ኢሳትን ወደሕዝብ ሚድያነት ስለማሸጋገር
ከኢንጂነር ሳባ ኣታሮ
በኢትዮጵያ የኢሳት መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ (2010 – 2012)
ኢሳትን ወደ ህዝብ ሚዲያነት ማሸጋገር አማራጭ የሌለው መፍትሔ ስለሆነ፤ ለ15ቱ የኢሳት ኢንተርናሽናል ቦርድ አባላትና የኢሳት ከፍተኛ አመራሮች በወቅቱ ካቀረብኩት ስትራቴጂክ አቅጣጫ ሰነድ የተወሰደ፤
“ኢሳትን ወደ ህዝብ ሚዲያነት ማሸጋገር፣
ላለፉት በርካታ አመታት የኢትዮጵያ ህዝብና በአለም ዙርያ ያሉ ቀናኢ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ኢሳትን በገንዘብ እየረዱ፣ በአገር ቤት ለውጥ ለማምጣት፣ ኢሳት የታለመለትን ግብ እንዲመታ አድርገዋል። ምንም እንኳን ኢሳት ሃገራቸውን በሚወዱ ቀናዒ ኢትዮጵያዊያን የገንዘብ ድጋፍ የተቋቋመ ተቋም ቢሆንም የአመራር ስልጣን ተዋረዱ ግን ህዝብን ያማከለ አልነበረም።
ኢሳት ኢትዮጵያ ውስጥ ከመግባቱ በፊት በውጭ ሃገር ለትርፍ ባልተቋቋመ መልኩ ተዋቅሯል። በጥቂቱ ለመግለፅያህል፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ ሚዲያ ለመንግስት ግብር የማይከፍልና፣ እንዲሁም ትርፍ ተቀባይ ወገን የሌለው ሲሆን፣የሚገኝ ትርፍ ካለም ድርጅቱን ለማሳደግ ሊጠቀምበት ይችላል። ነገር ግን ይህ አይነቱ አወቃቀር የአመራር ቦርዱን በህዝብ መወከል ወይም የህዝብ ባለቤትነትን አያረጋግጥም።
ኢትዮጵያ ውስጥ የተዋቀረው ኢሳት ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብን በባለቤትነት ማሳተፍ የሚችል የአክሲዮንማህበር ስለሆነና ይህም ደግሞ ተቋሙን ለህዝብ ለማሸጋገር ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ስለሚችል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አክሲዮን በመግዛት የኢሳት ባለቤት ሊሆን የሚችልበትን ምህዳር ይከፍታል። ይህ አወቃቀር ህዝብን በለጋሽነት ብቻ ሳይሆን በባለቤትነትም ጭምር ሊያሳትፍ ይችል ነበር።
ህዝብ ከአስቸጋሪ ኑሮው ላይ ከጉድለቱ ቀንሶ የሚረዳውን ገንዘብ ትርጉም ሰጥቶ፣ከገንዘቡ ባለፈ ህዝብ የሚዲያው ባለቤት እንዲሆንና በኢሳት እጣ ፈንታ ላይም ድምፁ እንዲሰማ ማድረግ ሃላፊነት የተሞላው አካሄድ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህ ከሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ኢሳት የመጀመርያው በህዝብ ባለቤትነት የተቋቋመ፣ በህዝብ የሚመራና፣ ተአማኒነቱን በስፋት ለሁሉም ወገን የሚያረጋግጥ ሚዲያ ይሆናል።
የኢሳት ወደ ህዝባዊ ባለቤትነት መሸጋገር ሊፈጥር የሚያስችላቸው ጥቅሞች በጥቂቱ፣
- ኢሳትን በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው በህዝብ የቆመና በህዝብ የሚመራ ሚዲያ ያደርገዋል
- ኢሳትን ከአክቲቪዝም ሚዲያነት ጥርጣሬ ወደ ፕሮፌሽናል ሚዲያነት ዕይታ ለመቀየር ይረዳዋል
- ከአንዳንዶች የሚመጣውን ኢሳትን እንደ ፖለቲካ ተቋም የመመልከት ፍራቻ ይቀንሳል
- የድርጅቱ አመራርና ሂሳብ አያያዝ ለለጋሾችም ሆነ ለህዝብ ይፋ እና ግልጽ በሆነ መንገድ ይከናወናል
- ኢሳት የፖለቲካ ፓርቲ ልሳን ነው ከሚለው ጥርጣሬ ነጻ ያረገዋል
- በቂ ካፒታል (ገንዘብ) ለመሰብሰብ እና ስፋት ያለው ማህበረሰብን ለማሳተፍ እድል ይከፍታል
- የጥቂት ግለሰቦች ከፍተኛ ድጎማ የሚዲያው ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ይረዳዋል
- የበርካታ ህዝብ ባለቤነት ከጥቂት ባለሃብቶች ወይም ፖለቲከኞች ሊያጋጥም ከሚችል ተጽዕኖ ነፃ ያደረገዋል
- የህዝብ ባለቤትነት በገለልተኝነትና በነጻነት፣ የመተቸትና የህዝብ ድምጽ የመሆን አቅሙን ያጎለብተዋል
- አሳታፊነቱ ሲሰፋ ከግዜው ጋር ተራማጅ የሆኑ ቴክኖሎጂ እና የሰው ሃይል ለማዳበር ሰፊ በር ይከፍታል
- የፕሮግራሞችን ይዘት በማስፋት አሁን ያለውን ማስታወቂያ የማግኘት ችግር ያቃልላል
- የንግዱ ማህበረስብ የባለቤትነት እድልም ሊኖረው ስለሚችል፣ ኢሳት ላይ ማስታወቂያ ለመስራት አመኔታና ፍላጎት እንዲጨምር ያደርገዋል።
- ኢሳትን ከጥገኝነትና ከልመና ያላቅቀዋል።
- ለምሳሌ አንድ ሚሊየን ሼሮች እያንዳንዱ በ100 (አንድ መቶ) ብር ቢሸጥ በቀላሉ 100,000,000.00 (አንድ መቶ ሚሊዮን) ብር መሰብሰብና ሚዲያውን ማጠናከር ይቻላል።
- ጥቂቶች እንደ እርስት ተቆጣጥረው ለግል ጥቅም እንዳያውሉት ለመከላከል ይረዳዋል።
- ህዝብ የኢሳትን የአመራር ቦርድ የመምረጥና የመመረጥም እድል ይኖረዋል።”