“በራያ አዲስ ዓመት በዚህ ወር የገባ ይመስላል”
በእናት ሀገር ባዳ፣ በባድማ እንግዳ፣ አትንኩኝ ባሉ ፍዳ ተጭኖባቸው ቆይተዋል። ለዓመታት የናፈቁት በከፋ ዘመን ውስጥ ሆነው የታገሉለት የማይናወጥ ማንነት ዋጋ ከፍለውበታል።
ኢትዮጵያዊነት ሚስጥር፣ የማይሻር ማንነት፣ የማይናወጥ ሰውነት፣ የማይቀደም ቀደምትነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ከዓለት የጠነከረ፣ በፈተና ውስጥ እያበራ የኖረ፣ የመከራን ድልድዮች ሁሉ በፅናት የተሻገረ፣ ጠፋ ሲሉት የሚያበራ፣ ደከመ ሲሉት የሚጠነክር፣ ተለያየ ሲሉት የሚያብር ነው።
ኢትዮጵያዊነት በሴራ ብዛት፣ በጥይት ጩኸት፣ በተሳሳተ የታሪክ ስብከት የማይሸጥ የማልወጥና የማይናወጥ ሚስጥር ነው። ኢትዮጵያዊያን ሚስጥሩን ይኖሩታል፣ በጋራ ገጥመው ያሸንፉበታል። በጋራ አጊጠው ይደሰቱበታል። ኢትዮጵያዊነት የድል ሁሉ መነሻ፣ የስኬት ሁሉ መድረሻ ነው።
ለማንነት ሲባል ዋጋ ተከፍሎበታል። እናቶች ልጆቻቸውን ገብረዋል። ወጣቶች በተገኙበት ተገድለዋል። በእጅ በሚያዝ በሚመስል ጨለማ ውስጥ ያለ ፍርድ ታስረዋል። ገሚሶች ምሬት አሳርሯቸው ብን ብለው ጠፍተዋል። የሚዋደዱ ቤተሰቦች ተበታትነዋል። ጭቆናና ግፍን ሽሽት ከሚወዷት ቀያቸው ወጥተው የተሰደዱት፣ ይጠጡት ወራጅ ውሃ፣ አንጀታቸውን ያርሱበት ደረቅ እንጀራ፣ ይጠለሉበት ቤት አጥተው በዱር በገደሉ በበረሃ ተበልተው፣ በባሕሩ ሰጥመው አልቀዋል። ለዚህ ሁሉ በደላቸው ማንነታችን አንትንኩ፣ ርዕስታችን አትንጠቁ ባሉ ነው።
የራያ እናት እንባዋን እያንቆረቆረች፣ ፈጣሪዋን እየተማፀነች በጨለማ ውስጥ አልፋለች። ወንድ ልጅ ስትወልድ ደረሰልኝ ሳይሆን መች ደርሶ ይገድሉብኝ እያለች ተሳቃለች። ዘላለማዊ የሆነ ምድራዊ ዙፋን በሌለበት፣ ማንም ከኛ በላይ የለም ያሉት በማይሰነብቱበት፣ በወርቅ የተዋቡት በብር ያጌጡት የወርቅ ጫማ የተጫሙት ሁሉ በተለካች አጭር ጊዜ በሚያልፉባት አድካሚ ዓለም ውስጥ ገናናነት የማይወድቅ፣ የግፍ እንባ ጠራርጎ የማይወስድ የመሰላቸው የትህነግ ሰዎች አማራን እርስቱንና ማንነቱን ነጥቀው ኢትዮጵያዊነቱን ሲፈታተኑት ኖረዋል።
አያልፍም ያሉት ዓለም ሊያልፍ፣ አይጠወልግም ያሉት ክብር ሊረግፍ፣ የኢትዮጵያዊያን የጨለማ ዘመን ሊገፈፍ፣ በዳይ ሁሉ ወደ ፍርድ አደባባይ ለፍርድ ሊሰለፍ፣ ጊዜው ሲደርስ ትህነግ ኢትዮጵያዊያን በዝምታ የማያዩትን ነካች።
“ፈጣሪ ካለ በዙፋኑ ይፈርዳል አይፈርድም አትበሉ” ነውና ፍርዱ ደረሰ። የኢትዮጵያውያን መከለካያ ሠራዊት ትህነግ ስትተነኩስ የጫረችው እሳት ሁሉ በላት፣ በግፍ ያፈሰሰችው የዕንባ ማዕበል ሁሉ ወሰዳት፣ ያረከሰችው ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ አወረዳት።
የራያ እናት እንባ ታበሰ። የለመነችው ደረሰ። የተወሰደባት ተመለሰ። ልጅ ያጣው የእናትነት አንጀት ቢያስራትም ባገኜችው ድል ግን ደስተኛ ናት። ትልቁን ሰጥታ ትልቁን ተቀብላለችና።
የራያ ምድር አዲስ ዓመቷን እያከበረች ትመስላለች። በዚያች ምድር ጀንበር ያለ ደመና የወጣች መስላለች። ይወስዳል መንገድ ይመልሳል መንገድ እንዲሉ እግሬ ዘወርዋራው ራያ ወስዶኛል። ቆቦን አልፌ ወጃና ጥሙጋ ደረስኩ። ወጃና ጥሙጋ የትህነግ የግፍ በትር ያረፈባቸው አካባቢዎች ነበሩ። አሁን ግን መልካም ጊዜ ከጀግና ሠራዊት ጋር ሆኖ የግፉን ቀንበር አላቅቆታል። የእንኳን አደረሳችሁና የእንኳን ደስ ያላችሁ ላይ ናት። በዋጃ ጥሙጋ ጎረቤት ከጎረቤት እየተሳሳመ መልካም ምኞት መገላለፁ ገና አላለቀም። በሁኔታው ተገርሜ የነበረኝን ሥራ ጨርሼ ወደፊት አለፍኩ።
ለምለሙን የራያን ምድር ተመልክቼ፣ በፍቅራቸው፣ በንግግር ለዛቸው፣ በፅኑ ኢትዮጵያዊነታቸውና በእንግዳ ተቀባይነታቸው ተደምሜ ግራካሱን ራስጌ አድርጋ ወደሰፈረችው ከተማ አቀናሁ። በዚያች ከተማ ትህነግ ከውሸትም ከሥርዓትም ተነቅሏል። እርዕስት እንኳን ድሮም አልነበረውም።
የግራ ካሱን ዳገት ባሻገር እየተመለከትኩ ወደ አላማጣ ከተማ ተጓዝኩ። አላማጣ የግራ ካሱን ዳገት እባክህን አስጠልለኝ እና ካጠገብህ ልኑር ያለች ትመስላለች። ከእግሩ ስር ተወሽቃ፣ በግርማ ሞገሱ ደምቃ ነው የምትኖረው። ግራ ካሱ አላማጣን ይታዘባታል። ከላይዋ ሆኖ ከጨፍ ጫፍ ይመለከታታል። ብቻ ግን ደስ ይላሉ። በከተመዋ መሀል ለመሀል የተሰራው አስፓልት በእኩለ ቀን ሲያዩት ከግራ ካሱ ዳገት ፈልቆ በከተማዋ የሚያልፍ ወንዝ ይመስላል። ለዓመታት የትህንግ ውሸት፣ ለሳምንታት የከባድ መሳሪያ ጩኸት የጠናባት አላማጣ ከተማ ደርሻለሁ።
ከሳምንታት በፊት ጦርነት ወደነበረበት ዳገት ሥር ወደምትገኝ ከተማ መሄድ ጥርጣሬ ውስጥ ይከታል። የህዝቡ አኗኗር፣ እንቅስቃሴው ምን ሊመስል ይችል ይሆን የሚለውን ማሰብ ያጓጓል። መድረስ አይቀርም። ተደረሰና ከተማዋን መቃኜት ጀመርኩ። የከተማዋ ነዋሪዎች ሁሉንም ነገር የረሱት ይመስላሉ። ስጋት አይታይባቸውም። ከስጋት ይልቅ እፎይታ፣ ከትካዜ ይልቅ ደስታ ይነበብባቸዋል። እኔም የነበረኝ ስጋት ብን ብሎ ሲጠፋ ታወቀኝ።
ያላቸው ደስታ ነፃነትና ኩራት በምን አይነት ዘመን ውስጥ እንዳለፉ ምስክር ነው። በዚች ከተማ በዚህ ወር አዲስ ዓመት የገባ ይመስላል። ዓመት መቆጠር፣ እድሜ መደርደር፣ ወረሃ ነሃሴን አሳልፎ መስከረም መግባት ለካ አዲስ ዓመት አይደለም። ጳጉሜን እየመጣች መሄድ። አንድ ዓመት አልፎ ሌላኛው ሲተካ ለካስ ከንቱ ነው። አዲስ ዓመት አዲስ የሚሆነው ነፃነትና ደስታ ሲኖር ነው ለካ። በጨለማ ኖሮ አዲስ ዓመት ዋጋ ቢስ ነው ። የወራት መለዋወጥ፣ የዘመን መሮጥ፣ ምድር በአበባ ብታጌጥ፣ የመስቀል ወፍ ቢዘምሩ፣ ፏፏቴዎች ባዘቶ ቢመስሉ ውበት የላቸውም ያለ ነፃነት።
በራያ ሰላሳ መስከረሞች አልፈዋል፣ አበቦች አብበዋል፣ ፏፏቴዎች ባዘቶ መስለዋል። ዘመን ቆጠሩ እንጂ ደስታ አልነበራቸውም። ደስታቸው በዘመነኞች ተወስዳ የምትመለስበትን ቀን ትጠብቅ ነበርና ። ከዓመታት በፊት የተቋረጠው የራያዎች አዲስ ዓመት ከዓመታት በኋላ ተመልሷል።
አደይ አበባ ባይኖርም፣ ፏፏቴዎች ባዘቶ ባይመስሉም፣ የመስቀል ወፍ ዝማሬ ባይሰማም፣ የመስቀል ደመራ ባይለኮስም በራያ ግን አዲስ ዓመት አለ። በዘመነኞች የተነጠቀችው ደስታ ዘመን ጠብቃ ወደባለቤቶቿ ተመልሳለችና። ራያ የወሎ እርስት፣ የአማራ ግዛት፣ የትግራይ ጎረቤት፣ የኢትዮጵያ መሬት ነው። ለዓመታት የተደበቀው እውነት ይህ ነበር። አሁን እውነቱ ተገልጧል። ትህነግ ፈርጥጧል ራያ በደስታ ተውጧል።
በአላማጣ ጎዳናዎች እየተንቀሳቀስኩ ነዋሪዎቹን ታዘብኳቸው። ወጃና ጥሙጋ እንዳለው ሁሉ የጎረቤት መሳሳሙ አላለቀም። ነዋሪዎቹ በጎዳናዎች ሲገናኙ “እንኳን ለዚህ ቀን አደረሰህ፣ እንኳን ደስ ያለህ፣ እንኳን ለዚህ ቀን አበቃን፣ ድካማችን ዋጋ አግኝቷል” ይባባላሉ። በዚህ ጊዜ እንኳን አደረሰህ የሚባልበት ምን ጉዳይ ይኖር ይሆን ስል? ጠየኩ። አረጋግጬ ልርካ ብዬ እንጂ የደስታቸው ምንጭስ ግልፅ ነበር። << የእኛ ደስታችን ዛሬ ነው። ይህ ጊዜ አዲስ ዓመት፣ ዳግም ልደት ነው። የከፋው ዘመን አልፎ አዲስ ዘመን ስላዬን የደስታችን ልውውጥ ለዚያ ነው አሉኝ።>>
የራያዎች ስቃይና ጭቆና የሚገባው ራያ ሆኖ ለተገረፈው፣ ለተሰደደው፣ ለታሰረውና ለተሰቃዬው ነው። የራያዎች ደስታ በአንድ ጀንበር የተገኘ አይደለም። ዓመታትን ያስቆጠረ እንጂ። በራያ ሰማይ የእውነት ፀሐይ ለመውጣት ሰላሳ የውሸት ዓመታት ጋርደዋት ቆይተዋል።
የራያዋ ፀሐይ ከመከራ በኋላ የተገኘች በመሆኗ ከወትሮው ትለያለች። ራያን ወደ ቀደመው ማንነቱ ለመመለስ የተደረገው ትግል ቀርቦ ላለዬው ቀላል ሊመስለው ይችላል። የራያን ደስታ ለመመለስ ደም ተከፍሏል። የትህነግ ቅሌት፣ እብሪትና ክፋት በዚያች ከተማ ላይመለሱ ኮብልለዋል። አሁን ፍቅርና ደስታ ከተማዋን ተቆጣጥረዋታል። የመከራው ዘመን አልፏል። የማይመስላቸው ካባ ተገፏል። ጀንበር ወጥታለች፣ ራያ ጫፍ እስከ ጫፍ ከዓመታት በኋላ እውነተኛውን አዲስ ዓመት እያከበረች ነው።
ከታፈነ ፈንጅ የታፈነ ነፃነት ያሰጋል። የታፈነን ፈንጅ ማምከን ሊቻል ይችላል። የታፈነን ነፃነት ግን ማምከን አይቻልም። ጊዜ ጠብቆ ሲፈነዳ እንዳልነበር ያደርጋል።
(በታርቆ ክንዴ ~ አብመድ)