በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የአየር ትራንስፖርት መስመር ዝርጋታ ስልጠና እየተሰጠ ነው
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በራሱ የሰው ሀይል ለአየር ትራንስፖርቱ ወሳኝ የሆነውን የአየር መስመር ዝርጋታ ለመስራት የሚያስችል (flight procedural design) ስልጠና ጥቅምት 23 ቀን 2013 መስጠት ጀመረ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ስልጠናውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ስልጠናውን በአፍሪካ በራሳቸው የሰው ሀይል የሚያሰለጥኑ የሲቪል አቪዬሽን ተቋማት አለመኖራቸው ገልፀው በምዕራብ አፍሪካ ባለሙያዎችን ከውጭ ሀገራት በማስመጣት ስልጠናው ይሰጥ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአለምአቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ጋር በመነጋገር ስልጠናውን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንዲሰጥ ፈቃድ ለማግኘት እንደሚጥር የገለፁ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን ከዚህ ቀደም በውጭ ሀገራት ሲሰጡ የነበሩ ሌሎች ስልጠናዎችንም በሀገር ውስጥ ለመስጠት ጥረት እንደሚደረግ አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ከ1944 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ስልጠና ማእከል ወደ አካዳሚነት (አዳሪ ትምህርት ቤት) ለማሳደግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም እየተገነባ ያለውና በቅርብ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው አዲሱ ህንፃ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው አበክረው ገልፀዋል፡፡
የአየር ክልል ማኔጅመንት ዳይሬክተርና ስልጠናውን አዘጋጅተው በመስጠት ላይ የሚገኙት አቶ መንግስቱ ንጉሴ በበኩላቸው እንደተናገሩት የበረራ ፕሮሲጀራል ዲዛይን ስልጠና በሲንጋፖር ለምሳሌ እስከ 18 ሺህ ዶላር ለአንድ ሰው የሚያስከፍል ከመሆኑ አንፃር ይህን ስልጠና በራሳችን ጥረት ሀገር ውስጥ መስጠት መጀመራችን ለሀገራችን ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
“ዋና አላማችን ተተኪ ማፍራት ነው” ያሉት አቶ መንግስቱ “ለአንድ ወር በሚቆየው ስልጠና ሰልጣኖች ተግባራዊ ልምምድ ስለሚያደርጉ አዳዲስ የበረራ መስመሮችን የመዘርጋት ብቃት ይኖራቸዋል”
ስልጠናው የሚሰጠው ለአንድ ወር ሲሆን ስምንት የመስሪያ ቤቱ ባለሙያዎችም በስልጠናው ላይ ተካትተዋል፡፡(ትራንስፖርት ሚ/ር)