ያልተነገረ ተጋድሎ!
“ከአማራ ልዩ ሀይል አባይ ብርጌድ ጋር አብሬ በራያው የጦር ግንባር ግራ ካሱ” ላይ ተሰልፌአለሁ። ነገር ግን እራሴን ከጠላት ልከላከልበት የሚያስችል ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ የለኝም። መኪናዬን የተቃጠለ ዘይትና ጭቃ ቀላቅዬ ቀብቻለሁ። ቢሆንም ግን ሞርታርና ቅንቡላ በእርምጃ ርቀት እግሬ ስር በተደጋጋሚ ይወድቅ ነበር” ግራ ካሱ በእሳት ይጨሳል ከባድ መሳሪያ እና ቦንብ ከላይ ወደ ታች በተደጋጋሚ ይወረወራል። የአምቡላንስ ሹፌሩ የበሀይሉ ደምሴ ትውስታ ነው::
በወራሪው እና በተስፋፊው የህወሓት አንጃ ላይ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ በተጀመረ ቅፅበት ነበር የኋላ ደጀን በመሆን በሞት መሀል መኪናቸውን እያሽከረከሩ በመመላለሱ ጉዳት የአጋጠመውን የወገን ጦርን መርዳት የጀመሩት የአንቡላንስ ሹፌሮች።
ሹፌሮቹ ወደ ግንባር በተሰማሩበት ወቅት የታዘቡትን እንዳጫወቱን ከላይ ልብን የሚያርድ ከባድ መሳሪያ ያምቧርቃል፤ በዙሪያቸው ክላሽ እንደ ፈንዲሻ ቆሎ ይንጣጣል፤ ባልታሰበ እና ባልተጠበቀ ሰዓት የሚወረወር ቅንቡላ ይዘንብና ሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ያደርሳል።
በዚህ መሀል ግን ልባቸውን ደንደን አድርገውና መሪያቸውን ጠበቅ አድርገው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በታላቅ ፍቅር እየተንከባከቡ ቀንም፣ ማታም ሌሊትም ወደ ህክምና ተቋም ያመላልሳሉ። የቆቦ ሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ የአንቡላንስ ሹፌሮች።
በጦር አውድማ መሀል በክብር መሰዋት፣ መውደቅና እና መጋጋጥ የነበረ፣ያለና የሚኖር ክዋኔ ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ በቅርብ ተገኝተው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰራዊቶች እየተንከባከቡ ወደ ህክምና የሚያደርሱ ግንባር ቀደም ደጀኖች የአምቡላንስ ሹፌሮች ናቸው።
ደሳለው ፈንታ ይባላል፡፡ 26 ዓመቱ ነው ስራውም የራያ ቆቦ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የአምቡላንስ ሹፌር ነው። በተስፋፊውና በወራሪው የትህነግ ሀይል ላይ እርምጃ መውሰድ በተጀመረ ማግስተ ነበር በሙያው የበኩሉን ሊያበረክት የተሰለፈው።
ጦርነትን በታሪክና በፊልም እንጅ በተግባር አያውቀውምና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጦር ግንባር ሲመደብ መደናገጥ ገጥሞት እንደነበረ ይገልፃል። “መጀመሪያ የመኪና ጎማን ዝግጁ ማድረግ፣ መኪናው እንዳይታይ ጭቃና የተቃጠለ ዘይት መቀባት፤ አንዲሁም ስልካችንን ቻርጅ ማድረግና ተቀያሪ ባትሪ መያዝ እንዳለብንና ቀንም ለሊትም ዝግጁ መሆን እንደሚገባ ሲነገረን መደናገጥ ይታይብኝ ነበር” ይላል ግራ ካሱ ላይ ለስራ ወደ ምሽግ ሲገባ የተሰማውን ሲገልፅ።
ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ነው፤ በመሆኒ አድርጋችሁ በግራ በኩል ወደ ማይጨው በሚወስደው ኮረኮንች መንገድ ላይ ቁስለኛ አለ ይዛችሁ ኑ ተብለን ሁለት አንቡላሶች ሆነን ሄድን። በመሆኒ በግራ ታጥፈን በፍጥነት እንበራለን እኔ ፊት ነኝ መብራት አብርቻለሁ ከኋላዬ ያለው አምቡላንስ መብራቱን አጥፍቷል፤ በዚያ ቅፅበት መከላከያ የጫኑ ኦራልና ፓትሮል መኪኖች በፍጥነት መንገዱን ዘጉና አስቆሙን ከዛ መብራቱን እንዳጠፋ በቁጣ አዘዙኝ።
“የት እየሄዳችሁ” ነው አሉን ቁስለኛ ልናነሳ አንደሆነ ነገርናቸው። “እዚህ ምንም ቁስለኛ የለም ትንሽ ብትጓዙ ጠላት እጅ ወድቃችሁ ነበርና በፍጥነት ተመለሱ! ቁስለኛ ያለው ግራ ካሱ ነውና ወደዛ ሂዱ” አሉን። በዚያ ግዜ አልፈን ትንሽ ብንጓዝና እነዚያ የመከላከያ ሀይል ባይደርሱልን ኖሮ ሞተን ነበር በማለት ደሳለው ፈንታ ያንን አስፈሪ ገጠመኝ ይገልፃል።
ሌላው ከቀኑ አስር ሰዓት አካባቢ ሄዋኔን አልፈን አምባላጌ ተራራ አካባቢ ቁስለኛ ልናመጣ ስንሄድ አካባቢው ላይ ክሬቸርና የተፈጨ ጠጠር አለ። ያ ጠጠር በመድፍ ተመታና በጣም ጮኸ መኪናችንንም ጠጠሩ መታው በዚያን ጊዜ አራት አምቡላንስ የያዝን ሹፌሮች የመኪናውን ሞተር ሳናጠፋ እየሮጥን ጫካ ገባን፤ ተራራ ላይ ወጣን ሲል ደሳለው ያንን አስቸጋሪ ጊዜ ይገልፀዋል።
ጊዜው የመከላከያ ሀይል ምን ያክል ሀገር ወዳድ እንደሆነና ለሀገር ያለውን ቁርጠኝነት የተረዳበት ወቅት እንደሆነ ይገልፃል። ከትወስታውም ሴት የመከላከያ አበል ግራ ካሱ ላይ ቆስላ ውጭ ብትባል አልወጣም ምሽግ መስበር አለብኝ ስትል በአድናቆት መመልከቱን ያስታውሳል። እሱም በዚህ ታሪካዊ ወቅት በሙያው በመሳተፉ ደስተኛ መሆኑንም ይገልፃል ወጣት ደሳለው።
ሌላው በሀይሉ ደምሴ ይባላል፤ የቆቦ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የአምቡላንስ ሹፌር ነው። ህዳር 6/2013 ዓ.ም ነበር ከአማራ ልዩ ሀይል አባይ ብርጌድ ጋር አብሮ ወደ አላማጣ መኪናውን ይዞ የገባው።
“በቀጣዩ ህዳር ሰባት ቀን ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ለረዥም ሰዓታት ግራ ካሱ ላይ ውጊያ ተደርጓል” ሲል የሚገልፀው በሀይሉ በዚህ ወቅት መቅደላ ብርጌድን አባይ ብርጌድ ሲተካው ”ቁስለኛ ላወጣ ስገባ በተደጋጋሚ ሞርተርና ድሽቃ ስቶኛል” ሲል ወቅቱ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበረ ያስታውሳል። ቁስለኛ ይዞ በሚወጣበት ወቅት በተከታታይ ሁለት ሞርታር ከርምጃ በአነሰ ርቀት በዙርያው ይወድቅ እንደነበረም ይገልፃል።
“ከአባቶቻችን እንደሰማነው ግራ ካሱ ተራራ ላይ ደርግና ወያኔ ለ17ቀን ተዋግተውበታል “ዛሬ ላይ ግን በሰዓታት ውጊያ ውስጥ በአማራ ልዩ ሀይልና በመከላከያ ሰራዊት ሲደረመስ በቦታው ነበርኩ እና በአማራ ልዩ ሀይል ክብርና ኩራት እንዲሰማኝ አድርጎኛል በማለትም በሀይሉ ያስረዳል።
አቶ ደመወዝ በየነ የቆቦ ሆስፒታል የአምቡላንስ ሹፌር ናቸው። ህዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም ከእይታ ለመሰወር ጭቃና የተቃጠለ ዘይት በመቀባት ስድስት አምቡላንሶችን በጋራ ወደ ግራ ካሱ መግባታቸውን ይናገራል። በተለይ ህዳር 9 እና 10 በመሆኒ በኩል አዲቀይ አካባቢ ርምጃው እየተጠናከረ ሲሄድ ቀንም ሌሊትም ስራ በዝቶባቸው እንደነበረም ያስታውሳል።
እንደ ጋሽ ደሞዝ አስተያየት “ህዳር 19 ቀንን መቼም አትረሳም” ይላሉ ምክንያቱን ሲያስረዱ ደግሞ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ በመሆኒ ታጥፈው በኮረኮንች መንገዱ ላይ ቁስለኛ ሊያመጡ ሲጓዙ ከጠላት እጅ ከመውደቅ ለጥቂት ያመለጡበትን ወቅት አንደሆነም ይናገራሉ።
አፈሙዝ ጨብጠው ከሚዋጉት ባልተናነሰ ለሀገር መስዋዕት እየሆነ ያለውን ፅኑ ወታደር ደግፎ ለህክምና በማብቃት ህይወት ማስቀጠል ትልቅ ውስጣዊ እርካታን እንደሚያጎናፅፎ አቶ ደሞዝ ያስረዳሉ። እሳቸውም አዚህ ታሪካዊ ሂደት ላይ በመሳተፍ ለሀገራቸው እንዳች ማበርከት በመቻላቸውም ደስተኛ እንዳደረጋቸውም አስረድተዋል።
አስር አለቃ ተማም እንድሪስ የ25ኛ ክፍለ ጦር 1ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አባል ነው። ተምቤን ላይ በነበረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ላይ አነስተኛ ጉዳት ደርሶበት በቆቦ ሆስፒታል በህክምና ላይ ይገኛል።
አስር አለቃ ስለ አምቡላንስ ሹፌሮች ሲናገርም “የአምቡላንስ ሹፌሮች ልክ እንደ ኦራልና ፓትሮል ሹፌሮች ታጋዮች ናቸው” በማለት ይገልፃቸዋል። እስከ ውጊያ መሀል በመግባት ቁስለኛን ያወጣሉ፤ የተሰዋን ያነሳሉ። በቶሎ ወደ ህክምና አድርሰው ህይወት ለማትረፍ የሚያደርጉትን ሁኔታ በጥልቀት ታዝቤአለሁ። የሚያደርጉት እንክብካቤም ለዚህ ህዝብ መዋደቅ ክብር እንደሆነ በጥልቀት እንድረዳ አድርገውኛል” በማለትም ይገልፃቸዋል። በዚህ አጋጣሚው ምስጋናውን ለእነስሱ እንዲደርስለትም ይጠይቃል።
አዲሱ ጋሻው በቆቦ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ውስጥ የድንገተኛ ክፍል አስተባባሪ ናቸው። በወቅቱ የደቡብ ወሎ፣ የሰሜን ወሎ እና የተለያዩ ወረዳዎች የአምቡላንስ ሹፌሮች ለ24 ሰዓታት ያለ መታከት ሲያገለግሉ እንደቆዩም ይመሰክራሉ።
በአጠቃላይ የአምቡላንስ ሹፌሮች ምሽግ ድረስ በመግባት ህይወት ለማትረፍ የአደረጉት አመርቂ ተግባር የህክምና ስራው የተሳካና ውጤታማ እንዲሆን የአምቡላንስ ሹፌሮች ሚና ከፍተኛ እንደነበረም አቶ አዲሱ ያስረዳል።
በመጨረሻ ሀሳባቸውን የአካፈሉኝ የአምቡላንስ ሹፌሮች በህግ ማስከበር ዘመቻው በሙያቸው በመሳተፋቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል::
(ግርማ ሙሉጌታ -በኩር ጥር 03 ቀን 2013 ዓ.ም ዕትም)