በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው ጠበቃቸውን አሰናበቱ
(የደብዳቤው ሙሉ ቃል እነሆ)
.***
ለአቶ አብዱልጀባር ሁሴንና ለሞያ ባልደረቦቻቸው
ጉዳዩ፦ የጥብቅና አገልግሎት ማቋረጥን ይመለከታል
በኦሮሚያ ክልል፣ በቢሾፍቱ ከተማ እኔን በሚመለከት በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው የክስ ሂደት የክልሉን ቋንቋ ባለማወቄና የፖለቲካ ሰው በመሆኔ ምክንያት ፍትህ እንዳይጓደልብኝ በማሰብ በራሳችሁ በጎ ፈቃድና በነፃ የጥብቅና አገልግሎት እየሰጣችሁኝ መሆኑ ይታወቃል።
ይህንን በማድረጋችሁም ምን ያህል ቃለ መሃላ ለፈፀማችሁበት ሞያችሁ እና ለህግ የበላይነት መከበር ፅኑ አቋም ያላችሁ የህግ ባለሞያዎች መሆናችሁን በተግባር አስመስክራችኋል።
እስካሁን በተኪያሄዱት የክርክር ሂደቶችም ፍትህ እንዳይጓደል ያደረጋችሁት ከፍተኛ ጥረትም ለህግ የበላይነት መከበር ያላችሁን ከፍተኛ ተቆርቋሪነት የሚያሳይ ነው።
ለዚህ ልባዊ አገልግሎታችሁ በእኔ በኩል ያለኝን አክብሮት እና ምስጋና እጅግ ከፍተኛ መሆኑንም በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ።
ሆኖም ካለፉት ስምንት የችሎት ሂደቶች እንደታየው የፖሊስ እና የአቃቢ ህግ ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያገኙ ሲሆን የኔ ህጋዊ የመብት ጥያቄዎች ግን አንድም ጊዜ ተቀባይነት ሲያገኙ አልታዩም።
የምርመራ ፋይሌ በፍ/ቤቱ በተዘጋበት እና ምንም አይነት የጊዜ ቀጠሮ ባልተሰጠኝ ሁኔታ የዋስ መብትም እንዳይኖረኝ ተከልክያለሁ።
በዚህ ምክንያት በፖለቲካ አመለካከቴ እንድታሰር የወሰኑብኝ የፖለቲካ ሰዎች ስለ ወደፊቱ እድሌም የሚወስኑትን የፖለቲካ ውሳኔ በእስር ላይ ሆኜ እየተጠባበኩኝ እገኛለሁ።
የእኔን የዋስ መብት ለማስከልከል በመንግስት በኩል ዋና መረጃ እና ምክንያት ሆኖ የቀረበውን የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ያቀረብኩት የሰላም ሰነድና እና ገና ታትሞ ያልተሰራጨው የመፀሃፍ ረቂቅ መሆኑ በግልፅ የሚያሳየውም እኔ የህግ ሳይሆን የህሊና እስረኛ መሆኔን ነው።
በአጭሩ እኔ የታሰርኩት ለምን ወንጀል ፈፀምክ ተብዬ ሳይሆን ለምን አሰብክ ተብዬ ነው።
ካለፉት ስምንት የችሎት ሂደቶች ለመታዘብ እንደቻልነው በፖለቲካ እና በህግ መካከል ክርክር እየተኪያሄደ መሆኑን እና ሁልጊዜም ግን በክርክሩ አሸናፊ እየሆነ ያለው ህግ ሳይሆን ፖለቲካ መሆኑን ነው።
ህግ የፖለቲካ መሳሪያ በሆነበት ሁኔታ በህግ ክርክር መብትን ማስከበር ስለማይቻል ከአሁን በኋላ ህጋዊ ግዴታዬን ለመወጣት ቀጠሮ ሲሰጠኝ በችሎት ፊት ከመገኘት ባለፈ የህግ ክርክር የማድረግ ፍላጎት የለኝም።
ስለሆነም እስከአሁን ለሰጣችሁኝ ልባዊ አገልግሎት ምስጋናዬን እያቀረብኩ ከዚህ በኋላ ግን ትርጉም የሌለው የህግ ክርክር በማኪያሄድ የናንተን ውድ ጊዜ ማባከን ስለሌለብኝ የጥብቅና አገልግሎታችሁን ማግኘት የማልፈልግ መሆኑን በአክብሮት እገልፃለሁ።
ከሰላምታ ጋር
ልደቱ አያሌው
(ምንጭ :-አዳነ ታደሰ የኢዴፓ ሊቀመንበር ፌቡ ገፅ)