Connect with us

ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠሏ ያሳስበናል ያሉ ድርጅቶች …

ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠሏ ያሳስበናል ያሉ ድርጅቶች ብሔራዊ የምክክር መድረክ ሊያዘጋጁ ነው
Photo: Ethiopian Reporter

ዜና

ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠሏ ያሳስበናል ያሉ ድርጅቶች …

በአሁኑ ወቅት ከሚታየው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ምስቅልቅሎሽ አንፃር፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠሏ ያሳሰባቸው ድርጅቶች ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር መድረክ ለማዘጋጀት ዝግጅቶችን ማጠናቀቃቸውን ተናገሩ፡፡

ኢትዮጵያ በአስቸኳይ የሚያስፈልጋት የተቀናጀ ብሔራዊ የምክክር መድረክ መሆኑን በመረዳት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ብሔራዊ የምክክር መድረኩን የሚያዘጋጁት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ዴስቲኒ ኢትዮጵያና የሐሳብ ማዕድ የሚባሉ ሦስት ተቋማት በጋራ ያቋቋሙት ‹‹ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ (Mind Ethiopia)›› የተባለ ድርጅት ነው፡፡

የድርጅቱ መሥራቾች አቶ ሙሳ አደም ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ፣ አቶ ንጉሡ አክሊሉ ከዴስቲኒ ኢትዮጵያና ሀደራ አብደላ (ዶ/ር) መስከረም 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በማሪዮት ሆቴል በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ የምክክር መድረኩን ለማዘጋጀት ከገዥው ፓርቲ ጋር ጭምር ጥልቅ ውይይት አድርገዋል፡፡

የብሔራዊ ምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን እያወዛገቡ የነበሩ፣ አሁንም የቀጠሉና ወደፊትም ሊከሰቱ የሚችሉ ሥር የሰደዱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ደረጃ በደረጃ በቅደም ተከተል ወደ ውይይት ጠረጴዛ ለማምጣት፣ የጋራ መግባባትን በየደረጃው እየፈጠሩ ለመሄድና ተወያይቶ ችግሮችን የመፍታት ባህልን መገንባት ዓላማ ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እርስ በርስ የሚያጋጩ የሐሳብ ልዩነቶችን ደረጃ በደረጃ ከማቀራረብ ባሻገር፣ በተሳታፊዎች መካከል መልካም ግንኙነትና የአንድ አገር ልጅነትን መንፈስ የሚያጎለብቱ፣ እንዲሁም መተማመንን የሚያበለፅጉ አሠራሮችን ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የምክክሩ ተሳታፊዎች ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ፣ ሁሉንም ክልሎች ያሳተፈና የአገሪቱን ብዝኃነት ያማከለ እንዲሆን ተደርጎ እንደሚዘጋጅ የማይንድ ኢትዮጵያ መሥራቾች አስረድተዋል፡፡ አገራዊና ሁሉን አቀፍ አጀንዳዎች ከልሂቃንና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሰባሰቡ የጠቆሙት መሥራቾቹ፣ የምክክር ሒደቱ ከጥንስሱ ጀምሮ የተሳታፊዎችን ባለቤትነት ያረጋገጠ መሆኑንና ሙሉ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በሚከበርበት ሁኔታ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡

የምክክር ሒደቱ ከማንኛውም ዓይነት ጣልቃ ገብነት ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ ሥርዓቶችና መርሆዎች ሥራ ላይ እንደሚውሉ ጠቁመው፣ በገንዘብም ሆነ በቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የሚያግዙ አካላት በሒደቱ ላይ ጫና እንዳያሳድሩ እንደሚደረግ፣ የሚኖረው ሒደት አገራዊና ባህላዊ እሴቶችን ያማከለና ፍፁም ሙያዊ በሆነ መንገድ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡ ሒደቱን ከሌሎች አገሮች በተቀሰመ ልምድ ለማካሄድ መሞከሩ እንዳለ ሆኖ፣ ከአገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ለማጣጣምና ለማቀናጀት፣ አገራዊ ልምዶችና ዕውቀቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል ግብዓት እንዲሆኑ ጥረት እንደሚደረግም አክለዋል፡፡

ማይንድ ኢትዮጵያ መድረኩን በማመቻቸትና በማዘጋጀት፣ የተለያዩ ሐሳቦችን በአንድ መድረክ በማምጣት እንዲወያዩ ማድረግ ዋና ተግባሩ መሆኑን፣ ‹‹አንድነታችንና ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው መግባባት ላይ እንድንደርስ ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የትግራይ ክልልን በሚመለከት፣ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በእስር ላይ ስለሚገኙ ፖለቲከኞችም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት፣ ብሔራዊ ምክክሩ ምላሽ የሚሰጣቸው መሆኑንም አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲደረስ ከመጠየቅ ባለፈ፣ እስካሁን ምንም ዓይነት ብሔራዊ የመግባቢያ (የምክክር) መድረክ ተዘጋጅቶ እንደማያውቅ የጠቆሙት አዘጋጆቹ፣ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ በሚዘጋጀው የምክክር ብሔራዊ መድረክ ላይ ሰባት የተመረጡ ጥናቶች በዋና አጀንዳነት እንደሚቀርቡና ጥሩ ግብዓት እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መቀጠል እነሱን ጨምሮ የሁሉም ሰው ሥጋት መሆኑን ተናግረው፣ መፍትሔ መፈለግ ለጥቂቶች የተተወ ነገር ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊያስቡበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ምክር ቤት በአገሪቱ ውስጥ እየተፈጸሙ ስላሉት ችግሮች ዝም ብሎ የተቀመጠ ሳይሆን፣ ለሕዝብ ይፋ ባይደርግም ከመንግሥት ጋር በየዕለቱ ውይይት እንደሚያደርግና እያሳሰበ መሆኑን አቶ ሙሳ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛም የዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት፣ በአገሪቱ የመዘዋወርና ሀብት ማፍራት ጉዳይ ያሳስበናል፤›› ያሉት አቶ ሙሳ፣ ይህ ሁሉ የሚስተካከለው ተመካክረንና ከእነ ልዩነቶቻችን ተግባብተን ስንቀጥል ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡(ታምሩ ፅጌ~ ሪፖርተር)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top