Connect with us

የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች የታሪፍ ማስተካከያ ካልተደረገ ሥራ እንደሚያቆሙ አስጠነቀቁ

የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች የታሪፍ ማስተካከያ ካልተደረገ ሥራ እንደሚያቆሙ አስጠነቀቁ
Ethiopian Reporter

ኢኮኖሚ

የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች የታሪፍ ማስተካከያ ካልተደረገ ሥራ እንደሚያቆሙ አስጠነቀቁ

የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች የታሪፍ ማስተካከያ ካልተደረገ ሥራ እንደሚያቆሙ አስጠነቀቁ

የኢትዮጵያ የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች ማኅበር አባላት፣ ለነዳጅ አቅርቦት የሚከፈለው ዝቅተኛ መሆንና የተሽከርካሪ ወጪዎች አለመጣጣም ለከፍተኛ ኪሣራ ከመዳረግ አልፎ በዘርፉ ለመቆየት የህልውና ሥጋት እየሆነባቸው በመምጣቱ ምክንያት፣ መንግሥት ተገቢውን የታሪፍ ማስተካከያ በማድረግ ካልታደጋቸው፣ ከጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ለማቆም እንደሚገደዱ አስጠነቀቁ፡፡

የማኅበሩ አባላት ማክሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. በተጠራው ስብሰባ የቦርድ አመራሮችና አባላት በወሰኑት መሠረት፣ መንግሥት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተገቢውን ማስተካከያ ካላደረገ ሥራ ለማቆም እንደሚገደዱ በአንድ ድምፅ ወስነዋል፡፡ ይህንኑ ውሳኔም የመንግሥት አካላት እንዲያውቁት ብለዋል፡፡

የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፀጋ አሳመረ እንዳስታወቁት፣ በአሁኑ ወቅት 3,500 ቦቴ ተሽከርካሪዎች ያሏቸው ባለንብረቶች፣ በ30 የነዳጅ ኩባንያዎች ውስጥ ተመዝግበው፣ በነዳጅ ማጓጓዝና ሥርጭት ሥራ ላይ እየተሳተፉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በየጊዜው እየናረ በመጣው የተሽከርካሪዎችና የመለዋወጫ ዋጋ፣ በተለይም የጎማና የባትሪ ዋጋ መናር፣ በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት ሳቢያ፣ እንዲሁም የብድር ወለድ ምጣኔ ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት ፈተና ውስጥ መውደቃቸውን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡ 

ማኅበሩ አባላቱ የገጠማቸውን ፈተና በማስመልከት ጥናት አሠርቶ ለመንግሥት ቢያቀርብም፣ ምላሽ እንዳላገኘ አቶ ፀጋ ከሌሎች የቦርድ አባላት ጋር በመሆን አብራርተዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የተደረገ የታሪፍ ክለሳ እየተተገበረ ቢሆንም፣ ታሪፉ በ2008 ዓ.ም. ተጠንቶና ለመንግሥት በመፍትሔነት የቀረበውን ሳይንሳዊ መንገድ የተከተለ አካሄድ በመተው፣ ለአንድ ጉዞ በሚከፈለው የአገልግሎት ክፍያ ላይ ጭማሪ በማድረግ መቅረቡ ተገቢነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡

በአንድ ጉዞ በሚከፈለው 41 ሺሕ ብር የአገልግሎት ክፍያ ላይ የ15 በመቶ ጭማሪ የተደረገበት ማስተካከያ ተድርጎ በዚሁ አግባብ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አግባብ እንዳልሆነ ማኀበሩ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ቅሬታውን በማቅረብ፣ ይህ ታሪፍ ተግባራዊ እንዳይሆን ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር የቦርድ ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

 የንግድና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በማኅበሩ በቀረበው ቅሬታ መነሻነት ማስተካከያ ለማድረግ ቃል ቢገባም ሳይፈጽም በመቅረቱ፣ በ2012 ዓ.ም. የዘርፉን ችግሮች በማስጠናትና ከጥናቱ የተገኙትን ውጤቶች ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባሻገር ለትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ለነዳጅ አቅርቦት ቁጥጥር ባለሥልጣን ኃላፊዎች የቀረበው ጥናት፣ ‹‹በመንግሥት በኩል የሚፈለገውን ዕይታ ሊያገኝ አልቻለም›› ያሉት አቶ ፀጋ፣ ለስምንት ወራት በጽሑፍና በግንባር በመቅረብ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር የተደረገው ጥረትም፣ በትራንስፖርት ኦፕሬተሮቹ ይጠበቅ የነበረውን ሳይሆን፣ የ15 በመቶ ጭማሪ ይዞ መምጣቱ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡

በፈሳሽ ትራንስፖርት ኦፕሬተርነት አገልግሎት ከሚሰጡ 3,500 ተሽከርካሪዎች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ ከሥራ ውጪ ሆነው በየጋራዡ ቆመው ይገኛሉ ያሉት አቶ ፀጋ፣ 15 በመቶዎቹ በወር አንድ ጊዜ ብቻ ሥራ እንደሚያገኙ ጠቁመው፣ ከ100 በላይ ቦቴ ተሽከርካሪዎች አካላቸው ተቀይሮ ለደረቅ ጭነት ሥራ እንደዋሉ ገልጸዋል፡፡

 በዘርፉ እያጋጠሙ ካሉ ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ የተባሉት በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የጉዞ ክልከላዎች መደረጋቸው የአውሮፕላን ነዳጅ ጭነት አቅርቦት በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረጉ ሲሆን፣ ይህም በርካታ ተሽርካሪዎችን ከሥራ ውጪ አድርጓል ተብሏል፡፡ መንግሥት የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት ተባባሪ አለመሆኑም ተወስቷል፡፡

ባለሀብቶቹ ከአቅምና ዕውቅናቸው ውጪ በአሽከርካሪዎች በሚፈጸም የኮንትሮባንድ ወንጀል ተሽከርካሪዎችን ለመውረስ የሚያስችል ሕግ ሥራ ላይ በመዋሉ፣ በባንክ ብድር የተገዙ ተሽከርካሪዎች እየተወረሱ መሆናቸው፣ ከችግሮቻቸው መካከል ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ አቶ ፀጋ ለማኅበሩ አባላት ባቀረቡት ሪፖርት አሰምተዋል፡፡

በመሆኑም ማኅበሩ በአቋም ካስቀመጣቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል፣ መንግሥት የሚከተለውን የ15 በመቶ ጭማሪ በመተው፣ በጥናትና በድርድር ላይ የተመሠረተ ታሪፍ እንዲሆን የሚጠይቀው ዋነኛው ነው፡፡

ከትራንስፖርት ሚኒስቴርና ከትራንስፖርት ባለሥልጣን የተወከሉ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ በማኅበሩ የቀረቡ ችግሮች ትክክለኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ድርድርና ውይይት እንዲደረግባቸው ጠይቀዋል፡፡ ማኅበሩ ያሉበትን ችግሮች በዘርፉ ለሚመለከታቸው ሁሉ አቅርቦ መፍትሔ በማጣቱ፣ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አቤቱታውን ለማሰማት ያቀረበው ሐሳብም በአባላቱ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የትራንስፖርት ባለሥልጣን ተወካይ ግን ጉዳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከመሄዱ በፊት፣ ችግሮች በየዘርፋቸው ተለይተው ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ቀርበው መፍትሔ ቢፈለግላቸው እንደሚሻል ጠይቀዋል፡፡( ብርሃኑ ፈቃደ – ሪፖርተር)

 

 

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top