Connect with us

የሕግ ባለሙያው ጌትነት የሻነህ አረፈ

የሕግ ባለሙያው ጌትነት የሻነህ አረፈ
Photo: Social media

ዜና

የሕግ ባለሙያው ጌትነት የሻነህ አረፈ

የሕግ ባለሙያው ጌትነት የሻነህ አረፈ

 (የኋላሸት ዘርይሁን እንደፃፈው)

“ጌትነትን ለመጨረሻ ጊዜ በስልክ አግኝቼ ያወራሁት ሰኞ ዕለት ልክ 6፡00 ሰዓት ላይ ነበር። 

6:20 ገደማ ራሱን መቆጣጠር ተስኖት ቦሌ አካባቢ በአንድ ጥግ  ድንጋይ ላይ ቁጭ አለ ። እንደምንም ብሎ ለሁለት ልጆቹ እናት ደወለ።”እያስመለሰኝ እና እየደከመኝ ነው ቶሎ ድረሺልኝ” ይላታል፤ እሷም እየከነፈች ከተባለው ቦታ ስትደርስ ጠዋት ከቤት ሲወጣ ልጆቹን በተኙበት ስሞ፤ እንደሳማቸውም ፤እንደሚወዳቸውም እንድትነግርለት አደራ አደራ ያላትን ጌትሽን እራሱን መቆጣጠር ተስኖት ከተቀመጠባት ድንጋይ ላይ ሸርተት ብሎ ታገኘዋለች ።

 “ልቤን እየወጋኝ ነው።” እየመላለሳ የሚላት ይኸንኑ ብቻ ነበር… ቤተሰቦቹ በአፋጣኝ ሰሚት ሚካኤል አሃዱ ሬዲዮ አካባቢ ወደሚገኘው ዚንዱንግ የልብ ህክምና ይዘውት ያቀናሉ። ከምርመራው በኋላ የሰሙት ውጤት ግን እጅግ አስደንጋጭ ነበር።

 የአዕምሮ ውስጥ ደም መርጋት (ስትሮክ) መሆኑን ይገልፁላቸዋል። የሆስፒታሉ ባለሞያዎች በሙሉ ጌትነትን ለማትረፍ የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።

ስትሮኩ ልቡ ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ 65 በመቶ የሚሆነውን የአእምሮ ክፍል ላይ ጉዳት በማድረሱ በምንም መልኩ   ሊተርፍ አይችልም ይሏቸዋል። “ጠዋት በሰላም ከቤቱ የወጣውን አባታቸውን  ምን ሆነ ብዬ ልንገራቸው? አባታቸውን እኮ በአንድ ስም ብቻ አይደለም የሚጠሩት፤ ብዙ ስም ነው ያለው። 

አንዲት ቀን እንኳን በቁጣ ተናግሯቸው አያውቅም …እባክህን ከልጆቹ ጋር ዳግመኛ እንዲገናኝ  ፀልይለት?”  ጌትነትን ልጠይቀው በሄድኩ ጊዜ ባለቤቱ እየደጋገመች የምትለኝ ይኸንኑ ብቻ ነበር …

አልሆነም፤ በመጨረሻም ጌትነት እስከወዲያኛው ይኸቺን ዓለም ተሰናበተ።

የአእምሮ ውስጥ የደም መርጋት (ስትሮክ) ከዚህ ቀደም በቅርቡ ወደ ባህርዳር አቅንቶ የእንቦጭ አረምን ሊዋጋ የሄደውን የሁለት ልጆች አባት የሆነውን ጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋምን ያሳጣን ይኸው ድምፅ አልባው ገዳይ ነው።

ጥቂት_ስለጌትነት

የአእምሯዊ ንብረት(intellectual property) ህጎች አዋቂው አቶ ጌትነት የሻነህ አረፈ።

ጌትነት በሀገራችን የአእምሯዊ ንብረት ህጎችን በተለይ( Copyright & Neighbouring rights)  አዋጆችን  እንዲወጡ፣ 

የወጡቱንም ሕጎች በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆኑ፣ 

የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር( Copyright & Neighbouring rights Collective Management Society of Ethiopia)  እንዲቋቋም፣  ከቅጅና ተዛማጅ መብቶች ተጠቃሚዎች ተሰብስቦ ለባለ መብቶች (Copyright & Neighbouring Right Holder’s or owner’s)  የሚከፋፈለው የሮያሊቲ( Royalty System) ስርዓት አሰባሰብ እና አከፋፈል  እንዲዘረጋ የተጋ፣ ቀና፣ ላመነበትም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ ሰው ነበር።

አንባቢ ፣ተመራማሪ፣ አስተማሪ፣ ያለ ስስት እውቀቱን የሚያካፍል ነበር።

ጌትነት በቅጅ መብት ኢንዱስትሪው( Copyright industries) በርካታ ጥናቶችን የሰራ፣ ልምዱና ዕውቀቱ ለህግ አካላት፣ ለሚዲያ ባለሙያዎችን፣ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች  በአእሙሯዊ ንብረት ምንነትና ጥቅም፣ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሚገባው ክብር እንዲያገኝ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ያለ ስስት ግዜውንና እውቀቱን መስዋእት ያደረገ የሕግ ባለሙያ ነበር።

የጌትነት  ቀብር ስነ ስርዓት በዛሬው ዕለት ከቀኑ በ6:00 ሰዓት ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በአስኮ ገብርኤል ይፈፀማል።”

ከአዘጋጁ:-  የድሬቲዩብ ዝግጅት ክፍል በሕግ ባለሙያው አቶ ጌትነት የሻነህ ድንገተኛ ሞት የተሰማውን ልባዊ ሐዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቹና ለወዳጆቹ መፅናናትን ይመኛል!

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top