በመጨረሻም ሚድሮክ ወርቅ አሸነፈ
የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሴራ ተጠልፎ ከገባበት ቅርቃር ወጥቷል። በታከለ ኡማ የሚመራው የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ያገደውን ፈቃድ መመለሱንና ከቀጣይ ወር ጀምሮ ፋብሪካው ወደመደበኛ ስራው እንደሚገባ በይፋ ተነግሯል።
ፋብሪካው ከሁለት ዓመት በላይ ለምን ሊታገድ ቻለ? ፋብሪካው በአካባቢና በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት አድርሷል የሚል ክስ በተለይም በእነጀዋር መሐመድ በመቀጣጠሉ ነበር።
እናም ጉዳዩ በገለልተኛ የውጭ ሀገር ባለሙያዎች ተጠና። የተባለው ውንጀላ እውነት ሆኖ መገኘት ግን አልቻለም።
መንግስት ያለበቂ ጥናት የወሰደው የእገዳ ውሳኔ በኩባንያው ላይ ብቻ ሳይሆን እንደሀገርም ከባድ ኪሳራን ያስከተለ ቢሆንም በመጨረሻ ለጉዳዩ እልባት መሰጠቱ በአዎንታ የሚወሰድ ነው።
ከምንም በላይ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩኘ የቀድሞ ሲኢኦ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ እገዳ እንዲነሳ እልህ አስጨራሹን ጉዞ በከፍተኛ ትግዕስትና ጥበብ በመወጣት ለዛሬው ድል መሰረት በመጣላቸው እንደአንድ ዜጋ ከልብ አመሰግናቸዋለሁ።
ከወራት በፊት ለመንግስት አቅርቤው የነበረ ተማፅኖ ለትውስታ ያህል እንደገና አቅርቤዋለሁ። መልካም ንባብ።
***
እነሆ ድብቁ ጥያቄ አፍጥጦ መጣ
ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አዶ ሻኪሶ አካባቢ በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ ከተሰማራ ከ 20 ዓመታትን በላይ አስቆጥሯል፡፡ ሌሎች የመንግሥትና የግል ባለሃብቶችም በአካባቢው ከ70 ዓመታት በላይ በተመሳሳይ ሥራ ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ነው።
ይህም ሆኖ ካለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ “በአካባቢ ላይ ብክለት እያስከተለ ነው፣ በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት ደርሷል” በሚል የተሳሳተ ክስ በሚያቀርቡ አንዳንድ ወገኖች አማካይነት ኩባንያው ፈቃዱ እንዳይታደስ ወይንም እንዲዘጋ ዘመቻዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከስራ ታግዶ ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን እንዲጠና ተደርጎም ነበር፡፡ የካናዳ ባለሙያዎች ዝርዝር ጥናት አድርገው እንደተባለው ኩባንያው አለም አቀፍ ደረጃን አሟልቶ እየሰራ መሆኑን በማረጋገጥ ለአሉባልታው ሳይንሳዊ መልስ ሰጡ፡፡
ይህ ጥናት ከተጠናቀቀ ቢቆይም ይፋ ማድረግ ያለበት አካል ዝምታን መርጦ ቆየ፡፡ እነሆ ዛሬ ደግሞ “አካባቢ በክሏል” የሚለው አጀንዳ ተቀልብሶ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከሚድሮክ ወርቅ ማዕድን የባለቤትነት ድርሻ እንደጠየቀና የሮያሊቲ ክፍያ እና የባለቤትነት ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ፣ በኩባንያው፣ በክልሉ መንግሥት እና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውይይት እየተደረገበት እንደሆነም አቶ ታከለ ኡማን ጠቅሶ ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቦናል፡፡ ገራሚ ነው፡፡ ለሁለት ዓመት ያህል ትልቅ ኢንቨስትመንትን ያለስራ አስቀምጦ በባለሃብቱና በሀገር ላይ ኪሳራ ሳይከሰት በፊት እኮ ይህን ጥያቄ አቅርቦ መነጋገር ይቻል ነበር፡፡ ይህን ጥያቄ ቀስ ብሎ ከመሳቢያ ውስጥ ለማውጣትና መደራደሪያ ለማድረግ ሀገር በየዓመት ከ400 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ እንድታጣ መደረጉ የዘርፉን መሪዎች ትዝብት ላይ የሚጥል አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡
የሆነስ ሆነና የፌዴራል መንግስት ከኩባንያው የታወቀ ሼር አለው፡፡ ኩባንያው ከዚህ ቀደም ሚድሮክ በሮያሊቲ፣ በተለያዩ የግብር ክፍያዎች ከአጠቃላይ ገቢው እስከ 50 በመቶ ወጪ በማድረግ በየዓመቱ ለፌዴራልና ለክልል መንግሥታት ገቢ ያደርጋል። የኦሮሚያ ክልልም ተጠቃሚ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ኩባንያው ከኢንቨስትመንቱ በተጨማሪም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ያላሰለሰለ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ የአሁኑ የፌዴራል ገቢን ጠቅልሎ የመውሰድ ጥያቄ መቅረቡ ሳይሆን በምን መልኩ ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ወደፊት የምናየው ነው፡፡
እዚህ ላይ አንገብጋቢው ጥያቄ የስራ ዋስትናው አደጋ ውስጥ የወደቀው የሰራተኞች ጉዳይ ነው፡፡ ከ1 ሺ 200 በላይ የሻኪሶ አካባቢ ሠራተኞች ፋብሪካው ከዛሬ ነገ ወደስራ ይገባ ይሆን ወይ የሚለው የህልውና ጥያቄ ዘወትር የሚያነሱት ነው፡፡ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ ይህን ጥያቄም ጭምር ከግምት በማስገባት በእጃቸው ላይ የሚገኘውን የሚድሮክ ወርቅ አጀንዳ ሁለቱንም ወገን አሸናፊ በሚያደርግ መልኩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንዲሰጡት እንደአንድ ዜጋ እማጸናለሁ፡፡(ጫሊ በላይነህ)