Connect with us

የኦሮማራ መድረክ ወደ ብሄራዊ መድረክነት አደገ

የኦሮማራ መድረክ ወደ ብሄራዊ መድረክነት አደገ
Ethiopian press agency

ዜና

የኦሮማራ መድረክ ወደ ብሄራዊ መድረክነት አደገ

የኦሮማራ መድረክ ወደ ብሄራዊ መድረክነት አደገ

ከአንድ አመት በፊት የተጀመረው የኦሮ-ማራ መድረክ ወደ ብሄራዊ መድረክነት ማደጉ ተገለጸ ። መድረኩ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠርና የውይይትን ባህል ለማዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቆመ።

በአዳማ ከተማ ትናንት መድረኩ ሲከፈት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ሊንጮ ለታ፣ ከዚህ ቀደም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተነሳውን ውዝግብ ተከትሎ ችግሩን ለማርገብ መድረኩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የዛሬ ዓመት አካባቢ መጀመሩት አስታውሰዋል።

መድረኩ ወደ ብሄራዊ መድረክነት መሸጋገሩን አስታውቀው፣ መድረኩ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ ተግዳሮት የሆነውን ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት የሚያስችል እንደሚሆን አመልክተዋል ። 

የችግሩ መሰረታዊ ምንጭ የዲሞክራሲ ባህላችን አለማደግ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሌንጮ ፣ ለአንድ ዓመት ያህል የአማራና የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በአገራዊና በክልላዊ ጉዳዮች ሲወያዩ መቆየታቸው አስታውቀዋል። በዚህም በተለያዩ ጉዳይ ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል ። ይህም በሰከነ መንፈስ የመነጋገር እና የዲሞክራሲን ባህልእየተለማመድን ለመሆናችን ማሳያ ነው ብለዋል። 

አገር አቀፍና ሁሉንም ቡድኖች ያሳተፈው የውይይት መድረኩ ለፖለቲካ ችግሮችን ዘላቂ መፍትሄ ያስገኛል ተብሎ እንደሚታመን ገልጸው፣ በተለይ ምን አይነት ኢትዮጵያ ናት የምታግባባን እና ልታስማማን የምትችለው በሚለው ጉዳይ ላይ ስምምነት ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል። 

የመድረኩ አወያይ ዶክተር ዲማ ነጋዎ በበኩላቸው፤ የኦሮሞና የአማራ የፖለቲካ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም በ10 ጉዳዮች ላይ ስምምነቶች መደረሳቸውን አመልክተው፣ በሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ሽማግሌዎች ተወስኖ የቆየው የወይይት መድረክ ወደ አገራዊ መድረክነት እንዲሸጋገር መደረጉን አስታውቀዋል። ይህም በአገራችንን ያለውን የፖለቲካ የውይይት ባህል ለማዳበርና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል። 

የመድረኩ ሌላኛው አወያይ ዶክተር ገበያው ጥሩነህ በበኩላቸው፣ የአሮሞና የአማራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጀመሩት ውይይት ፍሬ አፍርቶ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ደርሰዋል ። የዚህ ፍሬ አንዱ ማሳያም በሁለቱ ወገኖች ተወስኖ የነበረው ውይይት ወደ አገራዊ ውይይት ማደግ መቻሉ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመካሄድ ላይ ያለው አገራዊ የፖለቲካ ሽግግርና የለውጥ ሂደት መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በአገራዊ የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር መድረኮች በመካሄድ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። 

በአማራና በኦሮሞ ብሄሮች ምሁራንና ተጋባዥ እንግዶች፣ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ የሁለቱ ህዝቦች ሁሉን አቀፍ ግንኙነቶች የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ውይይቶችና ጉባኤዎችን ከታህሳስ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ ማካሄዳቸውን ጠቁመዋል። 

በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች በክልላዊና አገራዊ ነባራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምክክር ሲያደርጉ ቆይተው፣ በበርካታ ፖለቲካዊ አቋሞች ላይ የጋራ መግባባት በመድረስ መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም ታሪካዊ ስምምነት መፈራረማቸውን አመልክተዋል ። 

በአዳማ ከተማ በተካሄደው አገራዊ መድረክም በአገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ምሁራን፤ ታዋቂ ሰዎች፣ የሲቪል ማህበራት፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የብሄር ብሄረሰቦች ተወካዮች ተሳትፈዋል። ይኸው አገራዊ የምክክር መድረክም በቀጣይ ባህር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ ዕቅድ መያዙም በወቅቱ ተገልጿል።

በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑት የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ ማህመድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች የአገርን ችግር ለመፍታት ያለመ ውይይት ማድረጋቸው ጥሩ ጅምር መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ወደ ህዝቡ ወርዶ ፍሬ እንዲያፈራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ውይይቱ የሰላም መታጣት ባለባቸውና ግጭቶች በሚከሰቱባቸው አካባቢዎች ተወያይቶና ችግሩን ለይቶ መፍትሄ ለመስጠት መንገድ ይጠርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተው፣ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከራሳቸውን ፍላጎት ይልቅ ለህዝብ ጥቅም አስበው ህዝብ እንዳይጋጭ የማድረግ አላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል። ውይይቱ ለዚህ ስንቅ እንደሚሆናቸው ጠቁመዋል። 

የሀይማኖት አባቶች ግጭት እንዳይከሰት፤ ከተከሰተም በእርቅ እንዲፈታና በህዝቦች መካካል ወንድማማችንትን፣ መተባበርና አንድነትን በማስረጽ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

“ በእነዚህ እሴቶች ዙሪያ በቤተ ክርስቲያናት፣ በመስኪዶች ትምህርቶች ቢሰጡም ሰው የአምላኩን ቃል ሰምቶ ቢተገብር ኖሮ ሰዎች አይፈናቀሉም፣ የሰው ህይወት አይጠፋም ግጭቶችም አይኖርም። ይህም ሆኖ በአገሪቱ በስነ ምግባር የታነጸ መልካም ዜጋና አንድነትን በሚሸረሽሩ ጉዳዮች የማይሳተፍ አማኝ ለማፍራት የማስተማር ስራቸውን አጠና ከረው ሊቀጥሉ ይገባል”ብለዋል ።

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2013)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top