ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ብር 28 ነጥብ 7 ቢሊዮን ለማትረፍ አቅዶ በጊዚያዊ ሂሳብ መረጃ መሠረት ብር 28 ነጥብ1 ቢሊዮን ወይም የዕቅዱን 98 በመቶ አተረፈ፡፡
ድርጅቱ ይህንን ትርፍ ሊያገኝ የቻለው በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ ስልክ፣ሞባይል፣ዳታና ኢንተርኔት እንዲሁም ተጨማሪ እሴት ከታከለባቸው አገልግሎቶች በድምሩ ብር 45.4 ቢሊዮን ገቢ ለማግኘት አቅዶ ብር 47.7 ቢሊዮን ወይም የዕቅዱን 105 በመቶ ማግኘት በመቻሉ እንደሆነ የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ሪፖርት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ መሰብሰቢያ አዳራሽ በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር በአቶ በየነ ገ/መስቀል ሰብሳቢነት መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በተገመገመበት ወቅት ተገልጿል፡፡
የድርጅቱ ገቢ አፈጻጸም ከ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸም ብር 43.6 ቢሊዮን ጋር ሲነጻጸር በ3.5 በመቶ ያህል ጭማሪ ያሳያል፡፡ ከደንበኞች ቁጥር አንጻርም በባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከነበሩት 43.6 ሚሊዮን ደንበኞች በ2012 በጀት ዓመት ወደ 46.1 ሚሊዮን ከፍ ያደረገ በመሆኑ የ5.7 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡
ድርጅቱ አገልግሎቱን በውጭ ምንዛሪ ጭምር የሚሰጥ በመሆኑ በዚሁ በጀት ዓመት 138 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት አቅዶ 148 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት በመቻሉ ዕቅዱን በ107 በመቶ አሳክቷል፡፡
ድርጅቱ ያሉበትን ልዩ ልዩ ግዴታዎች በመወጣት ረገድ በበጀት ዓመቱ ለውጭ አበዳሪዎቹ ብር 10.2 ቢሊዮን ወይም 318 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ክፍያ የፈጸመ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ብድር እንደሌለበት በግምገማው ወቅት ተገልጿል፡፡ የመንግሥት የትርፍ ድርሻ እና ታክስ ክፍያንም በተመለከተ በበጀት ዓመቱ ብር 4 ቢሊዮን የትርፍ ድርሻ እንዲሁም ብር 11.3 ቢሊዮን ታክስ በድምሩ ብር 15.3 ቢሊዮን በታክስና በትርፍ ድርሻ መልክ ለመንግሥት ገቢ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡ በከፍተኛ ታክስ ከፋይነቱም ከዘንድሮ ወርቅ ተሸላሚዎች አንዱ መሆን ችሏል፡፡
ድርጅቱ በሀገሪቱ ተጨማሪ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ሲገቡ በዋጋም ሆነ በአገልግሎት ጥራት የመወዳደር አቅሙን ከአሁኑ ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡በሀገሪቱ ዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድም የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ በፋይናንስ፣በሰው ኃይል ልማት፣በአሠራር ማሻሻያ ሠፊ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ ገቢውንም በ2013 በጀት ዓመት ወደ 55.5 ቢሊዮን ለማሳደግ እንዳቀደ በግምገማው ተገልጿል፡፡
በግምገማው መጨረሻ ላይ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ለማስፋት አቅዶ ያከናወናቸው ተግባራት ከፍተኛ ስኬት ያስገኙለት ስለሆኑ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ይህንኑ ጥረቱን በ2013 በጀት ዓመትም አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው ግምገማው ተጠናቋል፡፡
(ምንጭ:- የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ)