አሁንም የኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭ ይታሰብበት!
(ክብር ገና)
በቅርቡ እየወጡ ካሉ መረጃዎች እንደተረዳሁት ከሆነ ኢትዮ ቴሌኮምን ለውጭ ድርጅቶች ለመሸጥ መደላድል መሆን የሚችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ይህም ኢትዮ ቴሌኮምን በተቻለ ፍጥነት ሊብራላይዝ ለማድረግ እንደተፈለገ አንድ ማሳያ ነው፡፡
ሊብራላይዝ ማድረግ ማለት ተወዳዳሪ የሌለውን ድርጅትን ተወዳዳሪ እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ቴሌኮም የሚሰጠውን ምርት በዋጋ ዝቅ ማድረግ አልያም በጥራት የተሻለ ይሆናል ተብሎ ስለሚታመን ነው ይህ እየተደረገ ያለው፡፡ አንድ ቦክሰኛ የቦክስ መወዳደሪያ ሪንግ ውስጥ ሲገባ ሊጋጠም የሚገባው ከእኩያው ጋር ነው፡፡
ታይሰን ከአንድ አልፎ ሂያጅ መንገደኛ ጋር ቢጋጠም ውጤቱ ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ አሁን ከውጭ የሚመጡት እነዚህ ግዙፍ የቴሌኮም ድርጅቶች እንደ ታይሰን ልምድ እና ትልቅ የካፒታል አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ሠራተኞችን አሁን ካለው ተቋም ስቦ ከመውሰድ ጀምሮ በጣም በርካታ እና አሁን የማናያቸውን ተጽዕኖዎች ማድረስ የሚችሉ ናቸው፡፡
በእኔ እምነት ወደድንም ጠላንም የፈንጆቹ አሽከር ለመሆን ነው እየሮጥን ያለነው፡፡ ፈረንጆቹም ለዘመናት ይህን አድርጉ ሲሉን ነው የኖሩት፡፡ በዚህ ሥራ እኛ እንከብራለን እናንተም ፍርፋሪ አታጡም ዓይነት እሳቤ ነው ያላቸው፡፡ እኛም ይህን እሳቤያቸውንም ተፈጻሚ ለማድረግ እየተሯሯጥን ነው ያለነው፡፡ የተቋምን ድርሻ ከውጭ ለሚመጣ ተቋም እስካስተላለፍን ድረስ የፕራይቪታይዜሽን ዓላማው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
ለብዙ ዓመታት ተጠብቆ የቆየን ሀብት ለውጭ ተቋማት የማስረከብ እንቅስቃሴ ነው አሁን እየታየ ያለው፡፡ የቱን ያህል ልንቀባባውና ልንሳምረው ምንፈልግም እውነታው እሱ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ሊዝብራላይዝ ቢደረግ የተሻለ እና ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት ይገኛል የሚል ታሳቢ ነው ያለው፡፡ ይሁን እንጅ አሁንም በመንግሥት እጅ ተይዞ በአግባቡ ቢሠራበት በጣም የተሻለ አገልግሎት ሊገኝበት እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡
አሁን የተቋሙን ድርሻ ለመሸጥ እንደ ዋና ምክንያት የሚቀርበው የኢንተርኔት አገልግሎቱ ፍጥነት እና ጥራት ተደራሽ አለሆነም የሚል ነው፡፡ ተቋሙ ለውጭ ቢሸጥ ኔትዎርክ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ ይቻላል፤ አገልግሎቱን በተሻለ ፍጥነት እና ጥራት ማግኘት ይቻላል የሚል እምነት በመንግሥት በኩል አለ፡፡
እዚህ ላይ ማንሳት የምፈልገው ጥያቄ አሁንስ የሚመጡት ተቋማት ኢንተርኔት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች ላይ ተደራሽ ማድረግ እንደሚችሉ ማረጋገጫው ምንድን ነው? የሚል ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ለትርፍ ነው የመጡት፡፡
አሁን ኔትዎርክ ተደራሽ ይሁን የሚባልባቸው አካባቢዎች አትራፊ አይደለም ብለው ካሰቡ የሚፈለገውን ሥራ ላይሠሩ ይችላሉ፡፡ መንግሥትም አሁን እንዳለው መብቱን ከሸጠ በኋላ እዚህ አካባቢ ኔትዎርክ የለም እና በቦታው አዳርሱ የማለት ሥልጣን የሚሰጠው መብቱን ያጣል፡፡ መንግሥት ተቋሙን አንዴ ከሸጠ በኋላ በሥራው ላይ የማዘዝ መብት የሚኖራቸው ተቋማቱ ናቸው፡፡
መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለጊዜውም ቢሆን ከመሸጥ ወደኋላ ብሏል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን አየር መንገዱንም በሚመከለት ውሳኔውን የቀለበሰው ለጊዜው ነው፡፡ በእኔ እምነት መንግሥት አየር መንገዱን የመሸጥ ዕቅዱን ለጊዜው ያዘገየው ገበያው በጣም በመዳከሙ ምክንያት ነው፡፡
እኔ እዚህ ላይ መጠየቅ የምፈልገው ኢትዮጵያን ጨምሮ ጠቅላላ የአፍሪካ ተቋማትን ሽጡ የሚለው ትዕዛዝ ከማን ነው የመጣው? እስከምረዳው ድረስ በዚህ መንገድ የአፍሪካ አገሮች እንዳለ እየነዱ ያሉት? በዋናነት የምዕራብ አገሮች ናቸው፡፡ ተቋማቶቻችንን እንድንሸጥላቸው ለበርካታ ዓመታት ሲታገሉ ነበር የቆዩት፡፡ አሁን ደግሞ ደካማ ሆነን ሲያገኙን እንድንሸጥ ከመጠየቅ አልፈው አዘዙን፡፡
በምዕራብ አገሮች ያሉ ኩባንያዎች የሠራተኛ ደሞዝ መክፈል አቅቷቸው በመንግሥት ስር የወደቁት በርካቶች ናቸው፡፡ በዓለም ላይ የቴሌኮምኒኬሽን ዘርፍ በኮቪድ-19 ምክንያት ከሌሎች ዘርፎች አንጻር የተሻለ ጥቅም እየተገኘበት ያለ ዘርፍ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው እንደ ቦይንግ ያሉ ተቋማት ሳይቀሩ ዛሬ በመንግሥት እጅ ላይ ወድቀዋል፡፡
ብዙ ጊዜ መንግሥት የሚጠራው የግል ተቋማቱ ችግሩን ብቻቸውን መወጣት ሲያቅታቸው ነው፡፡ መንግሥት ለምን ይጠራል ከተባለ ከግል ዘርፉ የተሻለ አቅም ስላለው ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አቅም አንሶታል የተባለውን ኢትዮ ቴሌኮምን አቅም ካለው መንግሥት የመነጠል ሥራ ነው እየተከናወነ ያለው፡፡ ይህን ተቋም በስሩ ይዞ የማሳደጉ ጉልበት ያለው ከግል ዘርፉ ይልቅ መንግሥት ነው፡፡
መሆን ያለበት ተቋሙ በመንግሥት ስር እንዳለ የሚያድግበትን አዲስ መንገድ መፍጠር ነበር፡፡ አሁንም ሊሆን የሚገባው እሱ ነው፡፡ ደጋግሜ በተለያዩ መድረኮች እንደገለጽኩት አየር መንገድ በዚህ አካሄድ ነው ስኬታማ የሆነው፡፡ መንግሥት ተመሳሳይ እርምጃ ለኢትዮ ቴሌኮም ሳያደርግ ለውጭ ተቋም ለመሸጥ መወሰኑ አግባብ አይደለም፡፡
እንደዚህ ዓይነት ተቋሞቻቸውን የሸጡ አገሮች ዛሬ እያለቀሱ ናቸው ያሉት፡፡ ያንን የሚናገር አካል ግን አናይም፡፡ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በዚህ ሒደት ምን እንደተፈጠረ፣ ምን ምን እናዳተረፈ፣ ማን እንደከሰረ በቂ ጥናት አልተደረገም፤ በቂ ውይይትም አልተደረገም፡፡
ተቋም መሸጥ የሥልጣኔ ማሳያ አይደለም፡፡ ፈረንጆቹ ተቋማችንን ፕራይቬታይዝ አድርገናል የሚሉት እርስ በርሳቸው እየተሻሻጡ ነው፡፡ እነሱ እኛን ተቋማቶቻችሁን ሽጡልን እንደሚሉት የአሜሪካ አንድ ተቋም ለሩሲያ ምን አይሸጥም? ይህን በፍፁም አያደርጉትም፡፡ እነሱ የማያደርጉትን ነው እኛን አድርጉ በሚል ሙግት ውስጥ የገቡት፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮ ቴሌኮምን ለመሸጥ ብዙ ርቀት እንደሄደ አውቃለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ግን እርምጃውን ቆም ብሎ ማሰብ አለበት ባይ ነኝ፡፡ ብዙዎቻችን ተቋሙ አይሸጥ የምንልበትን ምክንያት መንግሥት ቆም ብሎ በአግባቡ ቢያሰላስለው፤ በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይም በቂ ውይይቶችና ክርክሮች ቢደረጉ ኢትዮጵያ ትጠቀማለች፡፡ አሁንም ቆም ብለን እንድናስብ አሳስባለሁ፡፡
#ሲራራ-ቢዝነስ|ኢኮኖሚ!
ኅዳር 14/2013