ወይ ህወሓቶች፤ አሁንም አያውቁንም?
(እሱባለው ካሳ)
አዎ ነገሩ ያስቆጫል፡፡ ዋ! ያስብላል፡፡ ህወሓቶች ትላንት ከተቸከሉበት ስልጣን ለምን በሕዝብ ተቃውሞ ተመንግለው እንደወደቁ እስካሁን በቅጡ አልተረዱም፡፡ ለምን መቀሌ ሸሽተው፣ መሸሽ ብቻም ሳይሆን ፕላኔትና አክሱም ሆቴል ወጣ ለማለት ፈርተው፤ ሲብከነከኑ እንደሚውሉ ገና በቅጡ አልገባቸውም፡፡
እናም ዓይናቸውን በጨው አጥበው ዛሬ ስለዴሞክራሲያዊ ምርጫ፣ ስለሕገመንግስት ሲደሰኩሩ ትንሽ እንኳን አንደበታቸውን ደንቀፍ የሚላቸው አልሆኑም፡፡ ሕዝቡ ሌላው ቀርቶ ጠዋት ማታ በስሙ የሚምሉለት የትግራይ ሕዝብ ምን ይለናል የሚል ሼም አልፈጠረባቸውም፡፡
በእነሱ ቤት ሕገመንግስት አክብረው፣ ምርጫ አካሂደው ልባቸው ውልቅ ብሏል፡፡ አዎ! ብቻቸውን በሮጡበት ምርጫ እንደተገመተው፣ ብዙ ሰውም አስቀድሞ እንደጠበቀው መቶ በመቶ አሸንፈዋል፡፡ ይኸን ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ይሉታል፡፡ “ዴሞክራሲን” ይዘባበቱበታል፡፡ የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ፍቅር መቶ በመቶ የወደቀ ይመስል ዞር ብለው “ህወሓት ማለት የትግራይ ሕዝብ ነው፣ የትግራይ ሕዝብ ማለት ሕወሓት ነው” በሚል እያጃጃሉ የኖሩበትን ሌብነት አሁንም ማጧጧፉን ቀጥለዋል፡፡
አሁን ግን ሳይቸግራቸው ከእነዶ/ር አብይ ጋር ሆድና ጀርባ ሆነው ግራ ግብት ብሏቸዋል፡፡ በብስጭት አልኮል በቀማመሱ ተሯሩጠው ስብሰባ ይመጣሉ፡፡ የፈረደበትን አንድ አይነት ይዘት ያለው መግለጫ ያነበንባሉ፡፡ ቀጥለውም ጌታቸው ረዳን ወደቴሌቭዥን ጣቢያ አካልበው ይልኩታል፡፡ ጌቾ ሀሳብ በጠረረበት ጊዜ ሁሉ የስድብ ናዳ አውርዶ ይመለሳል፡፡ እንዲሁ ነግቶ እየመሸ ሁለት ዓመታት እንደዋዛ ነጎዱ፡፡ ሰዎቹ በእርጅና ላይ ብስጭት ታክሎበት በሞት አፋፍ ላይ ሆነውም ሲበድሉት የኖሩትን ሕዝብ አሁንም ስማን እያሉ ማላዘናቸውን ቀጥለዋል፡፡
ነጋ ጠባ በመግለጫ፣ በሚዲያ ስድብ ሕገመንግስት ተጣሰ ይላሉ፡፡ ምርጫ ሳይካሄድ ቀረ ይላሉ፡፡ ሰብአዊ መብት ተረገጠም ይላሉ፡፡ አሁን ደግሞ ቢቸግራቸው ሕጋዊ መንግስት የለም ወደሚል ወርደዋል፡፡ የሚናገሩት ግን አሳምሮ ለሚያቃቸው፣ የግፍ በትራቸውን ለቀመሰው የኢትዮጽያ ሕዝብ መሆኑን ደጋግመው መርሳታቸው ሰዎች እርጅና ለአልዛይመር (የመርሳት በሽታ) ሕመም እንደዳረጋቸው በቂ ማሳያ ነው፡፡ በቅሎ ገመድዋን በጠሰች ቢሉ ለራስዋ አሳጠረች አሉ፡፡
አሁን የፌዴራል መንግስት አልታዘዝም ካለ አካል ጋር አልሰራም ቢል ምን ሊፈጠር የሚችል ይመስላችሃል? ጦርነት?…ኸረ በጭራሽ፡፡ ጥቂት የዘራፊዎች ስብስብን ለማዳን የትግራይ ወጣት ከጎናቸው እንደማይቆም እነሱም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናቸው እንደማይቆምም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ እናም ህወሓቶች ያላቸው ብቸኛ ምርጫ አይናቸው እያየ ተፈጥሮአዊ ሞትን ማጣጣም ብቻ ነው፡፡ ምስኪን!… ነፍስ ይማር!