ዛሬ መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ/ም ይፋ የተደረገው የብር ኖቶች ቅያሪ 5 ብርን ሳይጨምር በሶስት ወራት ግዜ ይጠናቀቃል ተብሎ ታቅዷል፡፡
ሆኖም ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ማለትም ከ 100 ሺ ብር በላይ ገንዘብ በእጃቸው የሚገኝ ዜጎች የገንዘብ ለውጡን በ አንድ ወር ግዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በከፍተኛ ሁኔታ የጥሬ ገንዘብ በኢኮኖሚ ውስጥ ታትሞ መሰራጨቱን ያስታወቁት ጠ/ሚ አብይ አህመድ ለዚህም ማሳያ አሁን የታተመው የ10 ብር የገንዘብ ኖት ብቻ በ1990 ዓ/ም ለነበረው የብር ኖት መቀየሪያ ከታተሙት ሁሉም አይነት ኖቶች የሚበልጥ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በአዲሶቹ ኖቶች ላይ ከፍተኛ የደህንነት ማረጋገጫዎች የተካተቱበት ሲሆን አሁን ይፋ ለተደረገው የ 200 ብር ኖት ደግሞ ስፓርክ የሚያደርግ እና በርካታ የሰለጠኑ አገራት የሚጠቀሙበት የደህንነት መጠበቂያ እንደተካተተበት የብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ አስታውቀዋል፡፡
ባንኮች ቀደም ሲል ሲወተውቱት ነበር እሁን መሆኑ ያስደሰታቸው ቢመስልም የመቀየሪያ ግዜ እርዝማኔ ግን ተገቢ እንደልሆነ ሃሳባቸውን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የባንኮች ማህበር የወቅቱ ፕሬዝደንት አቶ አቤ ሳኖ ውሳኔው ለባንኮች ትርጉሙ ብዙ መሆኑን አውስተው ሆኖም የመቀየሪያው ግዜ ከ 1 ወር መብለጥ የለበትም ሲሉ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
በ 1990 ዓ/ም በነበረው የኖት ወቅት የባንኮች ተደራሽነት ዝቅተኛ በመሆኑ ሰፊ ግዜ አስፈልጎ ነበር አሁን ግን ይህ የሚያስፈልግ አይመስለኝም ብለዋል፡፡
አቶ አቤ ሌላ ያቀረቡት ሃሳብ ከፍተኛ ገንዘብ የያዙ ግለሰቦች የሚቀይሩበት ግዜ ከ 1 ወር ወደ 15 ቀን ዝቅ ቢል የሚል ሃሳብ አቅርበው፤ በተጨማሪም የገንዘብ መጠኑ ለ 100ሺ ወደ 50 ሺ ዝቅ ቢል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ብር ለመቀየር የሚመጣ ከ 10 ሺ ብር በላይ የያዘ ሰው ሂሳብ ከፍቶ እዛው እንዲያስቀምጥ ይደረጋል የሚለውን የመንግስት እቅድ ወደ 5 ሺ ቢወርድ የሚል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
ጠ/ሚ አብይ ሃሳቡን ወስደው ባንኮች ላይ ጫና እንዳይፈጥር የተያዘ የግዜ እቅድ መሆኑን በማስታወስ ባንኮች ከብሄራዊ ባንክ ጋር በሚኖራቸው ንግግር ለውጦች ሊደረጉ እንደሚችል ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
ሆኖም እስከ 95 በመቶ የሚሆነው የገንዘብ ለውጥ በአንድ ወር ግዜ መጠናቀቅ እንዳለበት መታቀዱን አስታውሰዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
የብር መቀየር ስራው 10 ወራት የወሰደ ሲሆን ከሶስት ወራት በፊት ቅያሬውን ይፋ ለማድረግ ታስቦ ኮሮና ተህዋስ በፈጠረው ተፅእኖ ተግባራዊ የማድረጊያው ግዜ መዘግየቱን የብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ ለካፒታል ተናግረዋል፡፡
ኖቶቹ የታተሙባቸውን አገራት ግን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡ ለገንዘብ ህትመቱ ብቻ 3.7 ቢሊየን ብር የወጣበት ይህ ቀደም ሲል ፕሮጀክት X ተብሎ ይታወቅ እንደነበር የገለፁት ጠ/ሚ አብይ በመቀየር ሂደቱ ተጨማሪ ወጪ መኖሩን አስታውሰዋል፡፡
የብር ኖት የመቀየር ሂደት ላይ ባንኮች ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸው በአፅንኦት የተናገሩት ጠ/ሚኒስትሩ መንግስት በሚመለሱ አሮጌ ኖቶች ላይ ሃሰተኛ ገንዘብ መኖሩን እያንዳንዱን ኖት በሰው ሃይል እና በማሽን በመፈተሽ የሚያረጋግጥ በመሆኑ ከየትኛውም ባንክ የሚመጡ ህገወጥ ኖቶች ባንኮቹን ዋጋ የሚያስከፍሉ መሆኑን አስጠንቅቀዋል፡፡
ህገወጥ እንቅስቃሴዎች አንዳንድ ባንኮች አካባቢ እንዳለ መረጃ እየደረሰን ነው ያሉት ጠ/ሚ አብይ በዚህ የብር ኖት የመቀየር ሂደት ይሄ የሚቀጥል ከሆነ ዋነኛ የባንክ ሃላፊዎችንም ሆነ እራሱ ባንኩን ህልውና የሚያሳጣ እርምጃ የሚወሰድ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡
የብር መቀየር ሂደቱ በአብዛኛው ከኢኮኖሚ ምክንያቶች ጋር የሚያየዝ መሆኑን የተናገሩት ይናገር ሕገወጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በዋንኛ ምክንያትነት አንስተዋል፡፡
አብይ የፀጥታ መዋቅሩ ከዛሬ ጀምሮ ከአገር ውስጥ የሚወጡ እና የሚገቡ የገንዘብ ኖቶች ላይ ከፍተኛ ስራ እንዲሰራ አዘዋል፡፡(Capital)