የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከፈረንሣይ ኤምባሲ የበጀት ድጋፍ አገኘ
የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚውል ከፈረንሣይ ኤምባሲ የበጀት ድጋፍ አገኘ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ለዕንባ ጠባቂ፣ የግልግል ዳኝነት አካልን ለማጠናከርና ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚውል የ100 ሺሕ ዩሮ ድጋፍ ከፈረንሣይ ኤምባሲ አገኘ፡፡
ምክር ቤቱ ወደፊት ሊያከናውናቸው ላቀዳቸው ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንደሚውል የተገለጸውን 100 ሺሕ ዩሮ ድጋፍ፣ በኢትዮጵያ የፈረንሣይ አምባሳደር ሚስተር ሬሚ ማሬሾ እና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ መካከል በተደረገ ፊርማ፣ የርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ተፈጽሟል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነፀና በኃላፊነት ስሜት ሕዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በኢትዮጵያ እንዲጎለብት የሚሠራ ተቋም መሆኑንና የግልና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን፣ የጋዜጠኞች የሙያ ማኅበራትንና የማኅበረሰብ ሬዲዮ በአባልነት ያቀፈ ተቋም መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከፈረንሣይ ኤምባሲ የተገኘው የበጀት ድጋፍ ምክር ቤቱ ባቀረባቸው የተለያዩ ዕቅዶች መሠረት እንደሆነና በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም ተግባራዊ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ የፈረንሣይ አምባሳደር ሚስተር ማሬሾ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት፣ ሚዲያ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ፣ መንግሥታቸው ነፃና ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ እንዲጠናከር ፍላጎቱ ነው፡፡ በመሆኑም በቀጣይነትም ከምክር ቤቱ ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አማረ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የምክር ቤቱ የሥራ ማስኬጃ በአባላት መዋጮ የሚሸፈን ነው፡፡ ምክር ቤቱ ያደራጀው የዕንባ ጠባቂና የግልግል አካል እንዲጠናከር፣ እንዲሁም የሥነ ምግባር ደንቡን በጋዜጠኞች ውስጥ ለማስረፅ ለቀረፀው ፕሮጀክት፣ የፈረንሣይ ኤምባሲ ላደረገው ድጋፍ አመሥግነዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ራሳቸውን በራሳቸው የሚዳኙበት ሥርዓት በመመሥረት፣ ሙያዊ ግዴታቸውን እንደሚወጡም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በሕግና በሥነ ምግባር ብቻ ተመርተው እንዲያከናውኑ የሚሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ በሥራ ሒደት የሚፈጠር ክፍተትን ራሳቸውን በራሳቸው የሚያርሙበት የግልግል ዳኝነት አካል አቋቁሞ ሥራ ለመጀመር፣ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ከፍርድ ቤት በመለስ በፈቃደኝነት የሚዳኙበት ሥርዓትን ለማጠናከርና የምክር ቤቱን አባላት ጋዜጠኞች ሙያዊ ሥነ ምግባር አክብረው መሥራት የሚችሉበትን፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠት ለተዘጋጀ ፕሮጀክትና ለሌሎችም ፕሮጀክቶች የሚውል የበጀት ድጋፍ ከፈረንሣይ ኤምባሲ መገኘቱ አስደሳች መሆኑም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን፣ በሚዲያ ባለሙያዎች ላይ የሚስተዋሉ የሥነ ምግባር ችግሮችን ለመቀነስና ራስን በራስ የመዳኘት ባህልን ለማሳደግ በመጣር ላይ መሆኑንና ሚዲያ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይተካ ሚና እንዳለው የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአጽንኦት ገልጿል፡፡(ሪፖርተር)