የነርሷ እማኝነት በማይካድራ
“በአገራችን ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ ዘግናኝና አሰቃቂ ድርጊት ነው”
– “የሄድንበት አምቡላንስ መንገድ አጥቶ በአስከሬኖች መሃል መንገድ እየመረጠ ነው ከስፍራው የደረሰው”
– ጫካ ውስጥ ባሏ ያዋለዳትን የአስራ አንድ ቀን አራስ አግኝተናል፣
– ሁመራ ሆስፒታል ፅኑ ህሙማን ክፍል ተዘግቶባቸው የነበሩ 22 ታካሚዎች ህይወታቸው አልፏል፣
– ባልና ሚስት አማራ በመሆናቸው ብቻ በትዳር አጋሮቻቸው ተገድለዋል፣
በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ውስጥ ከሚገኙት ጥበበ ግዮንና ፈለገ ህይወት ሆስፒታሎች የተውጣጡ ሰባት የህክምና ባለሙያዎችን ያካተተው ቡድን ከባህር ዳር ተነስቶ ወደ ስፍራው የተንቀሳቀሰው ሰኞ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር።
ቡድኑ ወደ ስፍራው አቅንቶ በትግራይ ልዩ ኃይል ጥቃት የደረሰባቸው በርካታ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የገቡበት ሆስፒታል ነበር።
ቡድኑ ከስፍራው ሲደርስ ወደ ሆስፒታሉ ቁጥሩ በርካታ የሆነ ቁስለኛ በመግባቱ ሳቢያ ለአፍታም እረፍት ማድረግ አልተቻለውም።
ለመከላከያ ሰራዊት አባላትም ሆነ ለትግራይ ልዩ ሃይል የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ ያመሸው ቡድኑ፤ አመሻሹን የሰማው መርዶ ማመን የሚያስቸግር ነበር። ከቡድኑ አባላት አንዷ የሆነችው ሲስተር በላይነሽ ውቤ እማኝነቷን ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነግራታለች።
አብራጀራ ሆስፒታል እንደገባን እህል እንኳን ሳንቀምስና እረፍት ሳናደርግ ወደ ስራሳችን ገባን-ብዙ ቁስለኛ ነበር።
ለእነሱ የህክምና እርዳታ እየሰጠን አመሻሹ ላይ ማይካድራ ላይ በንፁሃን ወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን ዘግናኝ የጅምላ ጭፍጨፋ ሰማን። ይህንን እየሰማን መቆየት አልቻልንም። ሁላችንም ወደ ስፍራው መሄድ እንዳለብን አምነን ተነሳን። አንቡላንሳችን እየተተኮሰበት ነበር የደረስነው።
ማይካድራ ላይ ደግሞ በየሜዳው የወደቀው አስክሬን አምቡላንሱን መሄጃ አሳጥቶት፣ በአስክሬኖች እስፍራው መሃል መንገድ እየመረጠ ነው የደረስነው። ሁኔታው እጅግ የሚዘገንን፣ በህይወቴ ያጋጥመኛል ብዬ የማላስበው ሰቅጣጭ ነበር። እዚህም እዚያም አስክሬን ወድቆ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ፣ በገመድ የታነቁ፣ በቢላ ፣ በገጀራ የታረዱ…. ዘግናኝ አስክሬኖች በየሜዳው ተጥለው ነበር። ሁሉም የቡድኑ አባላት ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም። በጥይት ተመትቶ መሞት መታደል የሆነበት የሰው ልጅ ክብሩ- አስከሬኑ ተራቁቶ….. የተጣለበት ዘግናኝ ሁኔታ ነበር ያየነው።
ሰው በዘሩ ብቻ እየተመረጠ የተገደለበት፣ ባል የሶስት ልጆቹን እናት ሲሆን ሚስት የአራት ልጆቿን አባት በአማራነታቸው ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉበት በአገሬ ይከሰታል ብዬ የማላስበውን ዘግናኝ ድርጊት አይቻለሁ።
የጅምላ ጭፍጨፋው የተካሄደ እለት ምጧ መጥቶ ወደ ጤና ጣቢያ የሄደች ነፍሰ ጡር፤ የአማራ ተወላጅ ሴት አንቀበልም ተብላ ከጤና ጣቢያ ተባርራ ከባሏ ጋር ወደ ጫካ ገብታ በመደበቋ ህይወቷ ቢተርፍም፣ እዛው ጫካ ውስጥ በባሏ አዋላጅነት የተገላገለች ሲሆን ለአስራ አንድ ቀናት በኋላ በዛው በጫካ ውስጥ ቆይታ አግኝተናል።
በገጀራ ተመተው ተጥለው ከአስክሬን መሃል በህይወት የተረፉ ሰዎችንም አግኝተናል፣ ሁለት ሶስት ቀን ጫካ ውስጥ ያለ ምግብና ውሃ የቆዩና በተለያዩ ስለቶች የተወጉ ሰዎችንም በአምቡላንሶች እየፈለግን ከየጫካው ለቅመናል። ይህ በአገራችን ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም ከማይታወቅ ዘግናኝና አሰቃቂ ድርጊት ነው። ቡድኑ ወደ ስፍራው በመሄዱ እነዚህን ወገኖች ከሞት መታደግ ችሏል።
በማይካድራው ሁመራ ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው ሲታከሙ የነበሩ 22 ፅኑ ታማሚዎች፣ ሐኪሞቹ በር ዘግተው ጥለዋቸው ስለሄዱ ህይወታቸው አልፏል።
ይህ በህክምና ሙያ ዲሲፕሊን ፈፅሞ የማይደረግ አረመኔያዊነት ነው። በዚህ ሙያ ውስጥ በቆየሁበት ጊዜ እንደዚህ አይነት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሲፈፀም ማየት ቀርቶ በጆሮዬም አልሰማሁም። ሁኔታው ልብ ይሰብራል። ወደ ስፍራው ተጉዞ ለወገኖቹ የህክምና እርዳታ ሲሰጥ የቆየው የህክምና ቡድን አባል በመሆኔ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ ብላለች……
የህክምና ቡድኑ በትናንትናው ዕለት በሌሎች የህክምና ቡድን አባላት ተተክቶ ወደ ባህር ዳር መመለሱን ሲስተር በላይነሽ ተናግራለች።
( መታሰቢያ ካሳዬ – አዲስ አድማስ)