤንነት ችግሮች እንዲቀረፉ እና በተለይ ሕጻናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች እንዲረዱ እንጠይቃለን፡፡
- ጊዜያዊው የክልሉ መንግስት እስከታችኛው የፀጥታና የአስተዳደር መዋቅር መልሶ ለማዋቀር እየሰራ እንደሆነ ብንገነዘብም በዘላቂነት ስራው እስኪሳካ ከነዋሪው እና ከሌሎች እትዮጵያውያን የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ሰላምና ማረጋጋቱን ለማገዝ የሚችል ግብረ ኃይል በማሰማራትም ጭምር ህግና ስርዓትን በማስከበር ዜጎቻችን ላይ ያለውን የደህንነት፣ የዝርፊያና የመደፈር… ስጋት በአፋጣኝ እንዲያስቆም እንጠይቃለን፡፡
- በክልሉ ዕርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች የእርዳታ ቁሳቁሶችና በማከፋፈል ሊያግዙ የሚችሉ በጎ ፈቃደኞች መሰማራት እንዲችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ እናሳስባለን
- የምግብ እና ሕክምና አገልግሎት ማድረስ የማይቻልባቸው ቦታዎች ካሉም ሰላማዊ ዜጎች በተለይ ሴቶች፣ ሕፃናት እና አቅመ ደካሞች ከአካባቢው ተጓጉዘው ወደሌሎች አቅርቦት ሊደርስላቸው ወደሚችሉበት የትግራይ ክልል ከተሞች ወይም ወደ አቅራቢያ የሀገራቸው ክልሎች በማድረስ የህይወት አድን ስራዎች እንዲሰሩ አበክረን እንጠይቃለን፡፡
- በሰላማዊ ሰዎች እና ባልታጠቁ ዜጎች ላይ የደረሰው አካላዊ ጥቃት፣ ዘረፋ እና የሞራል ድቀት በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ ፍትህ እንዲሰጥ አበክረን እንጠይቃለን፡፡
- በቀጥታ ከህግ ማስከበር እርምጃው ጋር ባልተያያዘ ሁኔታ በተለያዩ ተቋማት ላይ የደረሰውን ዝርፍያ እና የንብረት ውድመት በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ፍትህ እንዲሰጥ አበክረን እንጠይቃለን፡፡
- በሀገርም ውስጥ በውጭም ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው እየተጎዱ ያሉት ንጹሀን ዜጎቻችን ናቸውና ይህ ስቃይ እና ስጋት አብቅቶ ወደ ማቋቋም ለመሸጋገር ይቻል ዘንድ በሁሉም ዘርፍ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ ታደርጉ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
- የመንግስት የሚመለከታችሁ አካላት፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ሲቪል ማህበረሰብ ፣ የሚድያ ፣ የበጎ አድራጎት ማህበራት ያላችሁን መዋቅር በመጠቀም ቅድምያ ህይወት ለማዳን እና ሰብዓዊነትን በማስቀደም በአንድነት እንድንቆም እንለምናችኋለን፡፡
ኦባንግ ሜቶ
ዋና ዳይሬክተር
ጥር 10 /2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ