በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተላለፈ መልዕክት
በኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠውን የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና የገፅ ለገፅ ትምህርት ለማስቀጠል እንዲቻል በተቋማቱ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወሳል።
ለዚህም እንዲያግዝ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት የገፅ ለገፅ ትምህርትን ለማስቀጠል ሊከተሏቸው የሚገቡ ፕሮቶኮሎችን በማዘጋጀት ተቋማት በመመሪያው መሰረት እንዲዘጋጁ ሆኗል፡፡
ይሄንንም ዝግጅት የክትትል ግብረኃይል በማዘጋጀትና በማሰማራት በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች በአካል ተገኝተው ግምገማ አካሂደዋል፡፡ በግምገማው ውጤት መሰረትም ተቋማቱ ያላቸው ዝግጅት ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል መሆኑ በመረጋገጡ ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ትምህርትና ስልጠናቸው እንዲመለሱ ጥሪ ተደርጓል፡፡
በመሆኑም ውድ ተማሪዎች ከወራት ቆይታ በኃላ ወደ ትምህርት ገበታችሁ እንደመመለሳችሁና ትምህርትና ስልጠናው የሚቀጥለው ኮቪድ 19 ወረርሽኝን በመከላከል እንደመሆኑ በተቋማቱ የሚኖራችሁ ቆይታ ኃላፊነት የተሞላበት፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ላይ ያተኮረና በከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላ እንዲሆን አሳስባለሁ፡፡
ወደ የዩኒቨርስቲዎቻችሁ ስትመለሱም በአመራሩ የሚሰጣችሁን የጥንቃቄ መመሪያ ሁሉ ተግባራዊ ልታደርጉ ግድ ይላል፡፡ ወረርሽኙን ራሳችንን ብቻ በመከላከል ልንወጣው የምንችል ባለመሆኑ ለትምህርታችሁ ትኩረት ከመስጠት ጎን ለጎን ማስክ በመጠቀም፣ ንፅህናን በመጠበቅና በመመሪያው ላይ የተቀመጡ ሌሎች ህግጋትንም ተግባራዊ በማድረግ የራሳችሁንና የጓደኞቻችሁን ሕይወት እንድትጠብቁም አሳስባለሁ፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሩም ተማሪዎች ወደዩኒቨርስቲ ሲመለሱ መመሪያውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ግንዛቤ በመፍጠርና ከዚህ ቀደም ሲገለፅ እንደነበረው የጥንቃቄ መልዕክቶችን ሁሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በማመቻቸት እንዲሁም መመሪያው እንዲተገበር በማድረግ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አሳስባለሁ፡፡
መምህራን ከተማሪዎቹ ጋር ሰፊ ጊዜ የምታሳልፉ እንደመሆኑ ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ተማሪዎች እንዳይዘናጉ የማድረግና የጥንቃቄ መመሪያውን እንዲያከብሩ የማስገንዘብ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡
የአስተዳደር ሰራተኞችም ተማሪዎች በግቢ ውስጥ የሚኖራቸው መስተጋብር ጥንቃቄ አልባ እንዳይሆን የእናንተም አበርክቶ ከፍተኛ ነውና እናንተ ጠንቃቃ ሆናችሁ ተማሪዎችንም እንድታነቁ ይሆን፡፡
በያዝነው ዓመት የሚኖረንን የትምህርትና ስልጠና ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀምና ትምህርትና ስልጠናው በታቀደው ጊዜ እንዲከናወን ለማስቻል ከፍተኛ ስነ ልቦናዊና መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስና እንደ ጤናችን ሁሉ ሰላማችንንም ማስጠበቅ ኃላፊነታችንና ግዴታችንም ጭምር ነው፡፡
ለዚህም የትምህርትና ስልጠና ማህበረሰቡ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ጤናችሁንና ሰላማችሁን በመጠበቅ፣ ውድ ጊዜያችሁን ለእውቀት ሸመታ፣ ማህበረሰባችሁን በሚጠቅሙ እና አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር እንዲሆን ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ፡፡
ዓመቱ የተለያዩ የለውጥ ስራዎችን የምንከውንበት ውጤታማና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ጊዜ የምናሳልፍበት እንዲሆን ከምንጊዜውም በላይ በጋራና በትጋት እንሰራለን!
ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር
ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም