Connect with us

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤቶች ግንባታ ተበድሮ ያልመለሰው ዕዳ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤቶች ግንባታ ተበድሮ ያልመለሰው ዕዳ 50 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታወቀ
A new social housing project on the edge of Addis Ababa. Photograph: Charlie Rosse

ኢኮኖሚ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤቶች ግንባታ ተበድሮ ያልመለሰው ዕዳ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤቶች ግንባታ ተበድሮ ያልመለሰው ዕዳ 50 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታወቀ

~በመንግሥት ውሳኔ 94 ሺሕ ቤቶች ላልተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች ተላልፈዋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላለፉት 15 ዓመታት ለገነባቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ከባንክ ተበድሮ ያልመለሰው ዕዳ 50 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታወቀ።

ሪፖርተር ከከተማው አስተዳደር ምንጮቹ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ከተጀመረበት 1997 ዓ.ም. አንስቶ እስከ ዘንድሮ ድረስ የተገነቡ ቤቶች የፋይናንስ ምንጭ የባንክ ብድር ነው።

በዚህ መሠረት አስተዳደሩ የተለያዩ የብድር ሥልቶችን ተጠቅሞ ለኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባው ከወሰደው ብድር ውስጥ 50 ቢሊዮን ብር የተወዘፈ ዕዳ እንዳለበት ለማወቅ ተችሏል። አስተዳደሩ ከተጠቀማቸው የብድር ሥልቶች መካከል የረዥም ጊዜ ቀጥታ ብድርና የመንግሥት የዕዳ ሰነድን በዋስትና በማስያዝ የተገኙ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

አስተዳደሩ ካለበት ብድር ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘ መሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል። አስተዳደሩ ያለበት የዕዳ መጠን ከፍተኛ በመሆኑም፣ ለአዲስ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ የሚሆን ብድር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማግኘት አልቻለም።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ የጀመረው በ1997 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከዚህ ወቅት አንስቶ በነበሩት 15 ዓመታት ተገንብተው ለተጠቃሚዎች የተላለፉት አጠቃላይ ቤቶች ብዛት 276 ሺሕ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ የሚገኙ ቤቶች ሲጨመሩ ደግሞ የቤቶቹ ብዛት 300 ሺሕ ይደርሳል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት ወሮ አዳነች አቤቤ ባለፈው ሳምንት ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ ቤቶቹን ለማግኘት የተመዘገቡ ነዋሪዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን እንደሆነ ገልጸዋል።

ተመዝጋቢዎቹን ለማጥራት በ2005 ዓ.ም. በተደረገ ዳግም ምዝገባ ቤት ያገኙት ተመዝጋቢዎች ቁጥር ተቀንሶ፣ አሁን የአዲስ ከበባ ነዋሪ መሆኑ ተረጋግጦ በቤት ፈላጊነት መዝገብ ውስጥ የሚገኝ ቤት ፈላጊ ብዛት 650 ሺሕ መሆኑን አስረድተዋል።

ባለፉት 15 ዓመታት ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ከተላለፉት 276 ሺሕ ቤቶች ውስጥ፣ 176 ሺሕ የሚሆኑት ለተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች የተላለፉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የተቀሩት ቤቶች በመንግሥት ውሳኔ ለተለያዩ አካላት እንደተላለፉ ምክትል ከንቲባዋ የተናገሩ ሲሆን፣ ይህም ማለት 94 ሺሕ ቤቶች ያለ ዕጣ በመንግሥት ውሳኔ እንደተላለፉ ያስገነዝባል።

በመንግሥት ውሳኔ ቤቶቹን እንዲያገኙ የተደረጉት በኃላፊነት ላይ ያሉ የከተማ አስተዳደሩና ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎችና የልማት ተነሺዎችና መሬታቸውን የለቀቁ አርሶ አደሮች መሆናቸውን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።

የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለማግኘች የተመዘገቡ ነዋሪዎች ቤቱን ለማግኘት ቀድመው የመቆጠብ ግዴታ ያለባቸው ቢሆንም፣ የቤቶቹ ግንባታ የሚካሄደው በተቆጠበው ገንዘብ እንደሆነ ተደርጎ የሚነገረው የተሳሳተ እንደሆነና ግንባታው በባንክ ብድር ሲካሄድ እንደቆየም ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል። ነገር ግን ቤቶቹ ከተላለፉ በኋላ የባንክ ዕዳው ቤቶቹ ለተላለፈላቸው ተጠቃሚዎቹ እንደሚዘዋወር ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በ20/80 እና በ40/60 የቤቶች ፕሮግራም ቤት ለማግኘት ተመዝግበው እየተጠባበቁ የሚገኙ ነዋሪዎች ብዛት 650 ሺሕ መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ ውስጥ በትክልል የሚጠበቅባቸውን የባንክ ቁጠባ እየፈጸሙ የሚገኙት 200 ሺሕ ገደማ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

በ1997 ዓ.ም. ተመዝግበው እስካሁን ቤት ያልደረሳቸው ነዋሪዎች ቁጥር 45 ሺሕ እንደሆነ፣ ከዚህ ውስጥ የቁጠባ ግዴታቸውን የተወጡት 18 ሺሕ እንደሆኑም ገልጸዋል። ለእነዚህም በአሁኑ ወቅት በግንባታ ሒደት ላይ ከሚገኙትና በቅርቡ ዕጣ ከሚወጣባቸው 23 ሺሕ ቤቶች መካከል ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።

የተቀሩት 630 ሺሕ የሚሆኑ ቤት ፈላጊዎች ለማስተናገድ የተለያዩ የግንባታ አማራጮችን በመከተል፣ በተቻለ ፍጥነት ለመመለስ ጥረት እንደሚደረግም አስረድተዋል።

ከእነዚህ አማራጮች መካከልም ቅድሚያ የሚሰጠው በሁለቱም የቤቶች ግንባታ ከተመዘገቡት ውስጥ፣ አቅም ያላቸውን ከባንክ ጋር በማገናኘትና ከሊዝ ነፃ መሬት በማቅረብ፣ እንዲሁም ከተቋራጮች ጋር በማቀናጀት በማኅበር ተደራጅተው በራሳቸው እንዲገነቡ ማድረግ ይገኝበታል። (ዮሐንስ አንበርብር ~ ሪፖርተር)

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top