Connect with us

ንግድ ባንክ የብሔራዊ ባንክን መመሪያ በመጣስ ለማይገባቸው ግለሰቦች የውጭ ምንዛሪ ሲያድል ነበር

ንግድ ባንክ የብሔራዊ ባንክን መመሪያ በመጣስ ለማይገባቸው ግለሰቦች የውጭ ምንዛሪ ሲያድል ነበር
Photo: Social media

ኢኮኖሚ

ንግድ ባንክ የብሔራዊ ባንክን መመሪያ በመጣስ ለማይገባቸው ግለሰቦች የውጭ ምንዛሪ ሲያድል ነበር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ስልጣን በያዙ ማግስት የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ካዝና ክፉኛ ተመዝብሮ ባዶ እንደነበር ተናግረው ነበር።

እሳቸውም ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ከብሔራዊ ባንክ ደንብ እና መመሪያ ውጭ ሲባክን እንደ ነበር ሸገር ያገኘው አንድ ሰነድ ያስረዳል።

ከለውጡ ወዲህ ባሉ ጊዜያትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ከብሔራዊ ባንክ መመሪያ ውጭ ለማይፈቀድላቸው እንደሰጠ ሸገር ካገኘው ሰነድ ተረድቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአቶ በቃሉ ዘለቀ ይመራ በነበረበት በ2010 ዓ.ም ከግንቦት እስከ ነሀሴ ከባንኩ በትንሹ ከ69 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ (የውጭ ምንዛሪ ) ከመመሪያ ውጪ ለተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች እንደተሰጡ ከሰነዱ አንብበናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ድልድልን አስመልክቶ በተጠቀሰው ጊዜ ከ3 ዓመት በፊት ያወጣውን መመሪያ ንግድ ባንኩ በከፍተኛ ደረጃ ሲጥስ እንደነበር ይኸው ሰነድ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጪ ሀገር ገንዘብ ወይም የውጪ ምንዛሪ ድልድልን አስመልክቶ ያወጣው መመሪያ ቁጥር FXD/51/2017 ለኮንስትራክሽን ድርጅቶች የግንባታ ማሽኖች መለዋወጫ ለማስገባት ለአንድ የግዢ ማቅረቢያ ከ50,000 የማይበልጥ የአሜሪካ ዶላር እንዲመደብ ቢፈቅድም መመሪው ከወጣ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ማለትም በ1ኛው ወቅት በቁጥር 36 ለሚሆኑ በሌላኛ ወቅት ደግሞ 46 ለሚሆኑ የውጭ ምንዛሪ ጠያቂዎች ለእያንዳንዳቸው ከመመሪያው ውጪ ከ50,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ ተመድቦላቸው ወይም ተሰጥቷቸው እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ከራሱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወጣው እና በባንኩ የቀድሞ ፕሬዘዳንት አቶ ባጫ ጊና የተፈረመበት ይኸው ሰነድ እንደሚያስረዳው ከሆነ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በመጋቢት 2018፤36 ለሚሆኑ የውጪ ምንዛሪ ጠያቂዎች ለእያንዳንዳቸው ከመመሪያ ውጪ ከ50,000 ዶላር በላይ በድምሩ 19 ሚሊዮን 886 ሺ 137 የአሜሪካ ዶላር ፣ በነሐሴ ወር 2018 ደግሞ ለ 46 የውጪ ምንዛሪ ጠያቂዎች በድምሩ 27 ሚሊዮን 648 ሺ 788 የአሜሪካ ዶላር እንደተመደበላቸው ያሳያል።

በዚሁ ዓመት በግንቦት ወር 2018 መመሪያው የውጪ ምንዛሪ እንዳያገኙ ከፈቀደላቸው የስራ ዘርፍ ውጪ ላሉ ወይም መመሪያው ለማይመለከታቸው ቢያንስ ሸገር የሚያውቃቸው 5 ድርጅቶች በድምሩ 11 ሚሊዮን 847 ሺ 583 የአሜሪካ ዶላር እንደተሰጠ ሰነዱ ያስረዳል።

ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ

– ለመለስ ፋውንዴሽን 100 ሺ ዶላር፣

– ለኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ 66 ሺህ 750 ዶላር ፣

– ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ሴንተር 500 ሺ የአሜሪካ ዶላር

– ለኢዮሃ ፕሪንተር 27 ሺህ ዶላር እና

– ለብርሃኔ ወልዱ 140 ሺ 800 ዶላር መፈቀዱን ሸገር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ባንኩ በተመሳሳይ ጊዜ ማለትም በግንቦት 2010 በቁጥር 10 ለሚሆኑ መኪና አቅራቢዎች ከብሔራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ድልድል መመሪያው ውጪ ለመለዋወጫ ማስመጫ
10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ንግድ ባንኩ እንደሰጠ በዚሁ ሰነድ ተመልክተናል።

በአቶ በቃሉ ዘለቀ እግር አቶ ባጫ ጊና ከተተኩ በኋላ የተፈፀመው አሰራር እና የውጭ ምንዛሪ ብክነት ተጣርቶ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በየካቲት ወር 2011 ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ማሳወቃቸውን ሸገር ካገኘው ሰነድ ተመልክቷል።

ሸገር የተፈፀመውን ህገ ወጥ የውጪ ምንዛሪ ብክነት አስመልክቶ ጉዳዩ የሚመለከተው ህግ አስፈፃሚ አካል አስፈላጊውን ምርመራ እንዲያካሂድ ባንኩ ደብዳቤ የፃፈው በየካቲት ወር 2011 ማለትም ከዛሬ 1 ዓመት ከ6 ወር በፊት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ፤ በጉዳዩ ላይ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምን እርምጃ ወስዶ ይሆን? ሲል የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግን ጠይቋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ም/ል አቃቤ ህግ ለሆኑት አቶ ፍቃዱ ፀጋ ጉዳዩን አብራርተን ምን እርምጃ እየተወሰደ ነው ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ እሳቸው በምክትል አቃቤ ህግ ማዕረግ የተሾሙት በቅርቡ መሆኑን ተናግረው ጉዳዩ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አጣርቼ እነግራችኋለሁ ብለውናል።

ሸገር በዚሁ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖን መልስ አካቶ በሌላ የወሬ ግዜ ለመመለስ ይጥራል።

ይህ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ውጭ ተፈፀመ የተባለው የውጭ ምንዛሪ ብክነት ተግባራዊ በተደረገበት ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ይመሩ የነበሩት አቶ በቃሉ ዘለቀ እንደነበሩ ሸገር ለማወቅ ችሏል።(ሸገር ኤፍኤም ራድዮ)

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top