እነሱ ዘንጣ የኖረችውን ነፍሳቸውን በእርጅና ለማትረፍ ቀሚስ ለብሰው ገደል ተሸጎጡ፤ ወጣቱን ግን በአፍላ እድሜው እሳት ማገሩት
(ስናፍቅሽ አዲስ)
ውርደቱን ሀገር ጠል ለሆኑ ጥቂት ጨካኞች ብቻ አንስጠው፡፡ ውርደቱ፤ በአንድ ሀገር ከእነሱ ጋር ስንቆጠር ለኖርን፤ በእነሱ ለተመራን፤ እነሱ እጣ ፈንታችን ላይ ሲወስኑልን ለኖሩት ለእኛ ጭምር ነው፡፡
የትግራይ ህዝብ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እንደ ህወሃት ያለ ክፉ ጠላት የለውም፡፡ ወጣቱን አዲስ አበባ በማግስቱ እንገባለን ብለው ጦርነት ሲያስጎስሙት እነሱ ግን ገደል ገብተው ተደብቀው ነበር፡፡ የእርጅና ነፍሳቸውን ለማትረፍ ቀሚስ ለብሰው፣ መነኩሴ መስለው ሲሸሸጉ ገና ብዙ መኖር ያለበትን ወጣት ግን እሳት ማገዱት፡፡
ስብሃት ነጋና ቤተሰባቸው የወጡበትን ገደል አየሁት፤ ሰውዬው በዚህ ደረጃ ሁሉን ያየች እድሜያቸውን ለማክረም ሲደክሙ ጨቅላ ወጣቶችን ግን ትግራይን ነጻ እናውጣ ብለው ጦር ሜዳ ልከው ነበር፡፡ ጦር እመራለሁ ያሉት ሰው እየተመሩ ታዝለው ወጡ፡፡
ውስኪ ተራጭተዋል፣ መርከብ ጭነው ሸጠዋል፣ መሬት ቸብችበው ከብረዋል፡፡ የተጨናገፈ ህልም የላቸውም ነበር ቀድሞውኑ ያለሙት ኢትዮጵያን አፍርሶ ራሳቸውን መስራት ነበር፡፡ በሀገራቸውም በብሔራቸውም ስም ነግደዋል፡፡
አሁንም ግን ሰላሙን፣ ገንዘቡን፣ መልካም ስሙን የነጠቁትን የትግራይ ህዝብ ዳግም እድሜውን ለመንጠቅና እድሜያቸውን ለማራዘም ለዝንጀሮ በሚፈትን ገደል ተንጠልጥለው ተደበቁ፡፡
ያንን ሰላማዊ የትግራይ ገበሬ አጉራ ጠናኝ ሆነው ለእንግልትና ለስቃይ ዳረጉት፤ ሰላሙን አሳጡት፡፡ ብልጦች ስለሆኑ መሰደድን እንኳን አልደፈሩትም፡፡ ውጤቱ ምንም ቢሆን ግድ አይሰጣቸውም፤ እንሞትልሃለን ላሉት ህዝብ ሞተህ አንድ ቀን እንደር ባይ አረመኔዎች ሆነው ታዩ፡፡
ዛሬ እነሱ የደረሱበትን ምዕራፍ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ያሉ ምሁራን የአራዊት ህግ የፈጠሩ አራዊቶች ሲሉ ቀድመው ኮንነዋል፤ እንደ ጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝ ያሉ ወጣቶች የፈራ ይመለስ ብለው ያለ ፍርሃት ሲጋፈጧቸው ይሄንን ጠባያቸውን ነግረውናል፡፡ እንደ ሙሉጌታ ሉሌ ያሉ ሰዎች በእዳ እንዳስያዙን ገልጸውልናል፡፡
ገና በአፍላ የድርጅት እድሜያቸው ለእናትና ለአባቶቻቸው የመጣ የእርዳታ እህልን ወደ ገንዘብ ቀይረው የጦር መሳሪያ ገዝተዋል፡፡ ሀገር ነጻ አወጣን ብለው ነጻ ያወጣቸውን የትግራይ ህዝብ ሳይቀር በባርነት አሰቃይተዋል፡፡ ጭካኔ ቀን ቆጥሮ በስተርጅና አዋረዳቸው፡፡ በክብር ዶክትሬታቸው ማግስት ካቴና እጃቸው ላይ ገባ፡፡ በቅንጡ ሆቴሎች የቀበጡት እንደ ሽኮኮ በገደል ውለው ያድሩ ጀመር፡፡
ለህዝብ ቢሆንማ የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው አብሮ መኖር አብሮ መስራት አብሮ ማደግ ነበር፡፡ የእኛ ኪስ ካልደለበ የእኛ ስልጣን ከልተጠበቀ ገደል ግባ ብለው ገደል ገብተው የብዙ ወጣትና አዲስ ትውልድ ተስፋ ቀበሩ፡፡ ታሪክ ይሄንን ነውር ምን ያለ ቦታ እንደሚሰጠው ከጅምሩ እያየን ነው፡፡ ሁሌም ታሪክ ራሱን እንዳይደግም ከአለፈው ጥፋት እንማር፡፡