Connect with us

የማታው የጠቅላዬ ቃለምልልስ የቆሰቆሰብኝ ነገር

የማታው የጠቅላዬ ቃለምልልስ የቆሰቆሰብኝ ነገር
Photo: Social Media

ትንታኔ

የማታው የጠቅላዬ ቃለምልልስ የቆሰቆሰብኝ ነገር

የማታው የጠቅላዬ ቃለምልልስ የቆሰቆሰብኝ ነገር
(ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)

ጥሎብኝ እወዳቸዋለሁ። አንዳንድ ስራቸው ግን ከሁለት አመት የስልጣን ቆይታቸው በኋላም እየገባኝ አይደለም። ወይ እኔ ደደብ ሆኛለሁ፤ ወይንም እሳቸው አቶ ሽመልስ እንዳሉት ቀድሞውኑ ኮንፊዩዝ አድርገውኛል ማለት ነው።

የትላንቱን የአንድ የኢቲቪ ጋዜጠኛ ቃለምልልሳቸውን ስመለከት ውስጤ የተከፋው ወዲያውኑ ነበር። እንዲህ የተሰማኝ ጋዜጠኛ ስለሆንኩኝ ሊሆን ይችላል። ምናለበት ሀገሪቷ እንዲህ ግራ ቀኝ ውጥርጥር ባለችበት በዚህ ጊዜ እንኳን የግል ጋዜጠኞችን ጭምር ያሳተፈ ጋዜጣዊ መግለጫ ቢጠሩ? ምናለ አሉ የሚባሉ ጥያቄዎችን ሁሉ ተቀብለው መልስ መስጠት ቢችሉ?

በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን የመንግስት ጋዜጠኞች እንዲህ አይነት መግለጫ ላይ ሲላኩ የካድሬ አለቆቻቸውን ጥያቄ አንጠልጥለው እንደነበር አውቃለሁ። ጥያቄዎቹ ለተጠያቂዎቹ ቀድሞ ስለሚላክ ጋዜጠኛው ድንገቴ ጥያቄዎችን ማቅረብ አይፈቀድለትም። በአንድ ወቅት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣ ባልደረባ የነበረች እንእስት የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ከተሰጣት ጥያቄ ወጣ በማለት እንደስብሀት ገብረእግዚአብሄር አይነት የስነፅሁፍ ሰዎች መረሳት ጉዳይ ጥያቄ ማንሳቷ ከባድ ተግሳፅን አስከትሎባት ከመባረር የዳነችው በተአምር ነበር። ያ ክፉ ልማድ ዛሬም እንዳልቀረ ታዘብኩኝ።…ግን ለምን?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ “ጥሩ ስራ ሰርቻለሁ፣ ጥሩ የህዝብ ድጋፍ አለኝ” ካሉ ጋዜጠኞች ጋር ፊት ለፊት መገናኘትን ለምን ይፈራሉ? ወደስልጣን ከተሳቡ በኃላ በጋዜጣዊ መግለጫ ጋዜጠኞችን ፊት ለፊት ያገኙትበት ጊዜ ከሶስት ጊዜ የሚበልጥ አይመስለኝም። ከተሳሳትኩኝ እታረማለሁ። ግን እኛ ጋዜጠኞች ቢያድለን ኖሮ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ ፊት ለፊት ማግኘት የምንችልበት ምህዳር መፈጠር ነበረበት። ግን አልተቻለም ወይንም አልተፈለገም ወይንም አልታደልንም።
እኔ ዕድሉን ባገኝ የሚከተሉትን የተጠራቀሙ የህዝብ ጥያቄዎች አዘንብላቸው ነበር።

~ ባለፉት ሁለት አመታት በተለያዩ አካባቢዎች ለተከሰቱት ዘር እና ሀይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች፣ የንብረት ውድመቶችና መፈናቀሎች ኃላፊነቱን የሚወስደው የመንግስት አካል ማንነው?

~ መንግስት ንፁሀን ዜጎችን ከጥቃት መጠበቅ ባለመቻሉ ወይንም ሀላፊነቱን በአግባቡና በሰአቱ ባለመወጣቱ ህዝብን ቢያንስ በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አልነበረበትም ወይ?

~ በቅርቡ የሀጫሉን ግድያ ተከትሎ በተለይ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች መጠነ ሰፊና የተቀናጀ ጥቃት ከተፈፀመ በኃላ ቢያንስ ተፈናቃይ ወገኖችን በአካል ሄደው ማፅናናት ያልቻሉት ለምንድነው?

~ የተፈፀሙ ጥፉቶች ዳግም እንዳይደገሙና አጥፊዎች ተለይተው ተገቢውን ቅጣት እንዲቀበሉ ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ያልወሰኑት ለምን እንደሆነ?

~ ይኸ ሁሉ ቀውስ በሀገሪቱ ሲፈፀም ምን ተጨባጭ እርምጃ እንደወሰዱ?

~ በእሳቸው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተከሰተ የግድያ ሙከራ ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጋር የተያያዙ ክሶች ግልፅነት የጎደላቸውና ዋና “ማስተር ማይንድ” የተባሉ ሰዎች መያዝ ያልተቻለው ለምን እንደሆነ?

~የተጠለፉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ የተድበሰበሰውና በመንግስት በኩል በየጊዜው የተምታታ መግለጫ የሚሰጠው፣ አሁን ድረስ ጉዳዩ መቋጫ ያጣው ለምን እንደሆን?

~ አሁንም በትርክት ሰዎችንና ቡድኖችን የሚፈርጁ አመራሮች ለምን በስልጣን ላይ ሊቆዩ እንደቻሉ?

~ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰዎች ያለጥፋታቸው በእስር መንገላታታቸው ሳያንስ ፍርድ ቤት በነፃ ሲለቃቸው ፖሊስና የደህንነት ሀይሎች ከህግ ውጪ የሚያስሩበት ሁኔታ ለምን በዝምታ እንደሚመለከቱት?

~ በአዲስአበባ በመዋቅር የታገዘ የመሬት ወረራ እና የኮንደምኒየም እደላ ሲካሄድ እሳቸው የበላይ አመራር ሆነው እንዴት እርምጃ መውሰድ እንደተሳናቸው?

ከ15 ሚልየን በላይ የእለት እርዳታ ፈላጊ ወገን ባለበት ሀገር መናፈሻዎችን ለማሳመር እየወጣ ስለሚገኘው ገንዘብና የመንግስት የትኩረት ቅደምተከተል መዛባት ጉዳይ እሞግታቸው ነበር።
አዎ!… ነበር…ነበር። ያው ነገሩ እንደብሂሉ ነው።
“ዳቦ የለም እንጂ ዳቦማ በነበር
በወተት እየማግን እንገምጠው ነበር”

Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top