Connect with us

በመንግስት ፍቅር የወደቁ ሰዎች ቢችሉ መተንፈስ ይከለክሉን ነበር!

በመንግስት ፍቅር የወደቁ ሰዎች ቢችሉ መተንፈስ ይከለክሉን ነበር!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

በመንግስት ፍቅር የወደቁ ሰዎች ቢችሉ መተንፈስ ይከለክሉን ነበር!

በመንግስት ፍቅር የወደቁ ሰዎች ቢችሉ መተንፈስ ይከለክሉን ነበር!
(መልካም ይሆናል ለድሬቲዩብ)

በመንግስት ፍቅር ክንፍ ያሉ ሰዎች እስትንፋሳችንን ሊያቋርጡት ምንም አልቀራቸውም፡፡ እነዚህ ሰዎች በመንግስት ዓይን እንደ ጓድ የሚታዩ “ንቁ የፌስቡክ ተሳታፊዎች” ናቸው፡፡ መሬት ላይ ያለው ሃቅ … በሌላው ችግር የሚሳለቁ በስድብ የተካኑ ሰዎች ስብስብ ነው፡፡
በሀገራችን የአንበጣ መንጋ በትንሹ በሶስት ክልሎች እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ ገበሬውን እያስለቀሰው ይገኛል፡፡ ገበሬው ዓመቱን ሙሉ የለፋበት ማሳው በደቂቃዎች ውስጥ ዶጋ አመድ ከሚያደርግ አደጋ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጧል፡፡ የመንግስት ሚዲያዎች እንደሆኑ የገበሬውን ድምፅ ከፍ አድርገው ያሰማሉ ብለን ስንጠብቅ መዘገብ ያለባቸውን ጉዳይ ዝም ጭጭ ብለው ያሳልፉትና በማይመለከታቸው ጉዳይ ጥልቅ እያሉ በጆሮአችን ይቀልዳሉ፡፡

ዋናውን ስራቸው እርግፍ አድርገው የባለስልጣን ውሎ ዘጋቢ ከሆኑ ሰነባበተ፡፡ በጣም የሚገርመው ዛሬም በሌላ ሀገር ስለተጭበረበረ የህዝብ ድምፅና ጭቆና ሰፋ ያለ ትንታኔ ያቀርቡልናል፡፡ ሚዲያዎቹ እንኳን ከስርዓቱ ጋር በፍቅር ወድቀው ሳይሆን በፍርሃት ተሸብበው ነው፡፡

የአንበጣ መንጋው ሀገር ላይ የሚያመጣው አደጋ ያሳሰበቸው ዜጎች የመንግስት ያለህ ሲሉ መፍትሄ እንዲሰጥ ሲወተውቱ የመንግስት አፍቃሪዎችና ሚዲያዎቻቸው “አንበጣ ምን ያሳይሃል? የእንጦጦ ፓርክ አስገራሚ ጥበብ አትመለከትም ወይ” በማለት እስትንፋስ ለማሳጣት ይጥራሉ፡፡ “መተንፈስ አልቻልኩም” ነበር ያለው ጆርጅ ፍሎይድ ነፍሱን ይማረውና! ቆይ ዜጎች በሀገራቸው ለሚከሰተው ችግር መፍትሄ የመጠየቅ መብት የላቸውም?! ግብር ከፍለው መንግስትን በእግሩ እንዲቆም የሚያደርጉ ዜጎች ሌላው ቢቀር የመጠየቅ ዕድል መንፈግ ከጭቆና በምን ይለያል?

በመንግስት ፍቅር የወደቁ ሰዎች በሌላው ችግር መሳለቅ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ የባህረ-ጥምቀቱ ቦታ “ለምን የቆሻሻ መጣያ ሆነ?” የሚል ጥያቄ ስታቀርብ “ሁለቱ ቅዱስ ሲኖዶሶች ታርቀዋለው” ይሉሃል፡፡

“አሁን ያለው የእስረኞች አያያዝ ያሳስበኛል” የሚል ጥያቄ ካነሳሽማ ጉዳዩን ከሚፈልጉት ሰው ጋር እያያዙ “እገሌ ሲታሰር የትነበርሽ?” እያሉ የብሔር ታርጋ ሰጥተዉት የስድብ ናዳ ያወርዱብሻል፡፡ ጎበዝ ምን ዓይነት ፈተና ነው የገጠመን በጌታ!
መንግስትን “አይጠጌ አይነኬ” (asymptote) ለማድረግ እያለማመዱን ነው?

እርግጥ ነው ህይወታችን ወይም ኑሮአችን የሚያመሰቃቅል በርካታ ብርቱ ጉዳይ ገጥሞን ይህ የኢትዮጵያ ችግር ብቻ አይደለም ባደጉት አገራትም የሚያጋጥም ስለሆነ “አታካብዱት” ተብለን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ከትላንት ዛሬ የተሻለ ልምድ ይገኝበታል፡፡ ዕድሜ በመንግስት ፍቅር ለወደቁ ሰዎች ከ “አታካብዱት” ወደ “ማምታታት” ሽግግር እያደረግን ነው፡፡ ይህ የማምታታት አባዜም ማን ያውቃል አንዱ ኃላፊ ለልምድ ልውውጥ ከሄደበት ሀገር የቀሰመው ይሆናል፡፡

ለማንኛውም ዜጎችን በተለያየ መንገድ እያሸማቀቁ በዝምታ እንዲሸበቡ ማድረግ እና ጥያቄያቸውን ማፈን የፈነዳ ቀን ማጣፊያው እንደሚያጥር ከዚህ በፊት ከነበረን ልምድ አይተነዋል፡፡ አክሳሪ ስልት ነው፡፡

በመንግስት ፍቅር የወደቁ ሰዎች ችግሩ በራሳቸው እስካልደረሰ ድረስ በሌሎች ጫማ ሆነው የሚያዩ አይደሉም፡፡ እነዚህ ሰዎች ከወደቁበት ማንሳት እና ሚዲያዎች ከገቡበት የፍርሃት መንፈስ ማላቀቅ ዘላቂው መፍትሄ ቢሆንም ብዙ ስራ ይጠይቃል፡፡ ለጊዜው የተከበራችሁ እያለን የምፈልገው ሳይሆን የሚፈልገው ሊያቀርብልን የሚሞክረውን ሪሞታችንን አንስተን ጥርቅም ማድረግ፤ ሬድዮም ሳይለንት ሞድ ማድረግ፤ የፌስቡኩም ንቁ ተሳታፊ ወደ ብሎክ ቅርጫት በመጣል እስትንፋሳችን እንዳይቋረጥ ብንከላከል ይሻላል፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top