“21ኛ ክፍለ ጦር የተሰጠውን ተልዕኮ በስኬት እየተወጣ ወደ መቀሌ በመገስገስ ላይ ነው” – የክፍለ ጦሩ አዛዥ ኮለኔል መኳንንት ሲሳይ
(እያሱ መሰለ -ራያ ግንባር)
21ኛ ክፍለ ጦር የተሰጠውን ሕግ የማስከበር ተልዕኮ በስኬት እየተወጣ ወደ መቀሌ በመገስገስ ላይ መሆኑን የክፍለ ጦሩ አዛዥ ኮለኔል መኳንንት ሲሳይ አስታወቁ፡፡
ኮሎኔሉ ትናንት በአካባቢው ለሚገኘው የጋዜጠኖች ቡድን እንዳስታወቁት፣ 21ኛ ክፍለ ጦር የአሸባሪው ትህነግ ታጣቂዎች የተመኩባቸውን ሦስት ወሳኝ ምሽጎች ደረማምሶ፤ ከባድ መሣሪያዎችን አውድሞ እግር በእግር እየተከተለ በጁንታው ሃይል ላይ ከፍተኛ ሰብኣዊና ቁሳዊ ኪሳራ አድርሷል፡፡
የጁንታው ታጣቂዎች የ21ኛው ክፍለ ጦርን የጀግንነት ገድል የሚያውቁ በመሆኑ እፊቱ ቆመው አይዋጉም ያሉት ኮሎኔሉ፣ ጁንታው በአሁኑ ወቅት ከእጁ እየወጡ ለመከላከያ ሠራዊቱ እጃቸውን የሚሰጡ ታጣቂዎች ቁጥር ዕለት ተዕለት እየጨመረ በመምጣቱ የታጣቂዎቹን የተሸናፊነት ሥነ ልቦና ለማበረታታት ሲል 21ኛው ክፍለጦር ላይ ጉዳት አድርሻለሁ እያለ በማስወራት ላይ ነው ብለዋል፡፡
ጁንታው በበርተክላይ፣ ቶኦ እና በአዲቀይህ መውጫ የሚመካባቸው ምሽጎቹ በ21ኛው ክፍለጦር ከተደረማመሱ በኋላ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የተበታተኑ ታጣቂዎቹን ለማሰባሰብ እየሞከረ መሆኑን ጠቁመው፣ ያሸነፈና ያጠቃ ሃይል ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አይሸሽም ብለዋል። ወደ ኋላ እየሮጠ አጥቅቻለሁ ማለቱ የተለመደ የውሸት ባህሪው ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
ጁንታው የያዘው ፕሮፓጋንዳ የትህነግ ታጣቂዎች 21ኛው ክፍለ ጦር ከተደመሰሰ እጃቸውን ከመስጠት ይልቅ የመዋጋት ሥነ ልቦና ገንብተው ወደ ውጊያ በሙሉ ልብ ይመለሳሉ ከሚል ቀቢፀ-ተስፋ መሆኑን ገልፀዋል።
21ኛው ክፍለ ጦር በድል ላይ ድል እየተቀዳጀ፤ ወኔውና ሞራሉ እየጨመረ ወደፊት በመገስገስ ላይ ነው ያሉት ኮሎኔል መኳንንት፣ ክፍለጦሩ ወደፊትም የሚሰጡትን ግዳጆች በድል ለመወጣት በሙሉ አቋምና ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ከጁንታው መለያ ባህሪዎች ውስጥ አንዱና ዋንኛው ውሸት ነው ያሉት ምክትል አዛዡ፣ የዚህ ኦፕሬሽን አላማም ይህንን ውሸታም፣ ስግብግብና ዘራፊ ቡድን ይዞ ለፍርድ ማቅረብ ነው ብለዋል፡፡
በ21ኛው ክፍለ ጦር የሦስተኛ ብርጌድ አዛዥ ኮሎኔል ተክሉ ሁሪሳ በበኩላቸው፣ ክፍለጦሩ የጁንታው ታጣቂዎች ተራራማ ቦታዎች ላይ ምሽግ በመቆፈር እንደታንክና ሌሎች ከባድ መሣሪያዎችን በምሽግ ውስጥ አሰልፈው የወገንን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ቢሞክሩም በጀርባ በመግባት ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ምሽጎችን ማስለቀቁን አስታውቀዋል፡፡
ቡድኑ ሽንፈቱን ተከናንቦ ወደ ኋላ እየሮጠ እያለ ከአላማጣ አውደ ወጊያ ጀምሮ 21ኛው ክፍለ ጦርን ደምስሰናል የሚል ነጭ ውሸት እያወራ እንደነበር አስታውሰው፣ 21ኛው ክፍለ ጦር ከሙሉ ሃይሉና ዝግጁነቱ አሁንም ቀጣይ ድሎችን ለማስመዝገብ ወደፊት እየገሰገሰ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
(አዲስ ዘመን)