Connect with us

ፓርላማው ለመጪው ዓርብ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

ፓርላማው ለመጪው ዓርብ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ
Photo: Social media

ዜና

ፓርላማው ለመጪው ዓርብ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

~ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕጩ ተሿሚዎችን ለምክር ቤቱ

እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል

ከሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ለዓመታዊ እረፍት የተበተነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለመጪው ዓርብ መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ።

ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የሕዝብ ተመራጮቹ ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርተዋል፡፡ የተጠራው አስቸኳይ ስብሰባም ምክር ቤቱ የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ስብሰባውን በሚያካሂድበት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ እንደሚሆን ይጠቁማል።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ ምንጮች ለአስቸኳይ ስብሰባው ከሚቀርቡ አጀንዳዎች መካከል፣ እስካሁን እንደሚታወቀው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚያቀርቡትን የካቢኔ አባላት ሹመት መርምሮ ማፅደቅ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ ከሚያቀርቧቸው ተሿሚዎች መካከል ሦስቱ በምክር ቤቱ ሳይሾሙ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጧቸው የሹመት ደብዳቤ ብቻ ቢሮ ተረክበው እያገለገሉ የሚገኙት ባለሥልጣናት ናቸው።

ከእነዚህም መካከል ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባነት ተነስተው የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሹመት ደብዳቤ የተሰጣቸው ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ይገኙበታል።

በተመሳሳይ ወቅት ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትርነት ተነስተው የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር እንዲሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሹመት ደብዳቤ የተሰጣቸው አቶ ሳሙኤል ሁርካቶና የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ለማ መገርሳ በመተካት የተሾሙት ቀንአ ያደታ (ዶ/ር) ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱት ሦስት አመራሮች በሚኒስትርነት መሾማቸውን የሚገልጽ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊርማ ያረፈበት ደብዳቤ እንደደረሳቸውና የተሾሙበትን ኃላፊነት መረከባቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሾማቸውን ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ለፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮችን ሹመት የማፅደቅ ሥልጣን ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ዕጩ ተሿሚዎችን ለምክር ቤቱ ማቅረብ ብቻ እንደሆነ በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ ተደንግጓል።

በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የሰጡት የሚኒስትርነት ሹመት ሕጋዊ ሥርዓትን ያልተከተለ እንደሆነ የሕግ ባለሙያዎች ይተቻሉ። በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመቱን በምክር ቤቱ ማፀደቅ ያልቻሉት ምክር ቤቱ ለእረፍት በመበተኑ ሊሆን ይችላል ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ቢሆንም ምክር ቤቱ እረፍት ላይ በሆነበት ጊዜ ለአስፈላጊ ጉዳዮች በአስቸኳይ እንዲጠራ ማድረግ እንደሚቻል የሚጠቁሙ ባለሙያዎች፣ ይህንን በተገቢው ፍጥነት ማድረግ ካልተቻለ ሹመቱን አዘግይቶ ተቋማቱ በምክትል ወይም በተጠባባቂ ሚኒስትሮች እንዲመሩ ማድረግ ይቻል እንደነበር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በምክር ቤቱ የተሾመ ሚኒስትር ከመነሳቱ አስቀድሞ የሚነሳበትን ምክንያት የሾመው አካል በግልጽ ማወቅ እንዳለበት የጠቁሙት ባለሙያዎቹ፣ ይህንን አለማድረግ የምክር ቤቱን መንግሥትን የመከታተልና የመቆጣጠር (ቼክ ኤንድ ባላንስ) ዋነኛ ተግባር የይስሙላ እንደሚያደርገውና ምክር ቤቱ በገዥው ፓርቲ አባላት የተያዘ በመሆኑ ለውጥ የለውም የሚል ግንዛቤን በኅብረተሰቡ ላይ ከመፍጠር አልፎ፣ የፓርቲናና የመንግሥት ሚናን ለመለየት ያስቸገራል ሲሉ ያሳስባሉ።

ከሚኒስትሮችና በአዋጅ ከተቋቋሙ ኮሚሽኖች ውጪ የሆኑ ተቋማት አመራሮችን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ሳያቀርቡ በራሳቸው ሹመት መስጠት እንደሚችሉም አስረድተዋል።(ዮሐንስ አንበርብር ~ ሪፖርተር)

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top