Connect with us

ከስም ማጥፋት  መለስ የኢትዮጵያ መርከቦች እውነታ…

ከስም ማጥፋት መለስ የኢትዮጵያ መርከቦች እውነታ...
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ከስም ማጥፋት  መለስ የኢትዮጵያ መርከቦች እውነታ…

ከስም ማጥፋት  መለስ የኢትዮጵያ መርከቦች እውነታ…

~ ከኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን

በኢትዮጵያ መርከቦችን የመመዝገብ እንዲሁም አገልግሎት መስጠት ሲያቆሙ የመሰረዝ ኃላፊነት በአዋጅ ቁጥር 549/99 የተቋቋመ እና ተጠሪነቱ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር በሆነው የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን የሚከናወን ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁለት ዓይነት የመርከብ /የሐመር/ የምዝገባ ዓይነት ያለ ሲሆን እነሱም፡-

  1. “closed registry” አገራት ብሔራዊ የመርከብ ድርጅቶቻቸውን ብቻ የሚመዘግቡበት የምዝገባ ዓይነት ሲሆን እንዲሁም
  2. “Open registry” ወይም “Flag of Convenience” የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው አገራት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ በሌሎች አገራት የመርከብ ምዝገባ ሥርዓት እና ሕግ መሠረት የሚመዘገቡበት የምዝገባ ዓይነት በመባል ይታወቃሉ፡፡

ኢትዮጵያ እየተጠቀመች ያለችው የመጀመሪያውን “closed registry” የምዝገባ አይነት ብቻ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን በመጀመሪያው “closed registry” የምዝገባ አይነት ብሔራዊ መርከቦችን እየመዘገበ ይገኛል፡፡ እስካሁን በባለስልጣን መ/ቤቱ ተመዝግበው የሚገኙ ባለቤትነታቸው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስራ አንድ (11) መርከቦች/ሐመሮች/ ሲሆኑ ዘጠኝ(9) ደረቅ ጭነት የሚጭኑ(General Cargo) እና ሁለት የነዳጅ ጫኝ(Oil) መርከቦች /ሐመሮች/ ብቻ ናቸው፡፡ ከነዚህ መርከቦች (ሐመሮች) ውጭ በኢትዮጵያ የተመዘገበ መርከብ የሌለ መሆኑን ከዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት (IMO) የመረጃ ማዕከል (IMO Docs) ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የመርከቦች /የሐመሮች/ የመረጃ ምንጭ ሆነው የሚያገለግሉት የመርከብ መዝጋቢው አገር እና የዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት (IMO) ብቻ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ተመዝግበው የሚገኙ መርከቦችን የሚያረጋግጡትና ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ መሆን የሚችሉት የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን እና የዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት (IMO) ብቻ ናቸው፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ “የኔታ ቲዩብ”  በተባለው የማኀበራዊ ሚዲያ በታህሣሥ 22 ቀን 2ዐ13 ዓ.ም “የኔታ ትንታኔ” በሚል ኘሮግራም ላይ ‹‹መርከብ የሸጠው ባለሥልጣን››/ ‹‹በኢትዮጵያ ስም አደንዛዥ እጽ የሚነገድባቸው መርከቦች ፈቃድ የሰጡ ባለስልጣናት ሚስጥር›› በሚል ርዕስ ስለመርከብ ምዝገባ እና በአገራችን ተመዝግበው ስለሚገኙ መርከቦች አንድ ሰዓት ከሃያ ደቂቃ በላይ በፈጀ ትንታኔ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን መረጃ ሳይጠየቅ ከበይነ መረብ በተገኘ መረጃ ብቻ የባለሥልጣን መ/ቤቱን እና የመንግስት ባለስልጣናትን ሥም የሚያጠለሽ ትንታኔ ቀርቧል፡፡

በትንታኔው ላይ ኢትዮጵያ 9 መርከቦች ብቻ እያላት 29 መርከቦች ተመዝግበዋል፣ ሰንደቅ ዓላማ በህገወጥ መንገድ ተሸጧል፣ በሕገ ወጦቹ ሕጋዊ መርከቦች ሊታገዱ ይችላሉ… ወዘተ የሚሉ ትችቶች ተካተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መርከቦች #አስራ_አንድ (11) ሆነው ሳለ #ዘጠኝ(9) መባሉ እንዲሁም ኢትዮጵያ የውጭ መርከቦችን በ “Open registry” የምዝገባ ስርዓት የመመዝገብ ሥራ ባልጀመረችበትና ባላከናወነችበት ተጨማሪ 18 መርከቦች ተመዝገበውና ሰንደቅ ዓላማ በህገወጥ መንገድ ተሸጧል ተብሎ ያለ ተጨባጭ ማስረጃ እና ከታማኝ ምንጭ ባልተወሰደ መረጃ ብቻ ባለስልጣኑን መ/ቤት እና የመንግስት ባለስልጣናትን ስም ማጠልሸት ተገቢነት የለውም እንላለን፡፡

በተጨማሪም በሕገወጥ መርከቦች ሕጋዊ መርከቦች ሊታገዱ ይችላሉ የሚለው ትንታኔ ስህተት ከመሆኑም ባለፈ የዓለም አቀፍ የመርከብ አሰራርን ካለማወቅ የሚመነጭ ነው፡፡ አንድ መርከብ የሚታገደው ፈቃድ በተሰጠበት የሕግ ማዕቀፍ ጥሶ ሲገኝ እንጂ ባልተመዘገበ መርከብ ሰበብ ሕጋዊ መርከብ የሚታገድበት ሕጋዊና ዓለም አቀፋዊ አሰራር በፍፁም የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ‹‹የየኔታ ቲዩብ›› ተንታኝ ግለሰብ የተጠቀሙት የመረጃ ምንጭ “vessel finder data base”  እና “Marine radar” የተባሉ በዋናነት የመርከብ ምዝገባን ሳይሆን በጉዞ ላይ የማሪታይም ሴኩሪቲን ለማገዝ በተሰሩ “Automatic Identification System” በሚባል በሐመሮች ላይ የተገጠመ መሳሪያ በሚያስተላልፈው ዲጂታል መረጃ መሰረት በማድረግ ሲሆን ዳታው ለኢንፎርሜሽን አላማ ብቻ እንጂ ለዳታው ትክክለኛነት እና ተአማኒነት ኃላፊነት እንደማይወስድ የገለጸበት እያለ እንደ ታማኝ መረጃ አድርጎ በብቸኛ መረጃነት መጠቀሙ፤ እንዲሁም ተንታኙ በተደጋጋሚ ያለአግባብ የኢትዮጵያ ባንድራ ተሸጦባታል ተብላ የተጠቀሰችሁ “Laura Corilett” አንዷ ስትሆን ይህቺ መርከብ ቀደም ሲል የ “Cape Verdi” ዜግነት የነበራት ሲሆን አሁን ግን በዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት(IMO) መረጃ መሰረት ዜግነቷም ሆነ የ “Call Sign” የማይታወቅ መሆኗ የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ በድፍረት ስም ማጥፋት በማንኛውም መስፈርት ተገቢነት አይኖረውም፡፡ ተንታኙ ግለሰብ እውነት ችግሩን ለመንቀፍ ከሆነና ለሀገር ተቆርቋሪ ከሆኑ ለምን የዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት(IMO) መረጃን አላረጋገጡም?

በመሰረቱ መረጃን ለህዝብ አሳውቃለሁ የሚል ማንኛውም አካል ወይም የሚዲያ ተቋም የጉዳዩን ባለቤት ሃሳብ ማካተት ይገባው ነበር፡፡ የ “የኔታ ቲዩብ” ግን ይህን አላደረገም፡፡

እርግጥ ነው አገራችን ዓባል የሆነችበት የዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት(IMO) ትልቅ ሥጋት እየሆነበት የመጣው የተጭበረበረ የመርከብ ዜግነት (Fraudulent Ships Nationality) አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ ተኝታዩ የተጭበረበረ የመርከብ ዜግነት አለ ብለው በድፍረት የተናገሩትን ያክል የዓለም ስጋት የሆነውን የተጭበረበረ የመርከብ ዜግነት መኖሩን መፈተሽና ያገኙትን መረጃ ከዚሁ የዓለም ስጋት ጋር ማጣጣምና እውነታውን መረዳት ነበረባቸው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ‹‹ተንታኙ ግለሰብ የተጠቀሙት የመረጃ ምንጭ “vessel finder data base” እና “Marine radar” መሰረት የኢትዮጵያን መርከብ ዜግነት እንዳዩት ሁሉ ለምን የሌሎች አገራትን መርከቦችስ አላዩም? ቢያዩ ኖሮ እውነታውን መረዳት ይችሉ ነበር፡፡

ተንታኙ ግለሰብ በተጠቀሙት የመረጃ ምንጭ እና በዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት(IMO) የመረጃ ማዕከል (IMO Docs) መሰረት በማነፃፀር የሌሎች አገራትን መርከብ ዜግነት ጭምር በማካተት የተንታኙን መረጃ መሰረተቢስ መሆኑን እንደሚከተለው እንመልከት፡፡

  1. #ጅቡቲ… በዓለም ዓቀፍ የማሪታይም ድርጅት(IMO) የመረጃ ማዕከል (IMO Docs) 28 መርከቦች ሲኖሯት በ “vessel finder data base” እና “Marine radar” መረጃ ግን 131 መርከቦች መባሉ፣
  2. #ኤርትራ… በዓለም ዓቀፍ የማሪታይም ድርጅት(IMO) የመረጃ ማዕከል(IMO Docs) 9 መርከቦች ሲኖሯት በ “vessel finder data base” እና “Marine radar” መረጃ ግን 46 መርከቦች መባሉ፣
  3. #ኬንያ… በዓለም ዓቀፍ የማሪታይም ድርጅት(IMO) የመረጃ ማዕከል(IMO Docs)  30 መርከቦች ሲኖሯት በ “vessel finder data base” እና “Marine radar” መረጃ ግን 123 መርከቦች መባሉ፣
  4. #ደቡብ ሱዳን… በዓለም ዓቀፍ የማሪታይም ድርጅት(IMO) የመረጃ ማዕከል (IMO Docs) ምንም መርከብ ሳይኖራት በ “vessel finder data base” እና “Marine radar” መረጃ ግን 74 መርከቦች መባሉ፣
  5. #ሱዳን… በዓለም ዓቀፍ የማሪታይም ድርጅት(IMO) የመረጃ ማዕከል(IMO Docs)  21 መርከቦች ሲኖሯት በ “vessel finder data base” እና “Marine radar” መረጃ ግን 182 መርከቦች መባሉ፣
  6. #ሶማሊያ… በዓለም ዓቀፍ የማሪታይም ድርጅት(IMO) የመረጃ ማዕከል (IMO Docs) ምንም መርከብ ሳይኖራት በ “vessel finder data base” እና “Marine radar” መረጃ ግን 531 መርከቦች መባሉ፣
  7. #ኢትዮጵያ.. በተመሳሳይ መልኩ በዓለም ዓቀፍ የማሪታይም ድርጅት(IMO) የመረጃ ማዕከል (IMO Docs) 11 መርከቦች ሲኖሯት በ “vessel finder data base” እና “Marine radar” መረጃ ግን 29 መርከቦች መባሉ ‹‹ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው›› የሚለውን ሀገርኛ አባባል ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በአጠቃላይ የተንታኙ ግለሰብ የመረጃ ምንጭ የአገራችንም ሆነ የሌሎች አገራት መርከብ ዜግነት መረጃ ከታማኝ ምንጭ አለመወሰዱን የሚያረጋግጥ እና ትችቱም መሰረተ ቢስ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

ታዲያ ለምን የመረጃ መጣረስ ተፈጠረ ብሎ መጠየቅ ግን ተገቢ ነው፡፡ የመርከብ ዜግነት ማጭበርበር ዓለም አቀፍ ስጋት ጋር ተያይዞ ሊፈጠር እንደሚችል ይገመታል፡፡ የየኔታ ቲዩብና ተንታኙ ግለሰብ ይህን ቢጠይቁና ችግሩን በጋራ ለመቅረፍ ቢሞክሩ እሰየው ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ችግርን በጋራ ከመፍታት እና ሀገርን በጋራ ለማሳደግ ከመጣር ይልቅ ተቋምንና የመንግስት ባለስልጣናትን መውቀስ የተለመደ ድርጊት መሆኑ ያሳዝናል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የቀረበበት ወቀሳ በትክክለኛ ማስረጃ ላይ ያልተደገፈ፣ ስህተት ቢሆንም የመርከብ ዜግነት ማጭበርበር ፍፁም የለም ብሎ ግን አይከራከርም፡፡ ምክንያቱም የመርከብ ዜግነት ማጭበርበር ዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑን በመረዳት ከአባል ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን የተነሳውን ችግር በባለስልጣን መ/ቤቱ የተፈፀመ ባይሆንም ችግሩን ለማጣራትና እውነት ሆኖ ከተገኘ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን በዓለም አቀፍ የማሪታይም ሕግ እንዲዳኝ ጥረት የሚያደርግና እውነታውን ወደፊት የሚገልፅ መሆኑን ለህዝባችን መግለፅ እንወዳለን፡፡

ማንኛውንም ተቋም ይሁን የመንግስት ኃላፊ ስም ያላግባብ በማጠልሸት እውነታ ማገኘት እንደማይችል ተቋማችን ያምናል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም የሚዲያ አካል የሚያወጣው መረጃ የተቋማትን ሀሳብ ባካተተ፣ በእውነተኛና ተዓማኒነት ባላቸው የመረጃ ምንጮች ሊመሰረት ይገባል እንላለን፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top