የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ጉባዔ አካሄደ
(በድሬቲዩብ ሪፖርተር)
የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ “ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መርህ በሰላምና መቻቻል ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የምክክር ጉባዔ አካሄደ።
በክብር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ ስም በተሰየመው የዩኒቨርሲቲው አዳራሽ ታህሳስ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው የምክክር ጉባዔ ላይ ሶስት የውይይት መነሻ ፅሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በተወካዩ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ ሐጂ መስዑድ አደም በኩል የሰላም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በምክክር ጉባዔው የመክፈቻ ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት ዶ/ር ታፈረ መላኩ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ኘረዝደንትና የአማራ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ሰብሳቢ ባደረጉት ንግግር ሰላም ከየትኛውም ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብት በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። አያይዘውም ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ብዙ መከራና ችግሮችን ተቋቁማ መሻገርዋን፣ በአሁን ሰዓት የገጠማት ችግር ግን በዘረኝነት የሰከረ ፖለቲካ በማህበረሰባችን መካከል እየገባ በመተሳሰብ የተገነባውን አንድነታችንን ፈተና ውስጥ የከተተ ነው።
ከዚህ አንፃር ሁሉም ለሰላም፣ ሰላም ለሁሉም በሚል መርህ ጉባዔው መካሄዱ ትክክለኛ ወቅታዊ ነው ብለዋል።
የውይይት መነሻ ፅሁፍ ካቀረቡት ምሁራን መካከል አንዱ የሆኑትና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ምክትል ኘረዝደንት ኘሮፌሰር ሐብታሙ ወንድሙ ስለሰላምና ሰላማዊ ባህል ገለፃ አድርገዋል።በሰዎች መካከል የሀሳብ ልዩነቶች መኖር የሚጠበቅና ተፈጥሮአዊ መሆኑን የጠቆሙት ኘሮፌሰር ሐብታሙ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ በውይይት፣ በክርክር፣ በድርድር እንዲሁም በሽምግልና መንገድ ማጥበብ ከተቻለ ግጭት ሊኖር እንደማይችል ጠቅሰዋል።
ለግጭት መንስኤ ከሆኑ በርካታ ምክንያቶች መካከል የተዛባ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል፣ የተዛቡ መረጃዎችና ስሜታዊነት መሆናቸውን፣ እነዚህን ለመፍታት የየብሄረሰቡን ባህል፣ መብትና ጥቅም እንዲሁም የጋራ ፍላጎት ማክበር፣ ከስሜት ይልቅ በዕውቀትና መረጃ ላይ ተመስርቶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል።
የጉባዔው ሀሳብ አመንጪና አዘጋጅ የሆኑትና የሰላምና ባህል ምሁር ዶ/ር ወሰን ባዩ በበኩላቸው ሰላምን የምንፈልገው ለምንድነው? ለማንነው? ብለው ከጠየቁ በኋላ ሰላምን የምንፈልገው ለማንም ብለን ሳይሆን ለራሳችን ጥቅም ስንል መሆኑን አስረድተዋል።ኢትዮጵያዊ የሆኑ እሴቶች ማለትም መከባበር፣አንድነትን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ አብሮ መስራት ለሰላም ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።
ዕጩ ዶ/ር መሳሽ ካሳዬ መቻቻልና የሰላም ባህልን በተመለከተ ባቀረቡት ፅሁፍ መቻቻል ለሰላም ባህል መሰረት መሆኑን ጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲዎች የትንሿ ኢትዮጵያን እንደሚወክሉ፣በዩኒቨርሲቲዎች የሚኖሩ የአመለካከት፣ የሀይማኖት፣ የባህል ብዝሀነት እንዲጣጣም መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
ከ2010 አጋማሽ ጀምሮ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ግጭቶች መከሰታቸውን የጠቀሱት ዕጩ ዶ/ር መሳሽ በ2012 ዓ.ም ብቻ ከ45 ዩኒቨርሲቲዎች በ28ቱ በተቀሰቀሰ ግጭት ለ12 ተማሪዎች ሞት መንስኤ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ዓላማቸው የመማር ማስተማር፣ ምርምርና ጥናት ማካሄድ፣ ማህበረሰባዊ አገልግሎት መስጠት መሆኑን የጠቆሙት ዕጩ ዶክተርዋ አሁን አሁን አራተኛ ተግባር እየያዙ ነው። እሱም ሰላምን መገንባት ነው ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል።