Connect with us

የትግራይ ሕዝብና ትህነግ ለየቅል ናቸው !!

የትግራይ ሕዝብና ትህነግ ለየቅል ናቸው !! ( ኃይሌ ተስፋዬ )
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የትግራይ ሕዝብና ትህነግ ለየቅል ናቸው !!

የትግራይ ሕዝብና ትህነግ ለየቅል ናቸው !!

 ( ኃይሌ ተስፋዬ )

 

ትህነግ ከ1968ቱ ማኑፌስቶዋ ጀምሮ የአማራን ህዝብ በጠላትነት በመፈረጅ፣ ታሪካዊ ጠላቷ ማድረጓ ይታወቃል። ወደ ከተማ ከመጣችም በኋላ በዚህ ህዝብ ላይ የሀሰት ትርክቶችን በመፈብረክ የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ወንድማማች ብሔሮች ጋር ተከባብሮ እንዳይኖር ስውር የሆኑ የጥቃት ስልቶቿን ለ27 ዓመታት ስትፈጽም ኖራለች ።

ይህ ግብሯ ኢትዮጵያ የሚለውን ምስል ለመናድ ከተጠቀመችባቸው ከፋፍለህና አጋጭተህ ግዛው መርህ የቀዳችው የውሾች ፖለቲካዋ (The Dog Politics) ነው።

ይህች አደገኛ የማፊያ ቡድን ኢትዮጵያ የሚለውን ምስል ከካደችና በእርሷ (በኢትዮጵያ) ላይ ከተነሳች አያሌ አስርት ዓመታት አልፈዋል። በዚያ ሰሞን ስልጣኗን በፖለቲካ ብልጫ ከተነጠቀች በኋላም፥ ወደ አራት ኪሎ ለመመለስ መጣር፣ ወይም “ዲፋክቶ እስቴት መመስረት”፣ አሊያም ተወዳጁን የትግራይን ህዝብ ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ በመነጠል ደም በማቃባት አገሪቱን እንደ የመን እና ሶሪያ የማድረግ ሀሳብ ይዛ ነው የተንቀሳቀሰችው።

ለዚህ አላማዋም ማስፈጸሚያም የብዙ ንጹሃንን ደም በእጅ አዙር በማፍሰስ፣ የህዝብን ሰላምና የመንግስትን መዋቅር በመረበሽ፥ ለማፈራረስ መሞከር ነበር።

ትህነግ በአሁን ሰዓት እንደምናየው ከእነዚህ ምርጫዎቿ ውስጥ ራሷን አንዱ ላይ የጣለች ትመስላለች። ይኸውም የትግራይን ህዝብ በሌሎቹ ወንድሞቹ ላይ በማነሳሳት ወደ ጦርነት ማስገባት ነው። ይኹንና ይህ መላ ምት ሊሳካ አይችልም።

ምክንያቱም አሁንም እኔ የማምነው የትግራይ ህዝብና ወያኔ ለየቅል ናቸው ብዬ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ አሁን የገጠመችው ጦርነት ከትግራይ ህዝብ ጋር ሳይሆን፥ ከማፊያ ቡድኗ እና ከምትመራው ነፍሰ ገዳይ ቡድን ጋር ነው ።

ይህች መሠሪ ቡድን፥ መደፈር የማይገባውንና የእኛ የኢትዮጵያውያን ምልክትና የሀገር ዘብ የሆነውን መከላከያ ሠራዊታችንን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ቆጥራ፤ በሀገር ላይ ጥቃት ፈጽማለች። ይህም አደገኛ አካሄዷ የትህነግን የስልጣን ጥመኝነት ፍንትው አድርጎ ከማሳየቱም በላይ፥ የሰው ልጆች ሞትና እንግልት ለእርሷ ከዕቁብ የማትቆጥረው ጉዳይ እንደሆነ ያሳያል።

ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ኾነን አገራችንን የምንጠብቅበት፣ኢትዮጵያን ሲከፋፍሉ፣ ሲያባሉ፣ ሲያደሙ የነበሩና አሁንም ያሉ የሴረኞችን ቡድን በመታገል፥ አንድነታችንንና ሰላማችንን ማስጠበቅ ይኖርብናል።

ይህንን የምናደርገው ኢትየጵያን ስለምንወድ ብቻ ነው። ሀገር ማለት ሰው እንጅ ተራራና ሜዳ እንዳልሆነ እንረዳለን። በመሆኑም ኢትዮጵያ ማለት ልጆቻችን፣ እህቶቻችን፣ ኣባቶቻችንና እናቶቻችን ማለት ናቸው። እነዚህ ሁሉ በሰላም እንዲኖሩልን ስለምንፈልግ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር አንተባበርም።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር  !!     

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top