Connect with us

ከጥልቅ እንቅልፍ እና ከግልብ ሞት መልስ

ከጥልቅ እንቅልፍ እና ከግልብ ሞት መልስ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ከጥልቅ እንቅልፍ እና ከግልብ ሞት መልስ

ከጥልቅ እንቅልፍ እና ከግልብ ሞት መልስ

(በማስረሻ ማሞ)

በባሕርዬ ዳተኛ እና ገታራ ነኝ። ጨበጥኹት ብዬ ከማስበው “እውነት” ጋራ የሚጋጭ ምንም ዐይነት ሐሳብ ሲያጋጥመኝ በቀላሉ ለመቀበል እቸገራለኹ። በሌላ በኩል ደግሞ ያንኑ ጨበጥኹት ያልኹትን እውነት የምር ተፈታትኖ የሚያስጥል ሌላ ጠንካራ እውነት ሲያጋጥመኝ የቀደመውን የእውነት ምርኩዝ ሰቅዬ አዲሱን ምርኩዝ ለመጨበጥ ፈጽሞ የማላመነታ ነኝ። ይኸኛው ባሕርዬ ዳተኛ እና ገታራነቴን አያሳይም፤ አመቻማች እና ከኹኔታዎች ጋራ ራሱን የሚያሰናስል ማንነትን እንጂ። እንዲህ እንድኾን ያደረገው ማነው? እኔ ነኝ? ስሜቴ ነው? ፍላጎቴ ነው? እግዚአብሔር ነው? ወይስ ማነው? መልሱ እስካኹን ከእኔ ዘንድ የለም።

የእስከዛሬውም ዋነኛውና መሠረታዊው ችግሬ የተጠየቁ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ሊኖራቸው ይገባል የሚለው ድምዳሜ የተጫነው አመለካከቴ   ይመስለኛል። ይቺ ዓለም መልስ ዐልባ በኾኑ ዕልፍ ዐዕላፍ ጥያቄዎች የተሞላች እጅግ ውስብስብ ዓለም ናት። በዚህ መልስ ዐልባ ሐሳብ ላይ አተኩሬ እንድጽፍ ያደረገኝ ደግሞ የዓለማችን ቁጥር አንድ መልስ ዐልባው ኮሮና የተሰኝ ቫይረስ ነው።

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በዳተኛ እና ገታራ ባህርዬ ምክንያት የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ነገሩን አቃሎ የማየት ዝንባሌ ነበረኝ። “ኮሮና የለከፈው ሰው ብዛት ይኼን ያህል ደረሰ” ሲሉኝ “ይኼ ነገር ምነው ንግድ እየመሰለ መጣ፤ ልክ እንደ ስቶክ ኤክስቼንጅ አይነት ጫዎታ” እያልኹ አፌዛለኹ። “ካቢኔቱ ዛሬ በኮሮና ጉዳይ አንገት ላንገት ተናነቆ አረፈደ” ሲሉኝ ምነው ፖለቲከኞቹ ዓለም በአጀንዳ ድርቅ የተመታች አስመሰሉት? እያልኹ እዘባነናለኹ።

በማፌዝ እና በመዘባነን ላይ እያለኹ የተከበረው አቶ ኮሮና ቅዳሜ ዲሴምብር 12 ቀን በማላውቀው መንገድ ገብቶ ራሱን ከውስጤ ወለደ።  ወደ ሞት አፋፍ እስከደረሰበት እስከ ረቡዕ ዲሴምበር 23 ቀን ድረስ ባደረሰው እጅግ ከፍተኛ የኾነ ድብደባ ጨበጥኹት ያልኹትን እውነት በማስጣል ለ18 ዓመታት ያህል የሰቀልኹትን የመንፈሳዊነት ምርኩዝ ዳግም እንዳነሳ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶ በማለፍ ላይ ይገኛል።

ነገሩ የኾነው እንዲህ ነው። ኮሮና ቅዳሜ ዕለት ራሱን በውስጤ እንደወለደ ከማንጅራቴ ወደ ብራኳዬ ቁልቁል የሚወርዱት ቋንጃዎቼ ብቻቸውን ሃምሳ ኪሎ ያህል ከብደው አገኘኋቸው። በጠዋት ተነስቼ የተለመደ ቁርሴን ሠራኹ፤ ሁለት እንቁላል በሁለት ስላይስ ቺዝ ጋግሬ ከአራት ስላይስ ዳቦ ጋራ አዘጋጀሁ፤ ከጎን ከካሮት፣ ከኩከምበር፣ ከአቮካዶ፣ ከስትሮቨሪ እና ከስፒናዥ የተሠራ ስሙዚ አስቀምጥኹ፤ ይኼ የዘወትር ቁርሴ ነው። ለወትሮው ቁርሴን ለማጠናንቀቅ የሚፈጅብኝ 10 ደቂቃ ብቻ ነበር። ዛሬ ግን ታሪኩ ሌላ ኾኗል፤ 25 ደቂቃ ሙሉ ታግዬ ታግዬ መብላት የቻልኹት ¾ኛውን ብቻ ነበር።

ቀን ሙሉ ሃምሳ ኪሎ ቋንጃ ተሸክሜ ማታ ላይ ከአዲሱ ባለትዳር ወዳጄ ዳዊት ዘሚካዔል ቤት ወግ እያወጋን እራት እንብላ ተብሎ ተገናኘን። [በነገራችን ላይ ኮሮና በእኔ ውስጥ ስለመወለዱ እኔም ጭምር እውቀቱ አልነበረኝም] ሌላኛው የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው ተፈራ ነጋሽ (ፒኤችዲ) ዛላ የተባለች ቅመም ልጁን ይዞ ከእኛ በፊት ከእራቱ ላይ ታድሞ ነበር። ዮሐንስ የሚባል ሌላ ወዳጃችንም በስፍራው ተገኝቶ ነበር።

ራት ደርሶ መብላት ጀመርን። ኤልሳቤጥ የኔ ባለቤት፣ አስቱ የዴቭ ባለቤት በጋራ ተፈ ተፍ ብለው ነበር ያዘጋጁት። ክትፎ፣ አይብ፣ ጎመን፣ ጥብስ፣ አልጫ፣ ቀይ ወጥ እና ምሥር ወጥ። እጅ ያስቆርጥማል። ናፍቆት አጠገቤ ቁጭ ብሎ እጅ በሚያስቆረጥም አበላል ሲበላ የምኞትን ያህል ጉልበት ያፈረጠመው ኮሮና ጉሮሮዬ መሀል ቆሞ ወደ ውስጥ ባስገባኹ ቁጥር እሱ ወደ ውጪ እየገፋ ይታገለኛል። በዚህ ጣት በሚያስቆረጥም ምግብ ላይ ገፊ ጣት ወልጄ መብላት አቃተኝ። ግማሽ ያህሉን እንደምንም አስገብቼ ግማሹን እንዳማረኝ ተውኩት።

ወጋችንን በአግባቡ ስንጨረግድ አምሽተን ከምሽቱ አራት ሰዓት ሲኾን ወደየቤታችን ተመለስን።

እሁድ ጠዋት ስነሳ ኮሮና ከናፍቆት ጋራ ተስተካክሎ ጠበቀኝ። በምግብ ፍላጎቴ ላይ ታላቁ ባለስልጣን እሱ ኾኗል። “ጉንፋን ሊይዘኝ ፈልጓል መሰለኝ” የሚል መላ ምት ጠዋት ላይ ስመታ ቆየኹ። ረፋድ ላይ ብርድ ብርድ እንደማለት፣ እንደመቀረጣጠፍ ሲያደርገኝ እና ከሃምሳ ኪሎ ቋንጃ ወደ መቶ ኪሎ የብራኳ ሸክም ስሻገር “ኮሮና ሳላረግዝ አልቀረኹም” ብዬ መጠርጠር ጀመርኹ።

ከእነ ጥርጣሬዬ ሰኞ ኾነ፤ ብራኳዬ ሁለት መቶ ኪሎ ገብቷል፤ ወዲያው ስልክ አነሳኹ እና ወደ ማዕከላዊ የኮሮና መመርመርያ ጣቢያ ስልክ መታኹ።

“እኔ እና ቤቶቼ መመርመር እንፈለጋለን”

“ዝርዝር ስሜት ይነግሩኝ”

“አዎ፣ መገጣጠሚያ ይቀረጣጠፋል። ብራኳ 200 ኪሎ ግራም ይመዝናል፣ የምግብ ፍላጎት በአፍጢሙ ተድፍቷል።”

“በቃ በቃ ዛሬውኑ ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ላይ መጥታችኹ ምርመራችኹን ማድረግ ትችላላችኹ።”

“እሺ ወይዘሮ፣ በጣም አመሰግናለኹ”

“መንም አይደል አቶ። እስከዚያ መልካሙን ሁሉ እመኝልኻለኹ።”

“አመሰግናለኹ።”

ዘጠኝ ሰዓት ላይ አራታችንም ሄደ ተሰለፍን።

በመጀመርያ ኤልሲን አስቀደምናት። ጉሮሮዋን ሲቧጥጧት እና ሰርኗን ሲጓጉጧት ዛር እንደያዛት ሴት አንዘፈዘፋት።

“ምን ኾነሽ ነው ውዴ እንዲያ የኾንሺው?” ስላት

“እንዴ አእምሮዬ ውስጥ ግብቶ የኾነ ነገሬን ሲያስተካክል እንዴት ልኹን?”

ከዚያ ምኞት እኔ ካልገባኹ ሲል አይኾንም እኔ ልቅደም አልኹ። እሷ የኾነችውን ዐይቶ ናፍቆት ፈራ ተባ ማለቱን ሳይ ነገሩን ከወዲሁ ማስተካከል ተገቢ ነው ብዬም በማሰብም ጭምር ነው ራሴን ማስቀደሙን የመረጥኹት።

ጉሮሮዬን ቧጠጠ፤ እኔ ያልተመቸኝን ምግብ ለማስወጣት ከሱ በላይ ሞሳ ተጫውቼበት ስለማውቅ ምንም አልመሰለኝ። ሰርኔ ውስጥ ለመግባት አገጬን ከፍ አደረገ፤ ከአሁን አሁን የኾነ ስሜት ያሳያል ብሎ ይጠብቀኛል፤ እኔ እያንዳንዷ ስሜት ምን ትመስላለች የሚለው ላይ አተኩሪያለኹ። እኔ አተኩሬ ሳልጨርስ ሰውየው ገብቶ ወጥቷል።

ናፍቆት ከወንበሩ በተነሳኹበት ቅጽበት ተቀምጦ አገኘኹት። ያው እኔን ሊደግም መኾኑ ነው፤ እያየኹት ደገመኝ።

ውጤት በ48 ሰዓት ተባብለን ተሰነባበትን።

ማክሰኞ ጠዋት ብራኳ 400 ግራም ገባ። ላንዴም “ጁንታው” ከተደበቀበት አምልጦ የእኔን ጀርባ ሲቀጠቅጥ ያደረም መሰለኝ፤ ላንዴም የቄራዎች ድርጅት በበሬ እጦት ምክንያት የሚያንጠለጥሉት ቢያጡ መንጠቆው ባዶ ከሚያድር ያንተን ብራኳ እናንጠልጥል ብለው በመንጠቆ ላይ ሰቅለው ያሳደሩኝ መሰለኝ። ላንዴም ድሮ በልጅነቴ የማስታውሳቸው በየሰፈሩ እየዞሮ ዛፍ ይቆርጡ የነበሩ ሰዎች የሚቆርጡት ቢያጡ አዳራቸውን ሙሉ እኔን መጥተው ሲተፈትፉኝ ያደሩ መሰለኝ። በዚህ ሁሉ መሀል አገር ሙሉ እንቅልፍ ተኝቼ አድሬ፤ እንደገና የእንቅልፍ ጉድጓድ ውስጥ መውደቅ ያምረኛል።

ከዚሁ ስሜት ጋራ አቀብ ቁልቁል ሰወጣ ስወርድ ስልኬ ጮኸ።

ባለ 48 ሰዓቶቹ ናቸው። ስማቸውን ቀይረው 12 ሰዓት ኾነው ደወሉ። እኔን የለብህም ካሉኝ ነው ዜና የሚኾነው። እኔን በሚመለከት ዜና የላቸውም። “ከፖዘቲቭ ልጅምር አለ” ሚስተር 12።

እሺ

“ናፍቆት ኒጌቲቭ ነው።”

በጣም ጥሩ። [ መልካም ዜና ብሎ ኒጌቲቭ ግን አይገርምም?]

“ምኞት፣ ኤሳቤጥና ማስረሻ ፖዘቲቭ ናቸው።”

ምንድን ነው ማድረግ ያለብን? [መርዶ እያረዱ ፖዘቲቭ እንዴት ያለ ነገር ነው?]

“ራሳችኹን ለሚቀጥሉት 7 ቀናት ኩዋራንቲን ማድረግ።”

ሌላኛው ዝርዝር የጊዜ ኪሳችኹን ስለሚጨረግድባችኹ ወደዚያ አልሄድም።

ረቡዕ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ ኮሮና ከእኔ ገዝፎ እኔ ከሱ አንሼ ተገናኘን። ውስጤ ያለውን ኢነርጂ ሙሉ ለሙሉ ወስዶ እንደ እንጨት የደረቀ ማስረሻ አስታቅፎኛል። ከአልጋ ላይ ለመነሳት ስሞክር ገና ያልኖርኩትን መቶ ዓመት ሰርቆ የመቶ አርባ ስምንት ዓመት የተንቆሻቆሸ ምንጅላት አድርጎኛል።

የምንጅላት እግሮቼን እየጎተትኹ ወደ ሽንት ቤት ሄድኹ። በራሴ ላይ አንዳችም የእኔ የምለው ነገር የለኝም፤ በኮሮና ቁጥጥር ስር ወድቄያለኹ። ሽንቴን ሸንቼ ስነሳ ወደ መታጠቢያው ተጠጋሁ፤ ራሴን በመስታወት ውስጥ ተመለከትኹት ወትሮንም የማውቀው አካላዊው ማስረሻ ብዙ የተለወጠ ነገር የለውም። ከፍተኛ የኾነ ውግያ የተደረገበትና ድብደባ ተፈጽሞቦት ኀይልና ሥልጣኑን የተነጠቀው ውስጠኛው ማስረሻ ነበር። ከቀናት በፊት ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 40 ከሚኾን ወጣቶች ጋራ እኩል የኩሊነት ሥራውን ያራውጥ የነበረው ማስረሻ አሁን የለም። በቀናት ውስጥ የመቶ አርባ ስምንት ዓመት ምንጅላት ኾኗል።

ምንጅላት ማስረሻ እጁን ታጥቦ ጥርሱን ቦርሾ፣ በቀጥታ ወደ መኝታው ተመለሰ። ምንጅላት እግሮቹ ከዚያ በላይ አቅም አልነበራቸውም።

ምንጅላት ጭንቅላቴ ትራሱን ሲነካ በሞት እና በእንቅልፍ መካከል ያለ ቀርከሃ ላይ የወደቅኹ መሰለኝ። ተኝቼ ተኝቼ ተኝቼ ተኝቼ ተኝቼ ስንቃ ‘ኢየሱስ ከምን ጊዜው መጥቶ ትንሳዔ ሙታን ኾነ?” ከሚል ስሜት ጋራ አብሬ እባንናለኹ። ከእንቅልፍ የባነንኹ ሳይኾን ከሞት አምልጬ የመጣኹ ይመስል። እንቅልፍ እና ሞት ልዩነታቸው ጠፍቶብኛል።

አሁን ብራኳዬ 3000 ኪሎ ገብቷል። አዲሱ ዜና እሱ አይደለም። አዲሱ ዜና በብራኳ እና በብራኳዬ መሀል በምትገኝ አንዲት ኅብለ ሰረሰር ላይ ያለች ስሜት ናት ዜናዋ። ቀጭን ረዥም ሰውዬ፤ ቁመቱ ሁለተኛውን ሰማይ ነክቶ እንደገና ታጥፎ የሚመለስ፣ ክንዱ የምድርን ወገብ ግማሽ የኾነ፤ በቀኝ እጁ ኮልት ሽጉጥ የምታህል መቦርቦርያ ይዞ መሀል ኀብለ ሰረሰሬን ይሰረስረኛል። ይኼ ሁሉ የሚኾነው ኮሮና ኀይሌንም፣ ሥልጣኔንም ጉልበቴንም ነጥቆ ባዶ ቁርበቴን ስላስታቀፈኝ ነው።

በቁርበቴ ከዚህ በላይ ማሰላሰል ስለማልችል እንደገና ከጥልቅ እንቅልፍ እና ከግልብ ሞት በተሸመነ ስጋጃ ላይ እወድቃለኹ። ጥልቅ እንቅልፍ እተኛለኹ፣ ግልብ ሞት እሞታለሁ። ጥልቅ እንቅልፍ እተኛለኹ፤ ግልብ ሞት እሞታለኹ።

ሐሙስም ኾነ፣ ጥልቅ እንቅልፍ ተኛኹ፤ ግልብ ሞት ሞትኹ። አርብም ኾነ ጥልቅ እንቅልፍ ተኛኹ፤ ግልብ ሞት ሞትኹ።

እነኾ ቅዳሜ ኾነ፤ የጥልቅ እንቅልፍ እና የግልብ ሞት የዕድሜ ዘመናቸው አለቀ። ኮሮናም ብራኳ እና ኀብለ ሰረሰሬን ለቆ ወደ መጨረሻው የውጊያ ሜዳ ተሻገረ። እኔን ምንጅላት ጉድጓድ ውስጥ ቀብሮ እርሱ ጭንቅላቴ ላይ ሰፈረ። ብቸኛው እና አለኝ በምለው መመኪያ ላይ መጣ። ሴንትራል ነርቨስ ሲስተሜን ያለ ማቋረጥ በጥይት አረር፣ በመትረየስ፣ በታንክ፣ በሮኬት፣ እና በሚሳዔል ጭምር ይደበድብ ጀመር። በድብደባው ብዛት ዐይኖቼ እኔኑ መልሰው ይወጉኝ ጀመር። ጆሮዬ የዳግማዊ ምንሊክን ጦር ተውሶ እኔኑ መልሶ እየወጋ ያሰቃየኝ ጀመረ።

ኮሮና ሽምቅ ተዋጊ ነው። መደበኛ የሚባል የውጊያ ስልት ፈጽሞ አይመቸውም። ፊት ለፊት አይገጥምህም፤ ልክ እንደ ሕወሓት። መጀመርያ እያሳሳቀ በጀርባህ በኩል አሸምቆ ብራኳህን ይወጋኻል። ከዚያ ስፓይንህን ሰርስሮ ለደም ዝውውር ከፍተኛ የኾነ አስተዋጽኦ የሚጫወተው ሳንባህ ላይ በ3000 ኪሎ ጫማው ይቆምብኻል። ከዚያ አፍንጫህን ድል ይነሳል። ምላስህን ከጥቅም ውጪ ያድርጋል። ከዚያ ዐይንህን፣ ከዚያ ጆሮህን፣ ከዚያ የሁለንተናህ ሞተር የኾነውን ጭነቅላትህን በመደብደብ በቻለው ሁሉ መጠን ሲሞት አብሮህ መሞትን ይመርጣል።

ስለኾነ ሽብርተኛ እንጂ ስለኾነ ቫይረስ የማወራ አይመስልም አይደል? ለዚያ ነው አንዳንድ ሰዎች ኮሮናን የባዮቴሪሪዝም የመጀመርያው ፊሽካ አድርገው የሚወስዱት።

ለራሴ ኅሊና ብቻ በመታዘዝ፣ በራሴ የአእምሮ ሚዛን፣ በምክንያታዊነት እና በአምክንዮ ብቻ በመመራት፤ የእግዜር ጣልቃ ገብነትን ወደ ጎን በማድረግ ሕይወቴን መምራት አለብኝ የሚል ውሳኔ ከወሰንኹ እነኾ አስራ ስምንት ዓመታት ተቆጠሩ።

እናም የምንጅላት ቆዳዬ ብቻውን ሲቀር የገፋኹትን የእግዜርን ጣልቃ ገብነት ጠራኹት። ጣልቃ ገቡ እግዜር ኾይ ከወዴት አለህ? አልኹት? እርሱ ይስማኝ አይስማኝ አላውቅም። እኔ ግን እንደሚሰማኝ አድርጌ ማውራት ጀመርኹ። እገምታለኹ ከፍጥረታ ጅማሬ ጀምሮ አንተ ድንቅ መኾንሀን፤ እገምታለኹ መጀመርያ የሚባል ሐሳብ ሳይኖርም በፊት ልትኖር እንደምትችል፤ መኖርህ ያተርፍ እንደኾነ እንጂ አንዳችም ኪሳራ የለውም ብዬም መገመት እችላለኹ። እናም እላለኹ አንተ ሁሌም ትክክል ነህ! ስህተቱ ሁሉ ያለው ከእኛ ዘንድ ነው። ንጽሁ እና ቅዱስ አድርገህ የሠራኸውን ይኼን ዓለም በእያንዳንዷ የጊዜ መስፈርያ የቫይረሶች መጫዎቻ ያደረግነው እኛ ነን። ትልቁ እና የመጀመርያው ቫይረስም “ኑ እንውረድ ሰውን በመልክ እና በምሳሌያችን እንፍጠር” አለ እግዜር ተብሎ የተጻፈው ይመስለኛል። ይህ አባባል ሰፊውን እና ትልቁን እግዜር ግለኛው የሰው ልጅ በራሱ መልክ እና ምሳሌ ለማጠበብ መማሰኑን ያሳያል እንጂ የአንተን የትልቁን እግዜርን እውነተኛ ማንነት የሚገልጥ አይመስለኝም።

እናም ጣልቃ መግባት ካለብህ አሁን ጣልቃ ትገባ ዘንድ ልመናዬን ወደፊትህ እዘረጋለኹ። በዚህ ምድር ላይ ምንም ክፉ የሚባል ፍጥረትን አልሠራህም። ከሰው ልጅ በስተቀር።

እናም እግዜር ኾይ ደግሜም አለምንኻልለኹ። ኮራፕት ያደረጉ ልቦችን፣ በቫይረስ የተመረዙ ነፍሶችን ጎብኝ።

ክብርና ሞገስ ሁሉ ላንተ ብቻ ከዘለዓለም እሰከ ዘለዓለም ይኹን፤ በሰው ልጅ ቁንጽል ምናብ ሊገለጥ ለማይችለው ማንነትህም እንዲሁ ክብርና ምስጋና!

አሜን

!

ከኮሮን ቫይረስ ጥቃት ቁርበት ነፍሱ የተረፈችለት ፍጥረትህ።

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top