Connect with us

ለኘሬዝደንት ትራምፕ የተሰጠ መልስ… 

ለኘሬዝደንት ትራምኘ የተሰጠ መልስ...
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ለኘሬዝደንት ትራምፕ የተሰጠ መልስ… 

ለኘሬዝደንት ትራምፕ የተሰጠ መልስ…

“…ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም” የኢፌድሪ የጠ/ሚ ፅ/ቤት

ጥቅምት 14 2013

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ በፍጣሪዋ ታምና በሕዝቧ አንድነትና ጽናት የቆመች ሀገር ናት። ጥቂት ሰጥተው ብዙ ሊያዟት በሚሞክሩ ተማምና አታውቅም። ሕይወታቸውን ሰጥተው ሊታዘዟት በተዘጋጁ ልጆቿ እንጂ። ኢትዮጵያን የፈጠራት አምላኳ ነው። የገነቧት ደግሞ ልጆቿ ናቸው። እነዚህ ልጆቿ በከፈሉት መሥዋዕትነት ዓለምን ጉድ ያሰኙ ታሪኮችን ሠርታለች። 

እነዚህን አስደናቂ ታሪኮችን ስትሠራ አብረዋት ታሪክ የሠሩ ወዳጆች ነበሯት። የከዷት ወዳጆችም ነበሩ። ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። 

ነገር ግን የዓለም ታሪክ ያረጋገጣቸው ሁለት ሐቆች አሉ። ኢትዮጵያን ነክቶ በሰላም የኖረ የለም የሚለው ቀዳሚው ነው። ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለአንድ ዓላማ ከቆሙ ድል ማድረጋቸው አይቀርም የሚለው ደግሞ ሁለተኛው። የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ግድብ ነው። ኢትዮጵያውያን፣ አሰቡት፤ ኢትዮጵያውያን ጀመሩት፤ ኢትዮጵያውያን ገነቡት፤ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ይጨርሱታል። አይቀሬ ነው።

የሚያዋጣን ኅብረት አንድነታችን ነው። ለእኛ ያለነው እኛ መሆናችንን ዐውቀን ስለ እኛ ጉዳይ እኛው ራሳችን ኢትዮጵያን አለንሽ እንበላት። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ለኢትዮጵያ እንቁም። ከባዱ ፈተና ከውጭ የሚመጣው አይደለም። ከባዱ ፈተና ተለያይተን ችግሩን ከተጋፈጥነው ነው። 

ማንም ገዝቶን አያውቅም። ወደፊትም ማንም አይገዛንም።  ታሪክ የሠሩ እጆች ዛሬም አሉ። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸውን ለማክበር እንጂ ጠላቶቻቸውን ለመታዘዝ ተንበርክከው አያውቁም። ዛሬም ወደፊትም አናደርገውም።

ክንዳችንን እናበርታ። ትከሻችንን እናስፋ። ልባችንንም እናጽና። ከውጭና ከውስጥ የተሠነዘረብንን ጥቃት ድል አድርገን መሻገር ብርቃችን እንዳልሆነ እናስመስክር። 

በምንምና በማንም ካሰብነው መንገድ እንቀርም። ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም። አንድ ሆነን የምንይዘው ጋሻ ኃያላኑን ሁሉ ሲመክት የኖረ ነው። ዛሬም ያንን ጋሻ በአንድነት እናንሣ። ሁላችንም፣ በየቦታችን፣ 24 ሰዓት፣ ለኢትዮጵያ እንቁም።

PMOEthiopia

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top