Connect with us

በይቅርታ ላይ ስናፌዝ ዋልን!

በይቅርታ ላይ ስናፌዝ ዋልን!
Photo: Social Media

ትንታኔ

በይቅርታ ላይ ስናፌዝ ዋልን!

በይቅርታ ላይ ስናፌዝ ዋልን!
(ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)
.
.
የሀገሬ ሰዎች ለይቅርታ (ለመጠየቅም፣ ለማድረግም) ንፉግ ናቸው፡፡

‹‹ሳላውቅ ያስቀየምኳቸሁ፣ . . .›› ብሎ ይቅርታ መጠየቅ፡፡ መጀመሪያ እስቲ አውቀን የበደልናቸውን ይቅርታ እንጠይቅ፡፡ አውቄ የበደልኩት የለም ለማለት ነው? በየአንዳንዳችን ልብ የበደል ቁልል አለ፤ ያንን ለመናድ መድፈር ነው ይቅርታ፡፡ የበደልከውን ሰው፣ ‹‹ይህን ስላደረግኩህ ይቅር በለኝ›› ብለህ መጋፈጥ፡፡ በደለኛነትን ሸሽጎ በይቅርታ መንጻት አይቻልም፡፡
.
ይቅርታ በጅምላ አይሆንም፡፡ መሪዎች የገደሉትን፣ ያሰሩትን፣ ያፈረሱበትን፣ የወረሱትን፣ …ወዘተ. በስም እየጠሩ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው፣ እውን ይቅርታ ከፈለጉ፡፡

ጎንደር ላይ ወጣት ሲረሽን የነበረ፣ ተነስቶ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ የሚጠይቅበት ምክንያት የለም፤ የገደለውን ያስገደለውን በስም እየጠራ፣ የሟች ቤተሰቦች ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት፡፡

ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ስትላቀቅ የተደረገው ይኸውም ነው፡፡ በሀገር ላይ የተሰራ በደል ካለ (ለምሳሌ ኢትዮጵያን የባህር በር እንደማሳጣት አይነት) ህዝብ ይቅርታ ይጠየቃል፡፡ አንድ ተማሪ የበደለ መምህር ክፍል ገብቶ ‹‹ያስቀየምኳችሁ ይቅርታ›› ሲል፣ ፐ! ይቅርታ ጠየቀ ይባልለታል፡፡ በፍጹም፤ ይቅርታ አልጠየቀም፡፡ ስሙን ጠርቶ፣ የበደለውን ገልጾ ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት፡፡
.
ይቅርታ መጠየቅ ነው ማግኘት ቁም ነገሩ? እንዴ ይቅርታችንን ተበዳይ መቀበል አለመቀበሉን ማወቅ የለብንም? ካለብን ከበደልነው ጋር መጋፈጥ የግድ ነው፡፡ የጎረቤቴ ልጅ በተገደለ፣ በታሰረ እናት አባቱ እንጂ እኔን ማን ይቅርታ አድራጊ አደረገኝ?
.
ደግሞ አንዳንዱ ይገርማል፤ እራሱን ከእየሱስ መስቀል ላይ ሰቅሎ መሀሪ ይቅር ባይ መሆን ያምረዋል፤ ይቅርታ እኮ ዝቅ ማለት ነው፡፡ ‹‹ሳላውቅ በድያችኋለሁ ይቅርታ አድርጉልኝ፤ እናንተ ግን አውቃችሁ በድላችሁኛል፣ ይሁንና ይቅር ብያችኋለሁ››፡፡ እኔ ንጹህ፣ እናንተ ሀጥያተኞች ማለት እኮ ነው፡፡ እስቲ የሚከተለውን ይቅርታ እንመልከት፡፡

‹‹. . . እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ባለማወቅ ለበደልኩት ለማንኛውም በደል ይቅርታን በትህትና እጠይቃለሁ።
እኔንም ለበደሉኝ፤ ያለበደሌ ለከሰሱኝ፣ ያለ ተግባሬ መጥፎን ስም ሰጥተው ላሳጡኝ፤ ሕዝብን ለማገልገል በምተጋበት ወቅት አላስፈላጊ ጦርነትን በመክፈት ሲያደክሙኝና አላሠራ ሲሉኝ ለነበሩት ሁሉ ከልብ የሆነ ይቅርታን አድርጊያለሁ።››

አሁን እዚህ ውስጥ ምን የይቅርታ መንፈስ አለ? ይቅርታ ጠያቂው፣ አውቆ የበደለው አንድም ነገር የለም፡፡ እሱ ላይ የተደረገውን በደል ግን ሆን ተብሎ፣ ታቅዶ እንደተደረገ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ ምናለ የእነሱንም፣ ‹‹ሳታውቁ ለበደላችሁኝ›› ብሎ ቢያልፈው? ወይ የእሱንም ቢዘረዝረው?
.
እና እባካችን ያልደረስንበትን እንተወው፤ ቢያንስ ጽንሰሀሳቡ ለልጆቻችን ይቀመጥ፤ እነሱ ይደርሱበት ይሆናል፤ የልጅ ልጆቻቸውም ቢሆኑ::

የአ/አ ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ የይቅርታ ቃል!

ለመላው የከተማችን ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች በከተማዋ አስተዳደር አማካኝነት ለተፈጠሩ ስህተቶችና የአስተዳደር ግድፈቶች የምህረት ወር ተብላ በምትታወቀው በወርሃ ጳጉሜ የመጀመሪያዋ ቀን ላይ ከፊታችሁ ቆሜ ይቅርታ እንድታደርጉልኝ በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ። #ይቅርታ_እላለሁ_ይቅር_እላለሁ!


“ይቅርታ ይሁንልን!” ታከለ ኡማ (የቀድሞ የአ/አ ም/ከንቲባ)

“ውድ የከተማችን ነዋሪ ወገኖቼ፦

የኢትዮጵያውያን ሁሉ መዲና የሆነችውን ታላቅ ከተማ የማስተዳደርን ዕድል ላለፉት ሁለት ዓመታት በማግኘት ለማገልገል በመቻሌ ትልቅ ክብር ይሰማኛል።

ወደዚህ ኃላፊነት አከራካሪ በሆነ መንገድ ብመጣም፤ በወሬ ሳይሆን በሥራ፣ በብሔር ሳይሆን በኢትዮጲያዊነት የሚያምነው መልካምና ሰው ወዳድ ሕዝብ ጋር በፍቅር አብሮኝ ስለሠራና ስላሠራኝ ምስጋናዬ ሁልጊዜም ከፍ ያለ ነው።

አሁን በሥራ ላይ ያለው በእህቴ በወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው አስተዳደር የዛሬውን ቀን (ጷግሜ 1, 2012) “የይቅርታ ቀን ” ብሎ በሰየመው መሠረት፣ እኔም እንደከተማው ነዋሪና የቀድሞ አገልጋያችሁ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ ይቅርታ ይሁንልን እላለሁ።

ከተማዋን በማስተዳደር ኃላፊነቴ ወቅት እንዲሁም እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ባለማወቅ ለበደልኩት ለማንኛውም በደል ይቅርታን በትህትና እጠይቃለሁ።

እኔንም ለበደሉኝ፤ ያለበደሌ ለከሰሱኝ፣ ያለ ተግባሬ መጥፎን ስም ሰጥተው ላሳጡኝ፤ ሕዝብን ለማገልገል በምተጋበት ወቅት አላስፈላጊ ጦርነትን በመክፈት ሲያደክሙኝና አላሠራ ሲሉኝ ለነበሩት ሁሉ ከልብ የሆነ ይቅርታን አድርጊያለሁ።

የአዲሱ አመት የምህረት፣ የፍቅርና የአንድነት አመት ይሁንልን። ከስህተታችን የምንታረምበት፣ ካለፈው ተምረን ወደፊታችንን የምናሳምርበት ይሁንልን።”

 

Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top