እርምጃ የተወሰደባቸውን የህወሓት አባላት ስም ዝርዝር ይፋ ሆነ
የአገር መከላከያ የማይካድራውን ጭፍጨፋ የመራውን ኮሌኔል የማነ ገብረሚካኤልን ጨምሮ እርምጃ የተወሰደባቸውን የህወሓት ቡድን አመራሮች ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
ከተማረኩ የህወሓት ቡድን አመራሮች መካከል የቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሄር እንደሚገኙበት ተገልጿል።
የመከላከያ ሃይል ስምሪት መምሪያ ሃላፊ ብርጋዴል ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው በጉዳዩ ላይ ለኢዜአ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው በርካታ የጁንታው ከፍተኛ አመራሮችና ወታደራዊ አመራሮች መማረካቸውንና መደምሰሳቸውን ገልፀዋል።
ብርጋዴል ጄኔራሉ የመከላከያ ሃይልና የፌዴራል ፓሊስ በቅንጅት በወሰዱት እርምጃ በርካቶች መማረካቸውንና እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑት መደምሰሳቸውን አስታውቀዋል።
የተደበቁ የአጥፊው ቡድን አባላትን እግር በእግር እየተከታተሉና እየፈተሹ መሆኑን ገልፀው ፍለጋው ከሰፊ ወደ ጠባብ መጥቷል ብለዋል።
እየተካሄደ ባለው ፍተሻ የቡድኑ አመራሮች በየዋሻውና በየቤተክርስቲያኑ ተደብቀው መገኘታቸውንና የቤተክርስቲያን አባቶችን አልባሳት ለብሰው የተገኙ መኖራቸውን ተናግረዋል።
ብርጋዴል ጄኔራል ተስፋዬ ከመከላከያ ሠራዊት ከድተው ቡድኑን በተቀላቀሉና እጅ ስጡ ሲባሉ አንሰጥም ባሉ አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል።
በዚሁ መሰረት የማይካድራውን ጭፍጨፋ የመራው ኮሌኔል የማነ ገብረሚካኤልን ጨምሮ እርምጃ የተወሰደባቸውን የህወሓት ቡድን አመራሮች ዝርዝር ይፋ አድርገዋል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል ኮሎኔል አለም ገብረመድህን፣ ኮሎኔል ቢንያም ገብረመድህን፣ ኮሎኔል አምባዬ፣ ኮሎኔል ማሾ፣ ኮሎኔል ይርጋ ስዩም፣ ኮሎኔል ሃዱሽ፣ ኮሎኔል አጽብሃ፣ ኮሎኔል ተስፋዬ ገብረመድህን፣ ኮሎኔል ዮሃንስ ካልአዩ፣ ኮሎኔል ተክለእግዚአብሄር፣ ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኔ ቶላ እና ሌሎች በስም ያልተገለጹ አራት ኮሎኔሎችና ሁለት የዞን አመራሮች ይገኙበታል።
እጅ ከሰጡ የጁንታው አመራሮች መካከልም የቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር እንደሚገኙበት አክለዋል።
በተመሳሳይ ሃዱሽ ዘውገ ገዛኸኝ የክልሉ ኦዲት ሀላፊ የነበረ፣ ሰለሞን ህሉፍ ንጉሴ የክልሉ ልማት ስልጠና ሀላፊ የነበረ፣ ኪዳነማሪያም ገብረክርስቶስ ፋሲል የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ የነበረ፣ ባህታ ወልደሚካኤል የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ የነበረ፣ ሀጎስ ወልደኪዳን ገብረማሪያም የክልሉ ኢኮኖሚ ቢሮ የልማት እቅድ አስተባባሪ እጅ መስጠታቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በርካታ ቁጥር ያላቸው የሚሊሻና ልዩ ሀይል አባላት እጃቸውን መስጠታቸውን ነው የተናገሩት።
ከተማረኩ የጁንታው አባላት ዶክተር ዓለም ብርሃኔ፣ ኮሎኔል መብርሃቱ ገብረመድን፣ ኮሎኔል ሃዱሽ ሃጎስ፣ ኮሎኔል ህሉፍ ተ/መድህን፣ ሌተናል ኮሎኔል ተክለ ህይወት አሰፋ ይገኙበታል ብለዋል ብርጋዴል ጄኔራሉ።
ለጥፋት ሲቀሰቅስ የነበረ የህወሓት ቡድን አባል ገብረአምላክ ይኸብዮ የተባለ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሁር መማረኩንም ገልፀዋል።
የተደበቁ የህወሓት አመራሮች ከማንም ጋር የሚገናኙበት ዕድል እንደሌላቸው ገልጸው፤ በየቤተክርስቲያንና በየዋሻው ራሳቸውን ቀይረው ሲንቀሳቀሱ እየተያዙ መሆኑን ገልጸዋል።
የጥፋት ቡድኑ የራሱ አመራሮች ሲሞቱ በሰውነታቸው ላይ የፈፀመውን ጭካኔ የተሞላበት ደርጊትም ገልፀዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችን ይዞ በቅርቡ ዜናው ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚደርስ ተናግረዋል።(EBC)