Connect with us

የዜጎች በህይወት የመኖር መሠረታዊ መብት ይከበር

የዜጎች በህይወት የመኖር መሠረታዊ መብት ይከበር
Ethiopian press agency

ነፃ ሃሳብ

የዜጎች በህይወት የመኖር መሠረታዊ መብት ይከበር

የዜጎች በህይወት የመኖር መሠረታዊ መብት ይከበር

(ፍቱን ታደሰ)

ከሰብዓዊ መብቶች ሁሉ ቅድሚያውን የሚይዘውና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሰው ልጆች በህይወት የመኖር መብት ነው፡፡ ዜጎች በህይወት ሲኖሩ ነው ስለ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ፣ መብቶቻቸው እንዲሁም የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶቻቸውን ማሰብ የሚቻለው፡፡ በሃገራችን በተለይ ከለውጡ በኋላ ዜጎች ለህይወታቸው ዋስትና ማግኘት የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ ዜጎች በብሄራቸው፣ በሃይማኖታቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት በጅምላ የሚገደሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

ከ2012 ዓ.ም መስከረም ወር ጀምሮ እንኳን ያለውን ሁኔታ ብንመለከት በቡራዩ፣ በአርሲ፣ በምስራቅ ሐረርጌ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ በማይ ካድራ፣ በመተከል፣ በወለጋ፣ በራያ፣ በከሚሴ፣ ወዘተ. በበርካታ ንጹን ዜጎች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ ተፈጽሟል፡፡ በተለይ በቤንሻንጉል ክልልና በወለጋ በዜጎች ላይ በተከታታይ የሚፈጸው የጅምላ ግድያ መሰረታዊ የሆነ የማያድግም መፍትሄ ባለማግኘቱ ዜጎችን ማለቂያ ለሌለው ሰቆቃ እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡ መንግስትም የችግሩ መሰረታዊ ምክንያት ለይቶ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ እንደ ተራ የነፍስ ግድያ ወንጀል ገዳዮችን ብቻ ማሳደዱ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ወለጋ ውስጥ ግድያ ሲፈጸም ኦነግ ሸኔን ብቸኛ ተጠያቂ ማድረግ እንዲሁም በመተከል ጭፍጨፋ የጉምዝ ሽፍቶችን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ምናልባትም ከሃገር ውስጥ እስከ ውጭ በተደራጀ ሁኔታ ለተለየ ፖለቲካዊ አላማ ሃገሪቱን በማሸበር ላይ ያሚገኙ ቡድኖች ላይ ትኩረት እንዳይደረግ የሚያዘናጋና አቅጣጫ የሚያስት እንዳይሆን ቆም ብሎ ማሰብ ይፈልጋል፡፡

መተከል ውስጥ ጉምዝ፣ ሺናሻ፣ አገው፣ አማራ፣ ኦሮሞ እና ሌሎች ብሔረሰቦች ለዘመናት አብረው ኖረዋል፡፡ አልፎ፤ አልፎ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ግጭት ቢኖርም እንዲህ ያለ ዘርን መሰረት ያደረገ ግድያ ሲፈጸም ታይቶ አይታወቅም፡፡ በወለጋም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ወለጋ ውስጥ የአካባቢው ተወላጅ የሆነው የኦሮሞ ማህበረሰብ በኑሮ ደረጃው አብረውት ከሚኖሩት የሌሎች ብሐረሰብ አባላት የተሻለ የኑሮ ደረጃ ያለው ነው፡፡ ብዙዎቹ የቡናና የእርሻ መሬት አላቸው፡፡ ቡናና የቅባት እህሎችን አምርተው ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የአካባቢው ተወላጆች ከሌሎች ብሔረሰቦች የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ምዕራብ ወለጋን በሚገባ ስለማውቀው የኦሮሞ ማህበረሰብ ያላቸውን ከሌሎች በአካባቢው ከሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተካፍለው ነው  የሚኖሩት፡፡ በሃይማኖት የታነጹ በመሆናቸውም ያለው ለሌለው በማካፈል እየተሳሰቡ የሚኖሩ ህዝቦች ዛሬ በድንገት ተነስቶ አንዱ ሌላውን በገጀራና በጦር መሳሪያ የሚጨፈጭፍበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም፡፡ ኦነግ ሸኔ የሚባሉትም ከሌላ ሃገር ወይም ከሌላ ፕላኔት የመጡ ሳይሆኑ በፖለቲካ ድርጅት የተመለመሉ እዚው ማህበረሰብ ውስጥ ተወልደው ያደጉ ወጣቶች ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆኑ ካደጉበት ማህበረሰብ የተለየ ባህሪ ሊኖራቸው ይችላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ የችግሩን ምንጭ እስካሁን ያልተሄደበትን መንገድ በመሄድ መፈለጉ መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል፡፡ አሁን እንደሚታየው የሃገሪቱ ትልቅ ጠንቅ የነበረው ህወሓት ከነሰንኮፉ ሲነቀል የምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካ የሚያምሱት የአውሮፓና የአረብ ሃገራት የኢትየጵያ መንግስት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር በከፍተኛ ደረጃ ሲንቀሳቀሱ እያየን ነው፡፡ ግብጽም ሱዳንን አይዞሽ ግፊ በማለት ጦሯን አሰማርታ በገዳሪፍ በኩል የአዲስ አበባን ያህል የቆዳ ስፋት ያለው ቦታ በወረራ እንድትይዝ አግዛታለች፡፡ በዚህ ጉዳይ እስካሁን ምዕራባውያን ሲያወግዙ   አልተሰሙም፡፡ እንዲያውም ኢትዮጵያ ሱዳንን ወረረች የሚል ሪፖርት በሚስጥር ለተባበሩት መንግስታት እንዲቀርብ መደረጉን ሰምተናል፡፡

የዚህን ያህል የውጭ ሃይሎች የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውን ለማስፈጸም በተለያየ መልኩ ተፅእኖ የሚያሳድሩባት ሃገር እርስ በርስ መጠራጠሩንና መወነጃጀሉን ትተን አንድነታችንን አጠናክረን መቆሙ ይበጀናል፡፡ አሁን የሚታየው በፖለቲካ እተፈራረጁ መካሰስና መወነጃጀል ለውጭ ጠላት ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጠር በስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ያለምንም ልዩነት ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች አቅርቦ ሊያወያይ ይገባል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለይ መንግስትን በጦርነት አንበርክኬ ስልጣን እይዛለሁ ወይም አንድን ብሔር በጉልበት ነጥዬ ሃገር እመሠርታለሁ የሚለው አስተሳሰብ ያለፈበት ይመስላል፡፡ እስከቻልኩ እገዛለሁ ካልሆነ በጉልበት ተገንጥዬ ሃገር እመሰርታለሁ ብሎ የተነሳው ህወሓት አስተሳሰቡ ዘመን ያለፈበት መሆኑን 17 ዓመት ታግሎ የያዘውን ስልጣን በ17 ቀን ጦርነት ተፈጽሞ ግብአተ መሬቱ ሲፈጸም ተመልክተናል፡፡  

   

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top