Connect with us

በመተከል ለሠላማዊ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥሪ ቀረበ

በመተከል ለሠላማዊ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥሪ ቀረበ
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሙኒኬሽን

ዜና

በመተከል ለሠላማዊ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥሪ ቀረበ

በመተከል ለሠላማዊ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥሪ ቀረበ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የጁንታውን የጥፋት ተልዕኮ በውል ሳይረዱ ወደ ጫካ የገቡ ሠላማዊ የህብረተሰብ ክፍሎች ከጥፋት ኃይሉ ራሳቸውን ለይተው ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ጥሪ አቀረቡ፡፡

ባለፉት ወራት በመተከል ዞን በተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በደረሰው የንጹኃን ዜጎት ሞት፣ መፈናቀል፣ የሰውና የንብረት ጉዳት በእጅጉ ማዘናቸውን ርዕሰ-መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ ውይይት በማድረግ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀዋል፡፡ 

በመተከል ዞን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የጁንታውን የጥፋት ተልዕኮ በውል ባለመረዳት ወደ ጫካ የገቡ ሠላማዊ ዜጎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ እነዚህ ሠላማዊ ዜጎች ከጥፋት ኃይሉ ተጽዕኖ ራሳቸውን ለይተው ወደቀያቸው በመመለስ ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

“የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን በዞኑ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል” ያሉት አቶ አሻድሊ፣ ሠላማዊ ዜጎች በሚወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ እንዳይጎዱ ራሳቸውን ከጥፋት ቡድኑ ለይተው ሊመለሱ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የክልሉን ሠላም በማይፈልጉ ኃይሎች በአሶሳና በካመሺ ዞኖች የተከሰቱት ችግሮች በአጭር ጊዜ አልባት አግኝተው እንደነበር የጠቀሱት አቶ አሻድሊ፣ በመተከል ዞን ከ2011 ጀምሮ የሚስተዋለውን ግጭት ለማስቆም አመራሩና የጸጥታ አካላት ያደረጉት ጥረት ጊዜ መውሰዱን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ለተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተለያዩ አካላት ተሳትፎ እያደረጉ ስለመሆኑ ጠቁመው፣ በተለይም ሕወሓት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመጠቀም ወጣቶችን ለጥፋት ተልዕኮ ሲጠቀም መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ከፌዴራል መንግስት ጋር በተሠራው የተቀናጀ ሥራ በርካታ በርካታ የጸረ-ሠላም ኃይሎችን መደምሰስ፣ መማረክ እና ከነ ጦር መሳሪያቸው በቁጥጥር ስር መዋል መቻሉን ገልጸው፣ በቀጣይም ተጠናክሮ ለሚቀጥለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከህግ ማስከበር ዘመቻው ጎን ለጎን በክልሉ አመራሮች የተጀመሩት የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

የጁንታውን ተልዕኮ ተቀብሎ ለጥፋት ወደ ጫካ የገባው ኃይል፣ መንግስት ችግሮችን በመነጋገር ለመፍታት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን በመረዳት ሠላማዊ አማራጮችን እንዲጠቀም የጠየቁት ርዕሰ-መስተዳድሩ፣ ነገር ግን ካሁን በኋላ ጥቃት እየፈጸምን እንቀጥላለን የሚል አካሄድ መቋጫው ህግ ማስከበር ነው ብለዋል፡፡  

በዞኑ የተከሰተው ችግር የሰውን ሕይወትና ንብረት ውድመት ባሻገር፣ በመንግስት ወረዳን ከወረዳ፣ ክልሉን ከአጎራባች ክልል ለማገናኘት የተያዙ የመንገድ መሠረተ-ልማቶች እንዳይከናወኑ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉ ሕዝቦች የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ይዞት ከመጣው ዕድል ለመጠቀም ለሠላማቸው ቅድሚያ ሠጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የአማራ ክልሎች፣ የሁለቱን ክልል ሕዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸውን በመግለጽ፣ አሁን በመተከል ዞን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የጋራ በመሆኑ፣ ችግሩን  ለመፍታት በውይይት ላይ ተመስርተው በጋራ እንደሚሠሩም አቶ አሻድሊ ተናግረዋል፡፡ 

ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሠላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ከአማራ ክልል  የተውጣጣ የእርቀ-ሠላም ኮሚቴ እንደሚቋቋም አመልክተዋል፡፡

በመተከል ዞን የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማስቆም መንግስት ለሚወስደው እርምጃ  ህብረተሰቡ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም አቶ አሻድሊ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

#የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሙኒኬሽን

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top