Connect with us

ከኢትዮጵውያን ህዝቦች ለትግራዋይ ወንድሞቹ የተላለፈ ጥሪ!

ስማ የትግሬ ሰው!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ከኢትዮጵውያን ህዝቦች ለትግራዋይ ወንድሞቹ የተላለፈ ጥሪ!

ስማ የትግሬ ሰው!…

ከኢትዮጵውያን ህዝቦች ለትግራዋይ ወንድሞቹ የተላለፈ ጥሪ!

መቀሌ እጇን እንዴት ትሰጥ ይሆን?

(ተስፋጽዮን በድሬቲዩብ)

መቼም ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ትግራይ ህዝብ አሳረኛ ህዝብ የለም፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ታግሎ፣ ከህይወት ጋር የሚያደርገው የሞት ሽረት ግብግብ አንሶት የገዛ ራሱ ልጆች ለዘመናት መከራን ሲጨምሩለት ኖረዋል፡፡ 

ለጦርነት አጋላጭ ጂኦግራፊውም በደጉ የትግራይ ህዝብ ላይ የበረታ ይመስላል፡፡ ባለፉት 200 ዓመታት ብቻ አብዛኞቹ ትላልቅ ጦርነቶች በዚሁ ምድር ላይ ነው የተካሄዱት፡፡ የዶጋሊ፣ የአምባላጌ፣ የማይጨው፣ የመቀሌ፣ የአድዋ፣ የደደቢት፣ የሽሬና የባድሜ ጦርነቶች በሙሉ ከተከዜ ማዶ የተካሄዱ ናቸው፡፡

ምድሩ በቀለሃ፣ አየሩ በባሩድ ወይቧል፡፡ አጥንት ያላገጠጠበት፣ ደም ያልፈሰሰበት ሰርጥ በዚህ ተራራማ ሀገር ማግኘት አይቻልም፡፡ ከትውልድ ትውልድ ሳይቋረጥ አያት፣ አባትና ልጅ በተከታታይ የጠብመንጃ እሩምታ፣ የመድፍ ድንፋታ፣ የታንክ ማጓራት ድምጾችን ሰምተዋል፡፡ በዘመናት መካከል ያንን አስፈሪና ሰቅጣጭ ድምጽ ያልሰማ ትግራዋይ ማግኘት እብለት ነው፡፡ በጦርነት ያልተቀጠፈ፣ አካሉ ያልተጎዳ የቤተሰብ አባል የሌለበት ቤት ማግኘት አይቻልም፡፡

ይህ ሁሉ አንሶ አሁንም በእብሪት የተወጠሩ ጥቂት ስግብግብ ልጆቹ የትግራይን ህዝብ ወጣት ልጆች በፕሮፓጋንዳ ውርጅብኝ አእምሯቸውን አጨልመው ሌላ ዙር እልቂት ውስጥ ሞጅረውታል፡፡ በቂ ስልጠና ሳይወስድ፣ በቂ ስንቅና ሎጂስቲክስ ሳይዘጋጅለት፣ የተደራጀ የእዝ ሰንሰለት እንኳን ሳይፈጥሩለት “በድንጋይ ኮሎኔል ማርከህ ና” ብለው እየላኩ ሌላ ዙር ማቅ ለትግራዋይ እናቶች ደርበውላቸዋል፡፡

ለመሆኑ ይህ ምድር የምንጊዜም የአኬልዳማ መሬት እንዲሆን ያደረገው ምክንያት ምን ይሆን? ትግራዋይ እናቶች እንደማንኛውም ኢትዮጵውያን እናቶች ልጆቻቸውን ቆንጥጠው፣ መክረው ዘክረውና ገስጸው እንደሚያሳድጉ ለማየት ሽሬ ወይም አክሱም አካባቢ ከከተማ ወጣ ብሎ ያለ ገጠራማ ቦታ የሚኖሩ እናቶች ደሳሳ ጎጆ ዘለቅ ብሎ አንድ ቀን መዋል በቂ ነው፡፡ 

የትግራይ እናቶች ለልጆቻቸው  ጂጂ በግጥምና በዜማ “በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር…. በድል እኖራለሁ ይሄው በቀን በቀን…” ያለችውን ምስጢር በዝርው ቀን በቀን እየነገሩ እንደሚያሳድጓቸው እዚህ መሀል ሀገር ሆኖ ማመን ይከብድ ይሆናል፡፡ 

የትግራይን ህዝብ በድምጺ ወያኔና በትግራይ ቴሌዝቭን ብቻ ለሚያውቅ ለአንድ የሸዋ ሰው ግን ከራማ እስከ ማይጨው፣ ከአዲግራት እስከ ሽሬ እንዳስላሴ፣ ከእንጢጮ እስከ ውቅሮ፣ ከመቀሌ እስከ አድዋ፣ “ኢትዮጵያ” ሲባል የሚነዝራቸው ብዙዎች እንዳሉ ማሳመን ሞኝነት ይመስል ይሆናል፡፡ የትግራይ ምድር ኢትዮጵያን የሚወዱ፣ ከሌሎች አህዝቦች ጋር በኩራት በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር መኖርን የሚውቁበት አያሌ ልጆችን ቢያፈራም በየዘመኑ ጥቂት የሆኑ፣ ነገር ግን ህዝባቸውን ብረት እያስነከሱ፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋር የቂም ልቃቂት የሚጎትቱ፣ እነሱ ዘርፈው ድሃውን ትግራይ ገበሬ አንገት የሚያስደፉ፣ ባንዳ ሆነው ሀገር ወዳዱን የትግራይ ህዝብ ያለስም ስም የሚያሰጡ ጥቂት እንክርዳዶችም ይወለዳሉ፡፡

ከቀናት በፊት ህወሃት የሞት ሞቷን እያጣጣረች፣ በእብሪት የማገደችው ወጣት ልዩ ሃይል ሲፈጅባት፣ ህዝቡ በሙሉ በነቂስ ወጥቶ በመከላከያ ሰራዊቱ አፈሙዝ ፊት እንዲቆምና እንዲያድናቸው በተማጸኑባት መግለጫቸው ላይ፣ የአጼ ምኒሊክን ስም በሚያስቅም በሚያሳቅቅም ሁኔታ አንስተው ነበር፡፡ “አባቶቻቸው እነአጼ ምኒሊክም የልጆቻችንን ብልት እየቆረጡ ዘራችን ለማጥፋት እንደሞከሩት፣ አሁንም የመጡት ወራሪዎች ዘራችንን ሊያጠፉን ነው” የሚል ህዝቡን ወደ እሳቱ አንቀልቅሎ የሚከት ፕሮፓጋንዳ ለመስራት ሞክረዋል፡፡ ይሄኛውስ የተሳካላቸው አይመስለኝም፡፡

ይህ አይነቱ ፕሮፓጋንዳ ቀደም ሲልም በአጼ ምኒሊክ ላይ የሚነዙት የውሸት ትርክቶች እንደዚህ ላሉ ህዝብን ለእልቂት መጋበዣ እኩይ ፈጠራዎች መሆናቸውን ከማጋለጥ ባለፈ ዋጋ የላቸውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም፣ ትግራዋይን እንደሚጠሉ፣ ዘራቸውንም ሊያጠፉ እንደሚሹ፣ አረመኔና እርጉም እንደሆኑ አሰልቺ በሆነ ሁኔታ የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ የዛሬ 120 ዓመት አጼ ምኒሊክ የትግራዋይን ዘር ለማጥፋት እንደሞከሩ ተደርጎ ከቀረበው የፈጠራ ትርክት የሚለይ አይደለም፡፡

ታሪክ እንደሚነግረን ግን፣ በጊዜው ምኒሊክን ከድተው ባመጹ ጥቂት እብሪተኞች የተነሳ ንጉሱ ለትግራይ ህዝብ የነበራቸውን ክብር ቅንጣትም እንዳልነካው ይመሰክራል፡፡ አጼ ምኒሊክም ሆኑ ጠ/ሚ አቢይ የትግራይን ህዝብ ከባለጌ ለጆቻቸው ለይተው፣ አመጸኞችን በመቅጣት ህግን ከማስገበር ያለፈ ምናምኒት አላማ የላቸውም፡፡

ከአጼ ዮሃንስ በመተማ መሰዋት በኋላ በትግራይ ባላባቶች መካከከል የስልጣን ሽሚያ፣ መከፋፈልና መካካድ ነግሶ ነበር፡፡ አጼው መተማ ላይ ከመሞታቸው በፊት ራስ መንገሻን ዙፋን ወራሻቸው እንደሆነ ተናግረው ቢሞቱም ሌሎችም መሳፍንት ስልጣኑ ይገባናል በማለታቸው ቁርቁሱ የትግራይን ህዝብ እርስ በርሱ ሊያባላው ደረሰ፡፡ 

አንዱ ካንዱ ጋር ሲያብር፣ ሌላው በምቀኝነት ከውጪ ሀገራት ጋር ሲዶልት፣ ሌላው ደግሞ ከንጉስ ምኒሊክ ጋር ተባብሮ ሌላኛውን ለመጣል ሲሞክር የተከሰተው ፍጅት በእንዲት ትንሽ ግዛት ላይ የተከናወነ የስልጣን ሽኩቻ አይመስልም፡፡ በተለይ በራስ መንገሻ፣ በራስ ሀጎስ፣ በደጃች ስዩምና በራስ ስብሃት መካከከል የነበረው ፍጥጫ እስከሸዋ ድረስ አስጨንቆ ነበር፡፡ ይህም ክስተት በሁሉም መስፈርት፣ ማለትም በክብረ ነገስቱ፣ በጦር ሀይል፣ በግዛት ስፋት ንጉሰ ነገስትነቱ እንደሚገባቸው ሀገር የመሰከረላቸው  የሸዋው ንጉስ ምኒሊክ ንጉሰ ነገስትነቱን በቀላሉ እንዲጨብጡ አስቻለቸው፡፡

ንጉስ ምኒሊክ የሸዋ ንጉስ ብቻ ይባሉ እንጂ አጼ ዮሃንስ በህይወት እያሉም ግዛታቸው ስፋት ከአጼው በብዙ እጥፍ ይሰፋ ነበር፡፡ በደፈናው ሸዋ የሚባለው ግዛታቸው በምስራቅ ከአዳል ወይም አፋር ጫፍ እስከ ምዕራብ ወለጋ፣ ከበቡብ ምእራብ ሃረር እስከ ሰሜን ምዕራብ ጀማ ወንዝ አፋፍ፣ ከሰሜን ምስራቅ ወሎ እስከ ደቡብ ምዕራብ ከፋ፣ በደቡብ ጫፍ ከኦጋዴን በረሃ ዋቢሸበሌንና ኦሞ ወንዝን አልፎ እስከ ቱርካና ሀይቅ፣ ከጊቤ ማዶ ጂማ እስከ አርሲና ባሌ እንዲሁም ቦረናን የሚሸፍን በመሆኑ ቀጣዩ ንጉስ የብርቱው አንኮበር ሰው ንጉስ ሳህለስላሴ የልጅ ልጅ እንደሚሆን አገር ሁሉ ያወቀው፣ ጸሃይ የሞቀው ሀቅ ነበር፡፡

ንጉሰ ነገስቱ ከንጉሰ ነገስትነታቸው በተጨማሪ፣ ከሚገዙት ከትግራይና ከቤጌምድር በስተቀር ምኒሊክ ከራስ ዳሽን በታች ያለው ሀገር ራሳቸው ጥረት አብዛኛውን በሰላምና በድርድር፣ እምቢ ያለውን በነፍጥ ወደ ሸዋ አከማችተው ስለነበር በይፋም ባይሆን በውስጠ ታዋቂ ቀደም ብለው ንጉሰ ነገስት ሆነው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ከጎጃሙ ንጉስ ተክለሀማኖትና ከሌሎችም ነገስታት ጋር ጥሩ ግንኙነት መስርተው ወደ ሰለሞን ዙፋን የሚወስደው መንገድ ወለል ብሎ ተከፍቶ እየጠበቃቸው ነበር፡፡ 

ከአጼ ዮሃንስ ሞት በኋላ በትግሬ ምድር የተፈጠረው የስልጣን ሸኩቻ ሁሉንም መሳፍንት መኳንንት ስላዳከማቸው በቀላሉ ራሳቸውን ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ብለው መሃል ሸዋ እንጦጦ ላይ ተቀቡ፡፡ ራስ መንገሻም ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የትግራይ ክፍለ ሀገር ገዢ ሆነው ተሾሙ፡፡ ወዲያው ግን ምኒሊክን ክደው አመጹ፡፡ እንደገና ይቅርታ ጠይቀው ከታረቁ በኋላ ትንሽ ቆይተው በድጋሜ አመጹ፡፡

ጳውሎስ ኞኞ ስለሁኔታው ሲያስረዳ “የአድዋ ድል በተገኘ በዓመቱ ገደማ ራስ መንገሻ “ናፍቄያለሁና መጥቼ አይንዎን ልይ” ብለው ወደ አጤ ምኒሊክ ልከው ካስፈቀዱ በኋላ በታህሳስ ወር አዲስ አበባ ገቡ፡፡ በዚህ ጊዜ ራስ መንገሻ የእቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅ ወይዘሮ ከፈይን አግብተው ስለነበረ ለምኒሊክ ቤተመንግስት ቤተኛ ሆነዋል፡፡ 

አዲስ አበባም በታላቅ ክብርና ደስታ ከርመው፣ ተሸልመው፣ ለሰራዊታቸው ደመወዝ 60 ሺህ ብር ተቀብለው ወደ ግዛታቸው ወደ ትግራይ ሄዱ፡፡ ትግራይ ሲደርሱ እንደገና የመሸፈታቸው ወሬ ተሰማ፡፡ ለአጼ ምኒሊክም “ከእንግዲህ ወዲያ የምንገናኘው በጦርነት ነው” የሚል መልዕክት ላኩ፡፡

አጼ ምኒሊክም የወሎውን መምህር አካለወልድን፣ የግሼኑን ግራጌታ ውቤንና አባ ወልደ ገብርኤልን መስቀል አስይዘው “የትግሬን አድባራትና ታቦት ሁሉ ይዛችሁ እኔ በድዬህ እንደሆነ ማረኝ፣ ይቅር በለኝ፣ ብላችሁ መስቀሉን ይዛችሁ ውደቁና አስታርቁኝ” ብለው ላኩ፡፡ እቴጌ ጣይቱም ልብ የሚነካ ረጅም ደብዳቤ ጽፈው ለሽማግሌዎቹ ላኩ፡፡ ደብዳቤውም “.. እኛ ያንተን ቤት እንሰራለን ብለን ስንደክም አንተ የእኛን ቤት አፈርሳለሁ ብለህ አሰብከውን? ይሄንን ነገር እግዚአብሄር ይወደዋልን? ሰይጣን ያደረበት ሰው አነሳስቶሃል እንጂ አንተስ ይሄንን ነገር አታደርገውም፡፡ አሁንም ልጄ፣ ስለመድሃኔዓለም፣ ስለተሰቀለው ጌታ፣ ስለወደላዲተ አምላክ አማጥኜሃለሁ፡፡ 

ይህንን ክፉ ሃሳብህን ተው፡፡ ሰይጣናትን ክንፋቸውን ስበረው፡፡ … ደግሞም ከአሁን በፊት ከአድዋ አንስቶ እስከ እንቲጮ ድረስ የፈሰሰው ደም ወደ እግዚአብሄር ቢጮህ አያስጎዳህም? ደግሞ ሁለተኛ የሸዋና የትግሬ ወንድማማቾች ደም ይፍሰስን? እኔ የእናትነቴን መከርኩህ፡፡ እግዚያብሄር ደግሞ ይጨመርበት፡፡”

ከእቴጌ ጣይቱ ደብዳቤ ጋር ጉዳዩ ያሳሰባቸው የደብረ ሊባኖስ ሊቃውንትና መምህራን እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፈው ላኩ፡፡ “…..አጼ ዮሃንስ የትግሬን ሰው ረግመውታል ሲሉ እንሰማ ነበር፡፡ ይሄውም ይታወቅ ዘንድ ከመተማ ከገባችሁ ወዲህ የትግሬ ሰው መኳንንቱም ወታደሩም፣ ባላገሩም እርስ በርሱ ሲተላለቅ ኖረ፡፡ 

ያው ያጼ ዮሃንስ እርግማን እስከዛሬ ድረስ ከትግሬ ሰው ላይ አልተነሳምና እርስዎን በጤና አላስገዛም ብሎ ነው እንጂ፣ ሌባ፣ ቀማኛ፣ ወንበዴ በጠፋበት ጊዜ፣ ሴት ወርቅ በራሷ ላይ አድርጋ ብትሄድ በማትነካበት፣ እህልና መሬት ሰውና እህል በተስማማበት ጊዜ፣ ዳር እስከዳር ሀገሩ ሁሉ ጸጥ ብሎ በተገዛበት ጊዜ፣ በሰሜን፣ በበጌምድር፣ በጎጃም ነቅዐ አልወጣ፣ ደርቡሽ እንኳን አጼ ዮሃንስን ያህል ንጉሰ ነገስት ገድሎ ዳግመኛ በእግዚአብሄር ቸርነት ባገራችን ብቅ አላለብንም፡፡ እንደ እርስዎ ያለ ሰው የጌታ ልጅ፣ መሰረተ ጌታ፣ ለበጎ አርዓያ አብነት ይሆናሉ እንጂ፣ ራስ መንገሻ ሸፈተ ይባላሉን? ለክፉ አርዓያ መሆን መቼ ይገባል?…. አጤ ምኒሊክ እንደሆኑ እንደ ፈጣሪቸው ነቅዓ ምህረት ናቸው እንጂ ክፉ ነገር መቼ በሰው ይሰራሉ? ይህንን ሰይጣን ያነቃውን ነግር እናጥፋው፡፡ ክንፉን እንስበረው፡፡ ስለተሰቀለው ጌታ፣ ስለኩርዓተ ርዕሱ ብለው ይተዉልን” የሚል ደብዳቤ ለሽማግሌዎቹ ላኩ፡፡

እነዚህን ሁለት ደብዳቤዎችና የአጤ ምኒሊክን የቃል መልዕክት የያዙት መልዕክተኞ መቀሌ እንደገቡ ከትግራይ ጌታ ሀይሉን፣ ጌታ ገብረ ጊዮርጊስንና ሌሎችንም መኳንንትና መምህራን ጨምረው ከራስ መንገሻ ዘንድ ገብተው “ጃንሆይ ልከውን ነው… እሳቸው እንዳሉት መማር የሚገባ ለእኔ ነበር፡፡ 

ግን አንተ ማረኝ…. ብላችሁ መስቀሉን ተሸክማችሁ ውደቁ ብለውናል” ብለው መስቀሉን በየቆባቸው እየያደረጉ ወደቁ፡፡ ራስ መንገሻ ግን ሳቁባቸው፡፡ አጤ ምኒልክም በ1891 ዓ.ም በጥቅምት ወር ደሴ ሄደው ወረኢሉ ነበሩና ወደ ራስ መንገሻ የተላኩት መልእክተኞች “እኛ አልሆነልንም፡፡ የሚያደርጉትን ያድርጉ፡፡” ብለው ላኩባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ አጤ ምኒሊክ በራስ መንገሻ ቦታ ላይ ራስ መኮንንን ሾሟቸው፡፡ ወዲያውም ቀጥሎ ያለውን አዋጅ በመላው ትግራይ አሳወጁ፡፡

“ስማ የትግሬ ሰው…

“…ራስ መንገሻ ስወደው ጠልቶኛልና ግፌን እይልኝ፡፡ እኔ ግን የአጤ ዮሃንስን ውለታ እመልሳለሁ ብዬ መኳንንትና ወታደር ሳይወደው በግድ ሹሜው ነበርና መሬት አሰናበተችው እንጂ እኔ በድዬው አይደለም፡፡ አሁንም የትግሬ ሰው፣ አንተ ወዳጄ ነህ፡፡ ራስ መንገሻ ከዳኝ ብዬ በሱ፣ ተናድጄ አላጠፋህም፡፡ 

እግዚአብሄር የሰጠኝን አገሬን በእጄ አድርጌ አለማዋለሁ፡፡ ደስ አሰኝሃለሁ፡፡ ከእንግዲህ አራሽ እረስ፣ ነጋዴም ነግድ … ከዚህ በኋላ ከራስ መንገሻ ጋር የተገኘህ ሰው ግን በነፍስህ ተገዝተሃል፡፡ በስጋም እኔ እቀጣሃለሁ፡፡”

አጼ ምኒሊክ ይሄንን አዋጅ በመላው ትግራይ ካሳወጁ በኋላ ምናልባት ራስ መንገሻ ጦርነት ያስነሱ እንደሆነ በማለት ከአዲሱ ተሹዋሚ ራስ መኮንን ጋር ራስ ሚካኤልን፣ ራስ ጓንጉልንና ደጃዝማች አባተን አብረው እንዲሄዱ አዘዟቸው፡፡ እነዚህ መኳንንት መቀሌ ሲደርሱ ራስ መንገሻ ከመቀሌ ወጥተው ጣሊያኖች ከሰሩት እዳጋ ሀሙስ ካለ ምሽግ ውስጥ ገቡ፡፡ ከራስ መኮንን ጋር የሄደው ጦርም እዳጋ ሀሙስን ከቦ ተቀመጠ፡፡

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ራስ መንገሻ በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ በድጋሜ ተጠየቁ፡፡ በተለይም ራስ ሚካኤል የአጤ ዮሐንስ ክርስትና ልጅ በመሆናቸው ከራስ መንገሻ ጋር ልዩ ወዳጅነት ነበራቸውና “እባክህ እኔ ላስታርቅህ፡፡ ምን ሆንክና ነው? ያንተን ሀገር የሚሾምብህ የለ፣ አትታሰር፡፡ አጤ ምኒሊክንና እናትህን እቴጌ ጣይቱን ትተህ ለምን እምሽግ ትገባለህ?” ብለው ደጋግመው ደብዳቤ ጻፉላቸው፡፡ ራስ መንገሻ ግን ሁሉንም አልሰማ ብለው እምቢ አሉ፡፡

ከዚህ በኋላ ከራስ መኮንን ጋር ያሉት መኳንንት መክረው ለመዋጋት ወሰኑ፡፡ ወስነውም እነሱ በፊት ለፊት በግንባር፣ ከበስተኋላ በአጋሜ በኩል ደግሞ አራት ሺህ ጠብመንጃ የያዘ ሰራዊት አሰለፉ፡፡ ለመሰለል የወጣ ጥቂት የራስ መንገሻ ሰራዊት በአጋሜ በኩል ከተሰለፉት ወታደሮች ጋር ተገናኝቶ ተኩስ ከፈቱ፡፡ የራስ መንገሻም ሰዎች ተጎድተው ተረፉት ወደምሽጋቸው ተመለሱ፡፡

ስለመጨረሻው ሁኔታ ጸሃፌ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ በጻፉት ታሪክ እንዲህ ይላሉ፡፡ “… ራስ መንገሻ የሰፈረበት ምሽግ አጠገብ ያለ ተራራ፣ በሰማይ ደመና ሳይዞር፣ ዝናብም ሳይኖር፣ በጠራራ ጸሃይ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሲሆን ገደሉ ተናደበት፡፡ 

የተቀመጡበት መሬት እንደከዳቸው ያንጊዜ አወቁት፡፡ ገደሉም በተናደ ጊዜ እነራስ ሚካኤልና ራስ መኮንን ካሉበት ሰፈር ድረስ ተሰማ፡፡ እነሱም ይህ ነገር የመድፍ ተኩስ ነውን? ጦር መጣ ይሆን? ብለው ታጥቀው ተሰልፈው እስኪወጡ ድረስ የመሬቱ ጩኸት ድምጽ ሲሰማ አንድ ሰዓት ያህል ቆየ፡፡ ከዚያ በኋላ ራስ መንገሻ “ጃንሆይ ትግሬ አገራቸውን ለወደዱት ይሹሙበት፡፡ ብቻ እኔን ለእጄ አስምሩኝ” ብለው አስተማምነው ገቡ፡፡” አጼ ምኒሊክም ትግሬን ለሶስት ከፍለው ከወር ወንዝ ወዲያ ያለውን ሀገር ለደጃዝማች ገብረስላሴ፣ ከወር ወንዝ ወዲህ ያለውን ሀገር ለደጃች አብርሃ፣ አጋሜን ለሹም አጋሜ ደስታ ሰጡት፡፡ ራስ መንገሻ ግን አንኮበር ላይ ታሰሩ፡፡

አንዳንዴ ስትሸነፍ፣ ምድር ስትከዳህ፣ መረዳትና አምኖ መቀበል ጥሩ ነው፡፡ እንደ ራስ መንገሻ ቆራጥ ውሳኔ ወስነህ ህዝብህን ከእልቂት ማዳንም ብልህነት ነው፡፡ ያለዚያ ዘርህን ሊያጠፉ መጡ የምትለውን ህዝብ በጩቤና በቢላዋ ተዋጋ ማለት ዘሩን ለማጥፋት እንደቆረጥክ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ እንዲያውም በማይካድራ የተፈጸመው ጭፍጨፋ በጩቤና በመጥረቢያ የተፈጸመ እንደመሆኑ ያንን አረመኔት ማን እንደፈጸመው እየተናዘዝክ ነው፡፡ 

ሲቪሊያንን በመሰዊያ ላይ በማቅረብ ድል መድረግ እንደምትችል ካመንክ በሀውዜን ለተጨፈጨፉ ንጹሃንም ተጠያቂ ነኝ እያልከን ነው፡፡

የሆነው ሆኖ ለሆኑ ጥቂት ሽፍቶችን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ ደጃች አብረሃ ለጥቂት አመታት ያህል ከምኒሊክ ጋር ወዳጅ ሆነው ከቆዩ በኋላ ከድተው ሸፈቱ፡፡ እንደጋነ ጦር ታዞ ደጃች አብረሃ ድል ሆነው ተይዘው ታሰሩ፡፡ 

ይህን የተደጋገገመ የክህደት በደል ያየው ህዝብም በትግሬዎች ላይ ቂም ይዞ በያገኘበት በታ ሁሉ ይሰድብ ጀመር፡፡ ይህንንም ድርጊት አጼ ምኒሊክ እንደሰሙ የሚከተለውን አዋጅ በህዳር ወር 1902 አወጁ፡፡

አዋጅ

“አንድ ሰው ደጃች አብርሃ ቢከዳ እዚህ የተቀመጠውን እኔን የሚወደኝን የትግሬን ሰው ሁሉ ታስቀይማለህ አሉ፡፡ ሰነፍ ወንድሙ ይታሰርበታል እንጂ ይታረዳልን? አሁንም ዳግመኛ ባደባባይ የትግሬን ሰው የሚያስቀይም ነገር የተናገርህ ትቀጣለህ! አንተም የትግሬ ሰው፣ የሚያስቀይም ነገር የተናገረህን ሰው ተያይዘህ አምጣልኝ፡፡ ዳኝነት ይታይልሃል፡፡”

አሁንም የትግሬ ሰው ስማ፡፡ አመጸኛ ልጆችህ ዛሬም ለግላቸው ስልጣንና ጥቅም ብለው በከንቱ ደምህን ማፍሰስ ይፈልጋሉ፡፡ በእነሱ እብሪት አስራ ሰባት አመት ልጆችህን ገበርክ፡፡ በእነሱ ጎትጓችነት ብረት ነክሰህ፣ አጥንትህን ከስክሰህ፣ ደምህን አፍሰህ ምኒሊክ ቤተመንገስት ካስገባሃቸው በኋላ ኢትዮጵያን ህዝብ ጨቁነው፣ ዘርፈውና በዘር ከፍፍለው ስምህን አነወሩት፡፡ ይህም አንሶህ እነሱን ቤተመንግስት አስገብተህ ወደቤትህ በገባህ በ7 ዓመቱ በእነሱው እብሪት ያለአግባብ በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምድርህን በደም አረከሱት፡፡ ዙሪያህን ካለ ህዝብ ጋር አቆራርጠው ብቻህን ሊያስቀሩህ ቆርጠዋል፡፡

ዛሬ ደግሞ አማራ መጣብህ፣ ኢሳያስ መጣብህ፣ አውሬው አቢይ ዘርህን ሊያጠፋ መጣ እያሉ አንድ ፍሬ ልጆችህን ከትምህርት ቤት እያስወጡ፣ ጠብመንጃ እያሸከሙ ጦርነት ውስጥ ማገዷቸው፡፡ የትግራዋይን ዘር ሊያጠፋ የተነሳው ሌላ ማንም ሳይሆን እነሱ ራሳቸው ናቸው፡፡ እነሱ መቀሌ ውስጥ መሽገው መግለጫ እየሰጡ የትግራይ ወጣት በሰላሳ ዓመት ውስጥ ብቻ በአንድ ትውልድ ለሶስተኛ ጊዜ የደም ግብራቸውን እየገበሩ ነው፡፡ 

የምትወዳትን ኢትዮጵያን ክደው፣ ባለውለታህን መከላከያ ሰራዊቷን አዋርደው፣ የማይሆን ጦርነት ከፍተው ከተሸነፉና ከተከበቡም በኋላ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ሁሉም ትግሬ እስኪሞት ድረስ እንዋጋለን እያሉ ነው፡፡ ሁሉም ትግራዋይ ተሰውቶ እነሱ ጥቂት ቀን ከከረሙ ደንታ የላቸውም፡፡ የማይነካ ነክተው፣ ጨለማ ውስጥ ከተውህ፣ አስርበውህና አስጨንቀውህ ሲያበቁ እንትና እንዲህ አረገህ ይሉሃል፡፡ በላብህ እንጥፍጣፊ የሰራኸውን መንገድ አፍርስው፣ አየር ማረፊያህንና ድልድዮችህንም አውድመው እጉያህ ተደበቁ፡፡ 

ከተማህ ውስጥ መሽገው፣ በልጆችህ ተከበው፣ ቢችሉ ዘርህን ሊያጠፉ፣ ባይችሉ ግን ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ሊያቆራርጡህ ምለዋል፡፡

እባክህ የትግሬ ሰው ስማ… ከበደልንህ ይቅር በለን፡፡ የሰነፍ ወንድሙ ይታሰርበታል እንጂ ይታረዳልን? እኛ ግን ከጥቂት ስግብግብ ከሃዲዎች በቀር አንተ አልበደልከንም፡፡ እባክህ ለሺህ ዘመናት አብረን በኖርንባት ሀገር፣ አብረን በተወደቅንባት አንዲት ሰንደቅ አላማ፣ አብረን ድል ላደረግንባቸው ቀናት፣ አብረን አመድ ለአመድ ለሄድንባቸው ቀናት፣ አብረን ለወደቅንባቸው፣ አብረን ለተነሳንበቸው ቀናት፣ አብረን ፈጣሪን ለበደልንባቸው፣ አብረን ምህረትን ለጠየቅንባቸው ቀናት፣ አብረን ላዘንባቸው፣ አብረን ለተደሰትንባቸው ጊዜያት ስትል እነዚህን ከሃዲ ጁንታዎች ከከተማህ መንግለህ አባራቸው፡፡ 

እምቢ ካሉህ ከተማይቱን ለቀህላቸው ውጣ፡፡ ያንዬ ያንተም የኛም ጠላቶች ሆኑትን እነዚህን አሰዳቢዎች አይቀጡ ቅጣት እንቀጣቸዋለን፡፡ ከዚያም ከመላው ኢትዮጵየያውያንና ኤርትራዊን ህዝቦች ጋር በሰላም ለመኖር ድልድዩን አብረን እንጠግነዋለን! መንገዱንም እንደገና እንሰራዋለን፡፡ 

እኛን እንግዶችህን የምትቀበልበትን አየር ማረፊያውንም እንደገና አሳምረን እንሰራዋለን፡፡ ድልድዩን መልሰን እንጠግነዋለን፡፡ አብረን እንለማለን፣ አብረን እንበለጽጋለን፡፡ በሞቴ!

ይህን ክፉ ቀን በጥበብ ታልፈው ዘንድ የጺዮኗ ማሪያም ጸጋን፣ ማስተዋልን፣ ብርታትን እንድትሰጥህ እንማጸናለን፡፡

ከኢትዮጵውያን ህዝቦች ለትግራዋይ ወንድሞቹ የተላለፈ ጥሪ!

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top