Connect with us

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈጻሚ ዳውድ ኢብሳን ከፓርቲው ማገዱን አስታወቀ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈጻሚ የድርጅቱን ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳን ከፓርቲው ማገዱን አስታወቀ
Photo: Social Media

ዜና

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈጻሚ ዳውድ ኢብሳን ከፓርቲው ማገዱን አስታወቀ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈጻሚ የድርጅቱን ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳን ከፓርቲው ማገዱን አስታወቀ።
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ዛሬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ አቶ ዳውድ በፓርቲው አንድነትና ሰላማዊ ትግል ላይ እየፈጠሩት የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም ያሉባቸውን ችግሮች ከማስተካከል ይልቅ ፓርቲውን የመከፋፈልና አንጃ የመፍጠር አካሄዶችን ሲከተሉ ቆይተዋል። በመሆኑም ለፓርቲው ህልውናና ጥንካሬ ሲባል የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቶ ዳውድ ኢብሳን ከፓርቲው አግዷቸዋል።

በቀጣይ በፓርቲው ህገ ደንብና አሰራር መሰረት የሚከናወኑ ተግባራት መኖራቸውን ያስታወቁት አቶ ቀጃላ፤ ሁሉንም ሂደቶች በተመለከተ ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ሰነድና መረጃ ማስገባቱን አስታውቀዋል።

አቶ ዳውድ ላለፉት 20 አመታት በፓርቲው ላይ ተደጋጋሚ አደጋ መደቀናቸውን የተናገሩት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው፤ ቀደም ባሉት አመታት ሶስት ጊዜ ለፓርቲው መከፋፈል ዋናው ምክንያት እርሳቸው እንደነበሩና አሁንም ለአራተኛ ጊዜ ፓርቲውን ለመከፋፈል አንጃ ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ ይተዋል። ይህንን ለማስተካከል ጥረት ሲደረግም በተጨባጭ የፓርቲውን ንብረትና ገንዘብ ወደግላቸው የማዘዋወር እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል። ስለሆነም ፓርቲውን ለመታደግ ሲባል እርምጃው ተወስዶባቸዋል።

አቶ ዳውድ በፓርቲው ውስጥ ችግር መፍጠር የጀመሩት ከሀምሌ ወር ጀምሮ እንደነበር የተናገሩት አቶ ቀጀላ፤ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም በእርሳቸው በኩል ችግሩን ለመፍታት ባለመተባበራቸው ፓርቲው ህጋዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ቀጀላ ገለጻ፤ ፓርቲ ከአቶ ዳውድ ጋር ያለው ትልቅ ልዩነት በትግል አካሄድ ላይ ነው። ኦነግ ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላ ሰራዊቱ በዓለም አቀፍ አሰራር መሰረት ወደ መንግስት የጸጥታ አካላት እንዲቀላቀል ስምምነት ቢደረግም፤ አቶ ዳውድ ግን በዚህ ላይ ግልጽ አቋም አልነበራቸውም፤ በአንድ በኩል ሰላማዊ ትግሉን ይፈልጋሉ፤ የትጥቅ ትግሉንም በኪስ አድርጎ በድብቅ መሄድ ይፈልጋሉ።

በተጨባጭም በምዕራብና በደቡብ ጫካ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይሄ አካሄድ አግባብ አይደለም በሚል ስራ አስፈጻሚው ሲነጋገርበት ቆይቷል። ምክንያቱም የትጥቅና ሰላማዊ ትግል ድንበር ሊበጅለት ይገባልና ብለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጠቅላላ ጉባዔ ተደርጎ አዲስ መሪ ኣስኪመረጥ ድረስ የድርጅቱ ተወካይና መሪ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አራርሶ ቢቂላ እንደሆኑ አቶ ቀጀላ ጠቅሰው፤ በአቶ ዳውድ በኩል እስከዛሬ የነበሩ የዲስፕሊን ጥሰቶችን በተመለከተ ፓርቲው ዝርዝር መግለጫ ማውጣቱን አስታውቀዋል።

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top