Connect with us

የሀውጃኖ እውነት ቆይቶውም ቢሆን ተገልጧል

የሀውጃኖ እውነት ቆይቶውም ቢሆን ተገልጧል
አብመድ

ነፃ ሃሳብ

የሀውጃኖ እውነት ቆይቶውም ቢሆን ተገልጧል

የሀውጃኖ እውነት ቆይቶውም ቢሆን ተገልጧል

የቀድሞው የኢህዴን ታጋይ ነበሩ፤ ህወሓትን ከልጅነት እስከ እውቀት ያውቁታል። በሚቻላቸው ሁሉ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል። በተለይ ደግሞ በራያ ሕዝብ ላይ ሕወሓት ሲያደርሰው የነበረውን ለሕዝብ እያጋለጡ ሲታገሉ ቆይተዋል ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ። ሕወሓት አላማውን ለማስፈፅም የነበረውን አካሄድ በተመለከተ ዶክተር ሲሳይ ከአብመድ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ሕወሓት የሚፈልጋቸውን አካባቢዎች ለመውሰድና የሚፈልገዉን ሀገር ለመመስረት አማራን ማደካም፣ ማስወገድና ርዕስቱን ማሳጣት ቀዳሚው ዓላማው ነበር። የትግራይን ክልል በራያ በኩል ራያ ቆቦን ጨምሮ ከአለዋ ምላሽ፣ በጎንደር በኩል በላይ ወገራ አውራጃ ድረስ፣ በታች አርማጭሆና መተማን በመያዝ፣ ቋራን ለቤኒሻንጉል ክልል በመስጠት ከቤኒሻንጉል ጋር ለመዋሰን አልሞ ሲሰራ መቆየቱን ነግረውናል።

በአልዋ ምላሽ ያለው አልሳካ ሲለው ከዋጃ መለስ ወስዶ ቆይቷል። በጎንደርም ያለው ሁሉ ባይሳካለትም ወልቃይት ጠገዴን ወስዶ ቆይቷል። የትግራይ ክልል የማይደርስባቸውን መተከል፣ ደራና ሌሎችን ወደሌሎች ክልሎች የማዋሰን ሥራ ሰርቷል።

በውሸት የሚያካልሏቸውን አካባቢዎች በመጻሕፍ ደረጃ በማሳተም ሲያስተምሩበት መቆየታቸውንም ዶክተር ሲሳይ አንስተዋል። ህወሓት ትግራይ አንድ ቀን ራሷን የቻለች ሀገር ልትሆን እንደምትችል ያልም ነበር። በተለይም ወደ መጨረሻው አካባቢ ራሷን የቻለች ሀገር የሆነች ለማስመሰል ጥረት ያደርጉ እንደነበር ያነሱት ዶክተር ሲሳይ ለአብነት በሕግ ማስከበሩ ሂደት ቃል አቀባዮቹ የትግራይ መከላከያ ሠራዊት እያሉ ይጠሩ ነበር፡፡

የመከላከያ ሠራዊት የሚኖረው አንድ ሀገር ብቻ ነው፡፡ በክልል ደረጃ መከላከያ ሠራዊት የሚባል የለም ነው ያሉት። የጎንደር ሰው ከኤርትራ ጋር በኢኮኖሚ፣ በማሕበራዊና በባሕላዊ ጠንከር ያለ ግንኙነት ስለነበረው የጎንደርና የኤርትራ ሕዝብ እንዳይገናኝ እንቅፋት መሆን ሌላኛው ፍላጎቱ እንደነበርም አንስተዋል ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ።

የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት የአማራን አከርካሪ መስበር፣ የአማራን ሕዝብ ቁጥር ማሳነስና የአማራን መሬት ማጥበብ ዋነኛ ዓላማው እንደነበረም ነግረውናል።

‹‹አማራ ተስፋፊ ነው፣ እርስት አስመላሽ ነው›› ሲል የነበረው የወሰደዉ እንዳይመልስበት ስለፈራ ነው፡፡ አማራ የማንንም ወስዶ አያውቅም፤ አይወስድምም ነው ያሉት። ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል የራያ ተወላጆች እንደማንኛውም የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ቅድሚያ ይሰጡ ስለነበረ ኢህዴንን ተቀላቅለዋል። ዶክተር ሲሳይም የኢህዴን ታጋይ ነበሩ። በነበረው ትግልም የራያ ወጣቶች ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።

በዚያ ወቅት የትህነግን የበላይነት አስቀድሞ የተረዳውና አካሄዱ ሀገር እንደሚያፈርስ ያወቀው የራያው ተዋላጅ ይርጋ አበበ በትግል ስሙ (ሀውጃኖ) የህዋሓትን አካሄድ አጥብቆ ይቃወም ነበር። ሃውጃኖ የኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና ጀግና ጦረኛ የከበረ ሰው ነው። የትህነግ አካሄድ ከጅምሩ ያልጣመው ሀውጃኖ የህወሓትን ኀላፊዎች ‹‹ግንኙነታችን የድርጅት ከሆነ እኩል መሆን አለብን›› ይላቸው ነበር።

በዚህ ምክንያት ‹‹አንተ በህወሓት ላይ የተለየ አቋም ይዘሃል፤ ጥላቻ አሳድረሃል በማለት ከኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴነት አገዱት። ከነበረው ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊነትም ዝቅ እንዲል አደረጉት። ሀውጃኖ ግን ከሃሰቡ ንቅንቅ አላለም ነበር። አስቀድመው የፈሩትና የተሸፈነውን አካሄዳቸውን ያየው ሀውጃኖ መለስ ዜናዊና ታምራት ላይኔ ሀገረ ሠላም ድረስ አስጠርተው ሊያሳምኑት ሞክረው እንደነበረ አጫውተዉናል።

ሀውጃኖ ግን እውነት ነበረውና ከእውነት ንቅንቅ አላለም። ሀሳባቸውን አልቀበልም አለ። አካሄዳቸው የጋራ የሆነች ታላቅ ሀገር ለመምራት እንደማያስችልም በተደጋጋሚ ነገራቸው። ቢችሉ በመንገዳቸው እንዲሄድ ካልሆነ ግን ከመንገዳቸው ላይ እንዳይቆም ለማድረግ ወሰኑ። አማራጭ ሲያጡ ሊያስሩት ሞከሩ፤ ስለ አውነት አልታሰር አለ። በነበረው የተኩስ ልውውጥም ሀውጃኖ ተገደለ።

እውነትን እና እውነተኛን የመግደል ሥራቸው በዚያ ዘመን የጀመረ ነበር አሉ ዶክተር ሢሣይ። ከሀውጃኖ መሞት በኋላ ዶክተር ሲሳይን ጨምሮ አንዳንድ የኢህዴን ታጋዮች የሕወሓት አካሄድና የበላይነት ሀውጃኖን የሚያክል ሰው አሳጥቶናል፤ በቀጣይም ሌላ ችግር ይፈጠራል እያሉ መታገል ጀመሩ። አብዛኞቹ የኢህዴን ታጋዮች ግን ዝምታን መርጠው ነበር። ‹‹እንደ ሀውጃኖ ባልሞትም ጫናው ከፍተኛ ነበረ›› ነው ያሉት ዶክተር ሲሳይ ያን ዘመን ሲያስታውሱ።

ሕወሓት የአማራን ርዕስቶች ሲያካልል የኢህዴን ታጋዮች ‹‹በአማራ ሆኑ በሌላው ሆኑ ለአስተዳደር እንዲመች እንጂ አንድ ሀገር ናቸው›› የሚል የዋህ እሳቤ ነበራቸው፡፡ በአንፃሩ የሕወሓትን መስፋፋት የሚደግፉ የኢህዴን አባላት ነበሩ ነው ያሉት ዶክተር ሲሳይ። ህወሓቶች እስከመጨረሻው ድረስ መሬት የመንጠቅና የመስፋፋት ሥራ ሲሠሩ መቆየታቸውንም ነግረውናል።

ህወሓት አካባቢዎችን ሲያካልል የተቃወሙ ሰዎች መገደላቸውን አስታውሰዋል። የሕወሓት የመስፋፋት ጉዳይ የማይሞት ይመስል እንደነበርም ነግረውናል። በሕወሓት የአገዛዝ ዘመን የራያ ሕዝብ በደሎች ሲደርሱበት እንደነበርም ዶክተር ሲሳይ አስረድተዋል። የራያ ሕዝብ ደርግን ለመጣል በተደረገው ውጊያ ተጎጂ ነበር፡፡

በራያ ሕዝብ ሊተገበሩ የነበሩ የልማት ሥራዎች እንዲቆሙ ተደርገዋል። የራያ ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖር ማድረግ፤ በፈለገው ጊዜ የሚታሰር፤ የሚገረፍ፤ የሚፈናቀል ሕዝብ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ለምን ብሎ የጠየቀ ደግሞ ‹‹አካባቢውን ለቀህ ውጣ! ከመሬቱ እንጂ ከእናንተ ምንም የለንም›› ይባሉ እንደነበረ ነግረዉናል፡፡ ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይማሩ ማድረግ ሌላኛው የሕወሓት ሥራ ነበር።

የራያ ልጆች በብሔራዊ ፈተና በትግርኛ ቋንቋ ‹ቢ› እና ከዚያ በላይ ካላመጡ በትግራይ ውስጥ በሚገኙ ኮሌጆች መማር እንደማይችሉም ዶክተር ሲሳይ አስታውሰዉናል። ይህ መስፈርት የትግርኛ ተናጋሪዎችን ብቻ ያማከለ እና ወደ ትግራይ ተካለው የነበሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያገለለ ማሳያ መሆኑን ነው ያመላከቱት።

ለተጨማሪ ትምህርት ስልጠና እድል ያልነበራቸው እና የሥራ እድል ተጠቃሚ የማይሆኑት የራያ ልጆች ወደ አረብ ሀገራት ለመሰደድ ሲገደዱ መቆየታቸውንም አስረድተዋል። በተለይም ሀገራዊ ለውጥ ከመጣ በኋላ የራያ ልጆች በአማርኛ ቋንቋ እንዳይናገሩ፣ እንዳይፅፉና ሌሎችም ጫናዎች ሲደርሱባቸው እንደነበረ አንስተዋል። የራያ ሕዝብ ታፍኖ የኖረ፤ ነፃነት የጠማው ሕዝብ ነበር ነው ያሉት።

ባለፈው ሥርዓት ራያ በራያ ተወላጆች ስትመራ እንዳልነበርም ዶክተር ሲሳይ አስታውሳዋል። አሁን ለራያ ነፃነት መጥቷል፤ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ ነፃነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ከተቀረው የአማራ ሕዝብ ጋር ትስስሩን ማጠናከር ይገባል። ስለ እውነት ህይወታቸውን ያጡና ስለ እውነት የታገሉ ሁሉ አውነትን ያዩ ይመስላል። የሀውጃኖ እውነት ቢዘገይም ተገልጧል።

(ታርቆ ክንዴ ~ አብመድ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top