Connect with us

ቅዱስ ሲኖዶስ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጅምላ ጭፍጨፋ አወገዘ

ቅዱስ ሲኖዶስ: በምዕራብ ወለጋ፣ በጉራፈርዳ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጅምላ ጭፍጨፋ አወገዘ
Photo: Social Media

ዜና

ቅዱስ ሲኖዶስ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጅምላ ጭፍጨፋ አወገዘ

ቅዱስ ሲኖዶስ: በምዕራብ ወለጋ፣ በጉራፈርዳ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጅምላ ጭፍጨፋ አወገዘ

• መንግሥት፥ ለዜጐች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ፣ ወንጀለኞችንም ለፍርድ እንዲያቀርብ አሳሰበ፤

በአገራችን ኢትዮጵያ በምዕራብ ወለጋ እና በጉራፈርዳ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉምዝ በግፍ የተገደሉ ዜጐች አስመልክቶ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ስለ ዓለማት አፈጣጠር ስለ ሰው ዘር አመጣጥ ስለ ኃጢአት እና የሥቃይ ኑሮ አጀማመር፣ እግዚአብሔር ከሰው ዘር ጋራ ስላለው ግንኙነት በሚናገረው በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ፣ ምዕራፍ አንድ ቁጥር አንድ ላይ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ በዚያን ጊዜ ምድር ባዶ ነበረች ይላል፡፡

ከዚኽም ጋራ ለሰው ልጆች በእጅጉ አስፈላጊ የኾነውን ብርሃን፣ “ብርሃን ይኹን” በማለት ብርሃንን ከጨለማ ለየ፡፡ በዚኽም መሠረት፣ በብርሃን በሞላው ዓለም ይኖር ዘንድ፣ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ እና በራሱ አምሳያ ፈጠረው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከፈጠረው በኋላ፣ ብዙ ተባዙ ዘራችኹ ምድርን ይሙላ፤ ምድርም በቁጥጥራችኹ ሥር ትኹን፤ በሚል የሰው ልጆች ምንም ዓይነት መልክ ይኑረን፣ የትኛውንም ቋንቋ እንናገር፣ እግዚአብሔር በፈጠረልን ምድር በየትኛውም አቅጣጫ ተከብረንና ተከባብረን እንድንኖር ምድርንም እንድናለማ እግዚአብሔር ፈጥሮናል፤ ማለትም የሰው ልጆች በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር፣ እንግዶች እንጂ ከመካከላችን አንድም ባለአገር እንደሌለ ሊኖርም እንደማይችል ከላይ የተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል፡፡

እውነታው ይህ ኹኖ ሳለ፣ የሰው ልጅ በእጅጉ በተሳሳተ አመለካከት ውስጥ በመግባት፣ ይኼ የእኛ ያኛው የእናንተ አካባቢ እየተባባልን የመለያየት ኹሉ መሠረት የኾነውን የጠላትን መንፈስ እና አሠራር በመከተል እርስ በርሳችን በመጠላላት ወንድም ወንድሙን ሲያሳድድ እርስ በርሳችን እየተጠፋፋን እንገኛለን፡፡

በቅርቡ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም.፣ በኦሮምያ ክልል በምዕራብ ወለጋ እና ጉራፈርዳ እንዲሁም በቤንሻንጉል ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት የሌላቸው፣ ማልደው በመነሣት አምሽተው በመግባት ምድርን ቆፍረው እና አርሰው፣ ዘርተው እና አጭደው፣ በድካም ኑሮአቸውን የሚገፉ ንፁሐን ዜጐች ሽማግሌዎች፣ ሴቶች እና ሕፃናት ጭምር ሳይቀሩ፣ ጅምላ ጥፍጨፋ በማካሔድ ሕይወታቸው እንዲያልፍ መደረጉ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤው በዓመታዊ ስብሰባ ላይ እያለ የሰማው ሲኾን፣ ቅዱስ ሲኖዶሱንና ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ያሳዘነ ኢሰብአዊ ድርጊት በመኾኑ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት አውግዟል፡፡

መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤ ከላይ በመግቢያው እንደገለጽነው እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ፤ ሰውንም በራሱ መልክ አና አምሳያ ፈጠረው፤ እንዳለው ሁሉ፣ የሰው ልጆች በዚህ ዓለም ስንኖር፣ ሁላችን የእግዚአብሔር ፍጥረት መኾናችንን ተገንዝበን ሐሳባችንም ኾነ ተግባራችን እንደ እግዚብሔር ሐሳብ ኾኖ ሁላችን የዚህ ዓለም እንግዶች መኾናችን ተገንዝበን በወንድማማችነትና በፍቅር በአንድነት በመተሳሰብ እግዚአብሔር ፈጥሮ በሰጠን ምድር ላይ በፍቅር ልንኖር ይገባል፡፡

በርግጥ እንደ ሥጋ ለባሽነታችን በተለያየ አካባቢ ተወልደን እንደማደጋችን የተለያየ መልክ ሊኖረን የተለያየ ቋንቋ ልንናገር የተለያየ ባሕልና ሥርዓት ሊኖረን የእኔ የምንለው የራስ አመለካከትም ሊኖረን ይችላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ፣ ሌላው ከእግዚአብሔር የተሰጠን የጸጋ ስጦታ እንጂ ለመለያየት ምክንያት ሊኾነን አይገባም፡፡

ስለዚህ፣ አላስፈላጊ በኾነ ምክንያት በግፍ ለተገደሉት እና ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን፣ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ልባዊ ሐዘናችንን እየገለጽን፣ ዳግሞ እንዲህ ዓይነት ኢሰብአዊ ድርጊት እንዳይፈጸም፣ መንግሥት ለዜጐች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ፣ ወንጀለኞችንም ለፍርድ እንዲያቀርብ እያሳሰብን፣ መላው ኢትዮጵያውያን ልጆቻችንም፣ ለጋራ ሰላም እና አንድነት እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

የሞቱ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top