Connect with us

“ለደቂቃም ቢሆን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተፈፅሞ ነፃነቴን ባገኝና እንደገና ብታሰር ግድ የለኝም” አቶ ልደቱ አያሌው

"ለአንድ ደቂቃም ቢሆን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተፈፅሞ ነፃነቴን ባገኝና እንደገና ብታሰር ግድ የለኝም"
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

“ለደቂቃም ቢሆን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተፈፅሞ ነፃነቴን ባገኝና እንደገና ብታሰር ግድ የለኝም” አቶ ልደቱ አያሌው

“ለአንድ ደቂቃም ቢሆን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተፈፅሞ ነፃነቴን ባገኝና እንደገና ብታሰር ግድ የለኝም”

አቶ ልደቱ አያሌው፤ መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎት ላይ ከተናገሩት…

“በአጠቃላይ እጄ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለበት ቀን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ የታየው ሂደት የሚያሳየው ህግ አስፈፃሚው አካል በእኔ ላይ የፈጠራ ክሶችን በማቅረብ፣ በጊዜ ቀጠሮ በማጉላላት፣ የዋስትና መብቴን ያለ አግባብ በመከልከልና ይባስ ብሎም የፍርድ ቤቶችን ትዕዛዝ ባለማክበርና በመጣስ እኔን በእስር ቤት ለረዥም ጊዜ ለማቆየት እየጣረ መሆኑን ነው፡፡

ክቡር ፍርድ ቤት፣ እኔ ለህግ የበላይነት ከፍተኛ እምነት ያለኝና ለችሎት እና ለዳኞች ከፍተኛ አክብሮት ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የፖለቲካ ሰዎች፣ በፖለቲካ አመለካከቴ ምክንያት አምስት ጊዜ አስረውኝ አምስት ጊዜ የፈቱኝ ደግሞ ዳኞችና የፍርድ ቤት ችሎቶች ናችው፡፡ አሁን ግን የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበር በጣም አሳስቦኛል፡፡ ያሳሰበኝ ችግሩ በእኔ ላይ መፈጠሩ ሳይሆን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የማይከበርበት አንድ አገር፣ አገር አይደለም ብዬ ስለማምን ነው፡፡

እኔ አንድ ሰው ነኝ፣ ከማንም የበለጠ መብት የለኝም፡፡ ይህ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያለመከበር ጉዳይ ግን የእኔ የግል ጉዳይ ሳይሆን የአገር እና የስርዓት ጉዳይ ነው፡፡ ክስ እየፈጠረ መብቴን የሚጥሰው አካል መቼም ቢሆን አዲስ ክስ እየፈጠረ መብቴን ሊገፈው እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጀሁ የፖለቲካ ሰው ስለሆንኩ ይህ መሆኑ ቅንጣት አያሳስበኝም፡፡ 

ከሁሉም በላይ የሚያሳስበኝ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመከበሩ ነውና ለአንድ ደቂቃም ቢሆን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተፈፅሞ ነፃነቴን ባገኝና እንደገና ብታሰር ግድ የለኝም፡፡ 

እኔ የፖለቲካ እስረኛ ነኝ፡፡ የታሰርኩትም የፖለቲካ አመለካከቴ ለህዝብ እንዳይቀርብ ስለተፈለገ ነው፡፡ በእኔ ላይ ይህ መድረሱ ምንም አያስደንቀኝም፡፡ እኔ ላይ ሲደርስ መንግስት ጥሩና የህግ የበላይነትን የሚያከብር ሊሆን አይችልምና፡፡ የራሱ እንድ ተቋም የሆነውን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልቀበልም ማለቱ ግን ከልቤ አሳስቦኛል፡፡ የሚከበር ፍርድ ቤት ከሌለ አገር የለምና፡፡ 

ስለዚህ ክቡር ፍርድ ቤቱ ያለምንም ተጨማሪ ትዕዛዝ ከዚሁ በችሎቱ ፊት ሊለቀኝና መብቴን ሊያስከብርልኝ ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀጠሮ መስጠት ዞሮ ዞሮ እኔን ያለ በቂ ምክንያት በእስር ቤት ለማቆየት እየጣረ ላለው ሃይል በተዘዋዋሪ ተባባሪ መሆን ነውና፡፡ ይህ ጉዳይ የእኔ የአንድ ዜጋ ጉዳይ ሳይሆን፣ የህገ-መንግስት፣ የአገርና የህዝብ ጉዳይ ነው፡፡ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲፈፀም ለማድረግ ፍርድ ቤቱ የእኔን ሳይሆን የራሱን ስልጣን ሲያስከብር ማየት እፈልጋለሁ፡፡

አመሰግናለሁ”(ምንጭ:- ኢዴፓ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top