Connect with us

መንግስትን አምኜ ልጆቼን ወደ ትምህርት ቤት ልስደድ?

መንግስትን አምኜ ልጆቼን ወደ ትምህርት ቤት ልስደድ?
በድሬቲዩብ ሪፖርተር

ጤና

መንግስትን አምኜ ልጆቼን ወደ ትምህርት ቤት ልስደድ?

መንግስትን አምኜ ልጆቼን ወደ ትምህርት ቤት ልስደድ? (ፍሬው አበበ)

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጣራ በነካበት በዚህ ወቅት ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ የተወሰነበት ምክንያት እስካሁን በበቂ ሁኔታ የሚያስረዳኝ አላገኘኹም፡፡ 

ትምህርቱ ኮሮናን በመከላከል ላይ ተመስርቶ ይሰጣል በሚል እየተነገረ ያለውም ጉዳይ ጠለቅ ብሎ ላየው በከንቱ ጉንጭን ማልፋት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይኸን ያልኩበት በቂ ምክንያቶች አሉኝ፡፡ እጠቅሳለሁ፡፡  

ትላንት መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ለ34 ሺ ትምህርት ቤቶች በዘላቂነት ውሃ ለማቅረብ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ 

በእኔ አስተያየት ይህ ስራ እጅግ ዘግይቷል፡፡ ኮሮናን ለመከላከል ንጽህናን መጠበቅ ወሳኝ ከመሆኑ አንጻር ውሃ ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት አስተማማኝነቱ መረጋጋገጥ አለበት፡፡ ውሃ በአስተማማኝ መልኩ መኖሩ ሳይረጋገጥ ስለትምህርት ቤት መከፈት ማውራት በፍጹም የሚታሰብ አይሆንም፡፡ 

አሁን ትምህርት ቤቶቹ ሊከፈቱ የአንድ ወር ጊዜ ቀርቷል፡፡ ሚኒስቴሩ የውሃ ጉዳይን ገና አልፈታም፡፡ በዚህ ላይ አዲስአበባ ብቻ ብንወስድ በውሃ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ሰፊ አለመጣጣም በመኖሩ የትምህርት ሚኒስቴር መቀመጫ በሆነው መሀል አራት ኪሎ ሳይቀር ውሃ በፈረቃ የሚታደልበት ተጨባጭ ሁኔታ መኖሩ ጸሐይ የሞቀው ሐቅ ነው፡፡ 

የክልሎች ደግሞ ከዚህም የባሰ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ 34 ሺ ትምህርት ቤቶች በዚህ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ የ24 ሰዓታት አስተማማኝ የውሃ ስርጭት እንዴት ሊያረጋግጡ ይችላሉ የሚለው በበቂና አስተማማኝ ሁኔታ አስካሁን መልስ አለማግኘቱ እንደወላጅነቴ አሳስቦኛል፡፡

ሌላው የማስክ (ጭንብል) ጉዳይ ነው፡፡ ሚኒስቴሩ “ማስክ ያላደረገ ተማሪ ትምህርት ቤት አይገባም” የሚል መግለጫ ሰጥቷል፡፡ የማስክ አቅርቦትም አደርጋለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ይኸ ከቅድመ ጥንቃቄ አንጻር ዋጋው ከፍ ያለ ጥሩ እርምጃ  በመሆኑ ተቃውሞ የለኝም፡፡ 

ነገርግን በጥያቄ መልክ የማነሳው የትግበራ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ በተለይ ከሰባት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት እንዴት ይተገብሩታል የሚለው በግልጽ አለመመለሱ ያሳስባል፡፡ 

በፈረቃ ትምህርት ፕሮግራም መሰረት አንድ ሕጻን ከአራት ሰዓታት በላይ ጭምብሉን ሳያወልቅ እንዴት ሊማር ይችላል? ይህ ጉዳይ ከጤና አንጻር ታይቷል ወይ? አንዳንድ የሚወጡ አለምአቀፍ የጤና መረጃዎች ሕጻናት ለረጅም ሰዓት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረጋቸው እንደማይመከር የሚያስረዳ ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ረገድ ምን ይላል?

 በተጨማሪም  ህጻናት ልጆቻችን ጭምብሉን እንደእርሳስና ደብተር በየሜዳው ጥለው ላለመምጣታቸው ማን እርግጠኛ መሆን ይችላል? ይህ እንዳይሆን ስራዬ ብሎ፣ ሳይሰለች የሚቆጣጠር ትምህርት ቤትስ አለ ወይ የሚለው በደንብ የሚያነጋግር ነው፡፡ 

በዚህ ላይ ሕጻናቱ ጭምብሉን “የአንተ ያምራል፣ የአንቺ ያምራል…እስቲ ልለካው” እየተባባሉ ሲዋዋሱ ቢውሉ አደጋው የከፋ አይሆንምን ወይ?

መንግስትን አምኜ ልጆቼን ወደ ትምህርት ቤት ልስደድ?

በግሌ ልጆቼን በማስተምርበት ት/ቤት ሕጻናት የታሰረላቸውን ምግብ ስለመብላት፣ አለመብላታቸው እንኳን ክትትል ማድረግ የማይችሉ መሆናቸውን አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ 

እናም ይህ ትምህርት ቤት ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ የተቀመጡ የቅድመ መከላከል እርምጃዎች አመቱን ሙሉ ሊተገብር ይችላሉ ወይ ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፡፡ እናስ ምን ምርጫ አለ?

በግሌ የመንግስትን የትምህርት መጀመር ውሳኔ ባከብርም ከልጆቼ ጤና ሁኔታ ጋር ሁኔታዎችን ጠለቅ ብዬ ስመረምር  ሪስኩ ከፍ ብሎ ታይቶኛል፡፡ የደህንነታቸው ጉዳይ አሳስቦኛል፡፡ 

እናም ልጆቼን ወደትምህርት ቤት የመሰደዱ ጉዳይ ላይ  እኔና ቤተሰቤ ገና የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልደረስንም፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ? እስቲ ሀሳብ ይስጡበት?

 

Click to comment

More in ጤና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top