አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን በአገሪቱ የዴሞክራሲ አተገባበር ደስተኛ አለመሆናቸው ተጠቆመ
አብዛኞቹ ማለትም 54 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ዴሞክራሲ እየተተገበረ ባለበት መንገድ ደስተኞች አለመሆናቸውን፣ የአፍሮ ባሮሜትር ጥናት ጠቆመ፡፡ ግማሽ ያህሉ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ‹‹በብዙ ችግር ውስጥ ያለ ዴሞክራሲ›› ወይም ‹‹ምንም ዓይነት ዴሞክራሲ የሌለባት›› አድርገው እንደሚመለከቱ ጥናቱ አመላክቷል፡፡
ይህ የጥናት ውጤት ይፋ የሆነው ዓርብ ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በአብኮን የአማካሪ ድርጅት የሚመራው የኢትዮጵያ አፍሮባሮ ሜትር ቡድን ‹‹እጅግ የሚበዙ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲን ይደግፋሉ፣ ተጠያቂነት ያለው አስተዳደርን ይሻሉ›› በሚል መግለጫ በተሰጠበት ወቅት ነው፡፡
ምንም እንኳን በጥናቱ የተካተቱ 2,400 ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አተገባበር ላይ ደስተኞች ባይሆኑም፣ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን (90 በመቶ) ከማንኛውም መንግሥታዊ ሥርዓት ይልቅ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንደሚመርጡ ጥናቱ አመላክቷል፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ ሥርዓቶችን ማለትም የአንድ ፓርቲ አገዛዝን፣ ወታደራዊ መንግሥትን፣ እንዲሁም የአንድ ሰው አገዛዝን እንደማይፈልጉም ጥናቱ አስታውቋል፡፡
የመንግሥታቸውን ባህሪና አሠራር በተመለከተ 65 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጽያውያን፣ መንግሥት ዜጎችን ሳያማክር ውሳኔዎችን በራሱ ከሚወስን ይልቅ ተጠያቂ የሆነ መንግሥትና ሥርዓት እንዲኖር ፍላጎት እንዳላቸው በጥናቱ የተመላከተ ሲሆን፣ ከአሥር ኢትዮጵያውያን ሰባቱ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማው ቁጥጥርና ክትትል እንዲደረግበት እንደሚሹ ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡
ከዚህ ቀደም በነሐሴ ወር በዚሁ ተቋም ይፋ በተደረገ የጥናት ውጤት መሠረት ኢትዮጵያውያን የአገሪቱ ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል፣ የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ እንዲበዛና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ቆይታ በሁለት የሥራ ዘመን እንዲገደብ ፍላጎት እንዳላቸው ባከናወነው ጥናት ማግኘቱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ሆኖም የመሬት ባለቤትነትን ለዜጎች ስለመስጠት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ስለማቋቋም፣ በአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ መሀል ላይ ያለውን የኮከብ ዓርማ በተመለከተና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁኔታ ላይ ኢትዮጵያውያን ያላቸው አቋም የተከፋፈለ መሆኑን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡
ዋና ጽሕፈት ቤቱን በጋና ርዕሰ መዲና አክራ ያደረገው አፍሮባሮሜትር በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሠሩ የጥናትና የምርምር ተቋማት ዋነኛው ነው፡፡ ተቋሙ አፍሪካ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ገለልተኛ የሆነ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በዋናነትም በዴሞክራሲ፣ በአስተዳደርና በኑሮ ጥራት ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን በማጥናትና በማጠናቀር ለሚመለከታቸው አካላት የሚያቀርብ ነው፡፡
(ነአምን አሸናፊ ~ ሪፖርተር)