ሶስት ወራትን ይፈጅ የነበረው የፓስፖርት ዕድሳት በ12 ቀናት ይጠናቀቃል ተባለ
በአሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያንም በ’Online’ ፓስፖርታቸውን ማሳደስ መጀመራቸው ተሰማ።
ከ80 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው የሀገራችን ኢሚግሬሽን ዜግነት ጉዳዮች አገልግሎት ካለፉት 2 ዓመታት ወዲህ የነበሩበትን ጎታችና አሳሪ አሰራር እየተሻገረ ነው የሚሉ ተገልጋዮች ይደመጣሉ።
በተቃራኒው አገልግሎቱ በሀገሪቱ የረጅም ዓመታት እድሜ ቢኖረውም ዛሬም በርካታ ችግሮች አሉበት ብለው የሚሞግቱም አልጠፉም።
ሁለቱም ወገኖችን ግን ተቋሙ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተጠቅሞ ለረጅም ዓመታት በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስር የነበረ አንድ የሥራ ሂደት ከወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጋር አዋህዶ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በሚል በአዲስ መልክ በህግ እንዲቋቋም ከተደረገበት ወዲህ አሰራሩን ለማዘመንና የተቀላጠፈ ለማድረግ ደፋ ቀና እያለ ስለመሆኑ ይስማሙበታል።
ሸገርም በተለያዩ ጊዜያት ፓስፖርት ከማወጣት እስከ እጥረት ያለውንና ሌሎች መሰል ቅሬታዎችን ከአድማጮቹ ሲነሱ የተቋሙን ዳይሬክተርን ጨምሮ ሌሎች የተቋሙ የስራ ሃላፊዎች ምላሽና መፍትሔ ሲያሰጥ ቆይቷል።
ከተቋሙ አሰራር ጋር ተያይዞ ከሚቀርቡ ቅሬታዎች መካከል በቅርቡ መፍትሔ የተበጀለትን በኦን ላይን ወይም ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው በኢንተርኔት በመታገዝ በቀጥታ መስመር ፓስፖርታቸውን የሚያሳድሱበትን አሰራር በተመለከተ እንዴት ነው እየተሰራ ያለው? ስንል የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማልን ጠይቀን ነበረ።
የፓስፖርት እጥረቱና የእድሳት ጊዜው በመራዘሙ በሀገር ቤትም ሆነ በባህር ማዶ ባሉ ተገልጋይ ዜጎቻችን ይሰማ የነበረው ቅሬታ ዘላቂ መፍትሔ አበጅተንለታል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ በባህር ማዶ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የፓስፖርት ዕድሳትና የትውልድ መታወቂያ ካርድ አሰጣጥ ፈጣንና የዘመነ ተድርጎላቸዋል ይላሉ፡፡
ከቀናት በፊት የተጀመረው የበ’Online’ ዕድሳት እንደ ቀደሙት ጊዜያቶች ተገልጋዮች በግንባር መምጣትን ሳይጠበቅባቸው 3 ወር መጠበቅም ሳይኖርባቸው በ12 ቀናት ፓስፖርታቸውን ማሳደስ ይችላሉ ሲሉ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል ማረጋገጫ ይሰጣሉ።
በአውሮፓና በአፍሪካ በተለይም ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ይህንኑ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ እሩቅ እንዳልሆነ ከዋናው ዳሬይክተር ሰምተናል።
በሀገር ውስጥ ያሉ ዜጎችም በ’Online’ ፓስፖርት የሚያሳድሱበት ቴክኖሎጂ ዘጠና በመቶ ስራው መጠናቀቁንም ከኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ሰምተናል። (ሸገር)