Connect with us

ቁጠባን ለልጆችዎ ያስተምሩ

ቁጠባን ለልጆችዎ ያስተምሩ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ቁጠባን ለልጆችዎ ያስተምሩ

ቁጠባን ለልጆችዎ ያስተምሩ

ቁጠባ ሀብት ማፍሪያና አስተማማኝ የገንዘብ አቅም መገንቢያ መንገዶች አንዱ ነው፡፡ አብዛኞቻችን ግን ስለቁጠባ ገና አልገባንም፣ ወይም የቁጠባን ጥቅም የተረዳነው ዘግይተን በረጅም ሂደት በመውደቅ መነሳት ካገኘነው የህይወት ተሞክሮ ነው፡፡ በትምህርት ቤትም ስለቁጠባ በአግባቡ ትምህርት አላገኘንም፡፡

መጪው ትውልድ ግን ስለቁጠባ በአግባቡ ግንዛቤ ያለው እንዲሆን ልጆቻችንን ገና በለጋ እድሜያቸው ስለቁጠባ ጠቀሜታ እያስተማርን ማሳደግ ተገቢ ነው፡፡

የሚከተሉት ቁምነገሮች ልጆችን ስለቁጠባ ለማስተማር ይረዳሉ፡

  1. አነስተኛ የቁጠባ ሳጥን (ባንክ) ያዘጋጁላቸው

አነስተኛ የቁጠባ ሳጥን አዘጋጅቶ በመስጠት ልጆችዎ ሳጥኑን በሳንቲሞችና በብር እንዲሞሉ ያበረታቷቸው፡፡ ሳጥኑ ለወደፊታቸው የሚሆን ገንዘብ የሚያጠራቅሙበት እንደሆነና ይበልጥ ሲቆጥቡ ገንዘባቸው እየበዛ እንደሚሄድ ያስረዷቸው፡፡ ይህም ልጆች እየቆጠቡ የቁጠባን ጠቀሜታ በቀላሉ እንዲማሩ ይረዳል፡፡

  1.   የቁጠባ ሂሳብ ይክፈቱላቸው

 ሳጥኑ ሲሞላላቸው ወደ ባንክ ወስደው የቁጠባ ሂሳብ ይክፈቱላቸው፡፡

ምንያህል ገንዘብ መቆጠብ እንደቻሉ እንዲረዱ ገንዘቡን እራሳቸው እንዲቆጥሩ ያድርጉ፡፡ ከባንክ ስለሚያገኙት ወለድም ያስረዱዋቸው፡፡ ልጆቹ ገንዘባቸውን ካልነኩት እየበዛ እንደሚሄድ ማወቃቸው ትልቅ ተነሳሽነትን ይፈጥርላቸዋል፡፡

  1.   እንዲገዛላቸው የሚፈልጉትን  በቁጠባ እንዲገዙ ያበረታቱ

 ልጆችዎ እንዲገዙላቸው የሚፈልጉት ነገር ሲኖር መግዣውን ገንዘብ ቆጥበው ማግኘት እንዳለባቸው ያስረዷቸው፡፡ ለእያንዳንዱ እንዲገዛላቸው ለሚፈልጓቸው ነገሮች ገንዘብ ማጠራቀሚያ ጠርሙሶች ወይም ሌላ የውስጡን የሚያሳይ ማጠራቀሚያ ያዘጋጁላቸው፡፡ የሚፈልጉትን ነገር መግዣ እስኪሞላ ድረስ በየሳምንቱ ትንሽ ትንሽ ገንዘብ እየሰጡ እንዲቆጥቡ ያድርጉ፡፡

  1.   አርአያ ይሁኗቸው

ልጆችዎ እርስዎን አርአያ ስለሚያደርጉ እየቆጠቡ ያስተምሯቸው፡፡ እርስዎ ከሚያገኙት ገቢ ላይ የተወሰነውን እየቀነሱ በመቆጠብ ለወደፊቱ እንዴት እንደሚዘጋጁ ደጋግመው ያስረዷቸው፡፡ ለምን እና እንዴት ለወደፊት የኮሌጅ ትምህርታቸው እንደሚቆጥቡላቸው ለልጆችዎ ያሳውቁ፡፡

  1.   ከልጆችዎ ጋር ይወያዩ

ስለገንዘብ እና ስለቁጠባ ጠቀሜታ ከልጆች ጋር መወያየት ወላጆች ሊያደርጉት የሚገባ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ተግባር ነው፡፡ ስለገንዘብ ማውራት አስፈሪ ወይም ነውር ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ ስለገንዘብ የሚደረጉ ውይይቶችን ልጆችዎን እንደማስተማሪያ አጋጣሚ ይጠቀሙበት፡፡ ልጆች ለሚያነሷቸው እንደ “ሀብታም ነን ወይ?” ለመሳሰሉ ግልፅ ጥያቄዎች ወላጆች በአግባቡ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቤተሰብን በአግባቡ ለማስተዳደር ወላጆች ምን ያህል ጠንከረው እንደሚሠሩ እና ገንዘብ ሀላፊነት በተሞላበት መልኩ ወጪ መደረግ እንዳለበት ትኩረት ሰጥቶ ለልጆች በማስረዳት መልስ መስጠት ይቻላል፡፡

ቅድሚያ መሟላት ባለባቸው መሠረታዊ ፍላጎቶች እና በሌሎች አንገብጋቢ ያልሆኑ ፍላጎቶች መካከል ያለውን ልዩነት ለልጆችዎ ያስረዱ፡፡ ሁሌም ስለገንዘብ እና መቆጠብ ስለሚያስችሉ አዳዲስ መንገዶች ለመወያየት ዝግጁ መሆንዎን ለልጆችዎ ይንገሯቸው፡፡ ለምን ዓላማ ገንዘብ መቆጠብ እንደሚፈልጉ እንዲሁም የወደፊት ኑሯቸው ምን እንዲመስል እንደሚፈልጉ ልጆችዎን ይጠይቁ፡፡

መልካም መልካም ጥያቄዎችን በመጠየቅ ልጆችዎ ዘላቂነት ባለው ነገር ላይ እንዲያተኩሩና ከገንዘብ ጋር ያላቸው ግንኙነትም በበጎ መልኩ እነዲገነባ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ሁሌም በግልጽነት ለመወያየት ዝግጁነትዎን ሲያዩ ልጆች ገንዘብን በተመለከተ የበለጠ ለመጠየቅና ለመማር ተነሳሽነታቸው እየጨመረ ይሄዳል፡፡(የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top