Connect with us

‹‹ባሕረ ጥምቀቱን ታቦቱን አንግሳ ኑ ትላለች  ጎንደር በእጅጉ ደግሳ››

‹‹ባሕረ ጥምቀቱን ታቦቱን አንግሳ ኑ ትላለች ጎንደር በእጅጉ ደግሳ››
አብመድ

ጥበብና ባህል

‹‹ባሕረ ጥምቀቱን ታቦቱን አንግሳ ኑ ትላለች  ጎንደር በእጅጉ ደግሳ››

‹‹ባሕረ ጥምቀቱን ታቦቱን አንግሳ ኑ ትላለች  ጎንደር በእጅጉ ደግሳ››

የእምነት፣ የሃይማኖት፣ ኩሩ፣  ጀግና ሕዝብ  እና የጥበብ መገኜዋ ጎንደር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የምትነሳበት ታሪክ ከፍ ያለ ነው፡፡ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሙሽሪት ጎንደር ጎብኚዎች ለማየት ይመኟታል፡፡ አይተው ይወዷታል፤ በናፍቆት ያስቧታል፡፡

የአርባራቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ የፋሲል አብያተ መንግሥታት፣ የጃን ተከል ዋርካና ሌሎችም ታላላቅ ቅርሶችና የታሪክ አሻራዎች የሚገኙባት ጎንደር ዘመንን አድምቃ፣ ነገን ብሩህ ለማድረግ የምትተጋ ከተማ ናት፡፡

ጎንደር ጠቢባን ተጠበውባታል፣ ጀግኖች ታሪክ ሰርተውባታል፣ ሊቃውንት ፈልቀውባታል፣ ነገሥታት አጊጠውባታል፣ ኢትዮጵያዊያን በፍቅር ኖረውባታል፡፡  የፍቅር ከተማ ናትና በፍቅር ያስቧታል፡፡

‹‹እምነት እንደ ዢረት የፈሰሰብሽ፣ ዲያቆን ቀሳቀውስቱ የተቀኙልሽ፣ ጎበዝና ጀግና ደጎች ያሉብሽ፣ የነገሥታት ሀገር ጎንደር እንዴት ነሽ ?››  እንዳለ ከያኙ ጎንደር ባለብዙ ታሪክ፣ ባለብዙ ሀብት፣ ባለ ብዙ ቅርስ ባለቤት ናት፡፡

 ወረሃ ጥር ሲዳረስ፣ ታቦቱ ሲነግስ፣ ጥምቀተ ባሕሩ ሲቀደስ ኢትዮጵን ማዬት ይናፍቃል፡፡ ጥምቀት ሲነሳ ጎንደር ከተማ ትታወሳለች፡፡ የጥምቀት በዓል በመላው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቢከበርም በጎንደር ግን ይበልጥ ይናፈቃል፣ ከፍ ብሎም ይደምቃል፡፡

ዘውድ ናት ድሮም ዘወድ ናት  ዛሬም ከጥንት

ክብሯን ጠብቃ የምትኖር  በሃይማኖት

ልገስግስ ልጓዝ በማለዳ

ለጎንደር ልሁን የእርሷ እንግዳ፡፡

አርባ አራቱን ደብር በጉያዋ ይዛ

በሰፊው አዳራሽ ቄጤማ ጎዝጉዛ

ባሕረ ጥምቀቱን ታቦቱን አንግሳ

ኑ ትላለች ጎንደር በእጅጉ ደግሳ፤

ብሏል ከያኙ ጎንደርን ሲገልጻት፡፡

ወርሃ ጥር ሲደርስ የጥምቀት በዓል  ሲቃረብ በጎንደር የኪነጥበብ ሳምንት ማክበር እየተለመደ መጥቷል፡፡ የባሕልና ኪነጥበብ ሳምነቱ የጎንደር ባሕል፣ ወግ፣ እሴት፣ ታሪክና ጥበብ የሚያሳይ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ ነው፡፡ የኪነጥበብ ሳምንቱ ዘንድሮም በተለያዩ ክዋኔዎች ሊከበር ጎንደር ዝግጅት ላይ ናት፡፡

የባሕልና ኪነጥበብ ሳምንቱ ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ እንደሚከበር የጎንደር ባሕል ማዕከል ሥራ አስኪያጅ ገበረማርያም ይርጋ ከአብመድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነግረውናል፡፡ የባሕልና ኪነጥበብ ሳምነቱ የጎንደርን ባሕል፣ እሴትና ታሪክ በማስተዋወቅ ጎብኚዎች አካባቢውን እንዲያውቁና ሲመጡም የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ እንደሚረዳቸው ነው የተናገሩት፡፡ 

የዘንድሮው የባሕልና የኪነጥበብ ሳምነቱ ከጥር ሶስት ጀምሮ እንደሚከበርም ሥራ አስኪያጁ ነግረውናል፡፡ በባሕልና የኪነጥበብ ሳምንቱ ዝክረ ቴወድሮስን ጨምሮ በርካታ ባሕላዊና ጥበባዊ ክዋኔዎች ይካሄዱበታል ነው የተባለው፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችን ማሟላት ከተቻለ ሕይወት በቤተመንግሥት የሰተኜው የጎንደርን ነገሥታት ሕይወት የሚያስቃኝ ዝግጅት ሊኖር እንደሚችልም ገልፀዋል፡፡

በዘንድሮው የባሕልና የኪነጥበብ ሳምንት የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻን ጀብዱ በተመለከተ የምሥጋና ሥነ ሥርዓት እንደሚኖርም ተመላክቷል፡፡  የባሕልና የኪነጥብብ ሳምንቱ የከተማዋን ቱሪዝም ለማነቃቃት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ሥራ አስኪያጁ ገብረ ማርያም ተናግረዋል፡፡

የባሕል ሳምነቱ የክልሉ ባህል እንዲገለፅ፣ የኢትዮጵያዊያን ባህል እዲንዲታወቅና ሕብረተሰቡ ተሳታፊ እንዲሆን እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ የጎንደር የኪነጥበብ ቤተሰብ የሚጠበቅበትን ሥራ ለመስራት ተነሳሽነቱ ከፍ ያለ መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ ለኪነ ጥበቡና ለኪነ ጥበበኞች የሚሰጠው ድጋፍ ግን አናሳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የባሕልና የኪነጥበብ ሳምንቱ ብዙ ክዋኔዎችን እንደሚያሳይና ጥምቀትን በጎንደር ተጨማሪ እሴትና ውበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡   ወደ በዓሉ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ባሕሉን እንዲያውቁና እንዲኮሩ እንደሚያደርጋቸውም ተናግረዋል፡፡ የባሕልና የኪነጥበብ ሳምነቱ የመከባበር፣ የመተሳሰብ፣ የአብሮነትና የአንድነት መንፈስን እንደሚያጎለብትም አስረድተዋል፡፡ በዓሉን ለመታደም የሚመጡ ሰዎች የጎንደርን የልማት አማራጮች የሚያዩበትና  አካባቢውን ቀርበው የሚያውቁበት እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡

ጎንደር በርካታ ሁነትና እውነት የሚገለፅባት ናት ያሉት ሥራ አሥኪያጁ  የጎንደርን ባሕልና ጥበብ ለማየት እንግዶች እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡  ኑ ጥመቅትን በጎንደር በፍቅር ከተማዋ በፍቅር እናክብር  ነው ያሉት፡፡

ጥምቅት በጎንደር ሲከበር  ያልተበረዘ ማንነት፣ የማይናወጥ ኢትዮጵያዊነት፣ ጀግነንት፣ ብልህነት፣ ደግነት፣ ውብ ባሕልና ሌሎቹም በአንድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዚያው ያደርሰን፡፡ #አብመድ

 

Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top