ምርጫ ቦርድ በተለያዩ መመሪያዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክሮችን አከናወነ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ 1162/ 2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት የተለያዩ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ከመጽደቃቸው በፊት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ምክክሮችን እያደረገ ይገኛል፡፡
የምክክሮቹ አላማ በባለድርሻ አካላት የሚሰጡ ግብአቶችን ለማካተት እና መመሪያዎቹንም ለማስተዋወቅ ሲሆን ባለፈው አርብ ህዳር 11 ቀን 2013 ዓም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰአት ድልድል መመሪያ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሚዲያዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ የአየር ሰአት ድልድል ቀመር፣ ድልድሉ ከዚህ በፊት የተካሄደበት መንገድ እና የድልድሉ ማከናወኛ ቴክኖሎጂ በቦርዱ እና በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አማካኝነት ቀርበዋል።
በውይይቱም ከዚህ ቀደም በፓርላማ መቀመጫ ያለው ፓርቲ የሚያገኘው የአየር ሰአት ከ60 በመቶ ወደ 5 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉ የውድድሩን ሜዳ የተሻለ እንደሚያደርገው የፓርቲዎች ተወካዮች ገልጸዋል፡፡ ለአየር ሰአት ድልድሉ ፓርላማ መቀመጫ መስፈርት በተጨማሪ
– በእኩል የሚደለደል – 25 በመቶ
– ፓርቲው በሚወዳደርበት የፌደራል እና/ወይም የክልል ም/ቤቶች በሚያቀርባቸው እጩዎች ብዛት የሚደለደል- 40 በመቶ
– ፓርቲው በሚያቀርበው የሴት እጩ ተወዳዳሪዎች ብዛት የሚደለደል፣- 20 በመቶ
– ፓርቲው በሚያቀርበው የአካል ጉዳተኛ እጩዎች ብዛት የሚደለደል፡፡ – 10 በመቶ
መሆኑ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱም ለሴት እጩዎች ማቅረብ የተቀመጠው ቀመር በዝቷል የሚል ሃሳብ ከፓርቲዎች ቀርቦ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ መስፈርቶቹ የተቀጡበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ቀመሩን መሰረት በማድረግ ስለሚኖረው የአሰራር ስነስርአት እና የግል ሚዲያዎች የጠበቅባቸው ሃላፊነት ላይ ለተጠየቁ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ዛሬ ህዳር 14 ቀን 2013 ቀን በልዩ ሁኔታ የሚቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች መመሪያ እና የአርብቶ አደር መራጮች ምዝገባ መመሪያ ከሲቪል ማህበራት ጋር ውይይት ተደረገባቸው ሲሆን በተለይም በአርብቶ አደሮች ፤ተማሪዎች፣ በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ፤ በሴቶችና አካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰሩ ሲቪል ማህበራት በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
የሁለቱ መመሪያዎች ዋና አላማ ከቋሚ የመኖሪያ አድራሻቸው ርቀው የሚኖሩ ዜጎች በህገ መንግስቱ የተረጋገጠላቸውን የመምረጥ መብት በተሟላ መልኩ ለመጠቀም እንዲችሉ ተደራሽ የሆነ አሰራር ለመዘርጋት እንዲሁም በአርብቶ አደር አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ከአኗኗራቸው ዘይቤ አኳያ የመምረጥ መብታቸውን ሳይጠቀሙ እንዳይቀር ለማድረግ የሚያስችል ስርአት መዘርጋት መሆኑ በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ወቅት የመራጮች ምዝገባ በአርብቶ አደር አካባቢዎች እንዲሁም በተፈናቀሉ ዜጎች መኖሪያዎች እንዴት ሊሆን እንደሚችል፣ የመራጮች ምዝገባ እና የምርጫ ቀን በልዩ ሁኔታ እንዴት እንደሚስተናገድ፣ የአንድ ምርጫ ጣቢያ የመራጮች ቁጥር ( 700 መራጮች) አወሳሰን እንዴት እንደሆነ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን የተለያዩ መመሪያዎቹን የተሻለ ሊያደርጉ የሚችሉ ግብአቶችም ተገኝተዋል፡፡
(የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ)