ያለንሰሃ ይቅርታ
(ሙሼ ሰሙ)
ንስሃ የሌለው ይቅርታ በተሿሚው ባለስልጣን ቁጥርም ቢጎርፍ፣ በዘመን መለወጫ ወይም በዘመን መሸጋገርያ፤ አሊያም በባዕለ ሲመትም ሆነ በበዓለ ንግስና ዓመት እየቆጠረ ቢደጋገም፤ ከአንጀት ጠብ አይልም። ይቅርታ ከልብ ቢሆንማ ኖሮ የአምናውና የካቻምናው፣ ይቅርታ ባጠገበን ነበር።
የሞተውን እምባ ያላበሰ፣ ንብረቱን አጥቶ ጥገኛ የሆነውን፣ የተጎዳውን፣ የታረዘውን፣ የተዋረደውን፣ ያዘነ ያለቀሰውን ያልጎበኘ፣ ትናንትን ለትናንት ያልተወና ነገን ደግሞ በአዲስ መንፈሱ ያልሰነቀ፣ በስጋው ያልደከመና ከቂም ያልጸዳ ይቅርታ፣ ቀን የሚወልደው የመንገደኛ ይቅርታ ነው።
የትናንት ይቅርታ ለእውነት፣ በሀቅና ለሀቅ ከልብ ቢሆኖ ኖሮ የአምናው ይቅርታ በስጋም ሆነ በመንፈስ ሁላችንንም ከአንጀታችን ባሽረን ነበር።
‘ትንቢት ይቀድም ለነገር” እና “ነገም ሌላ ቀን ነው” እንዲል ተረቱ ትናንት በቃሉ ያልጸና፣ ነገ በቃሉ ይገኝና ይታመን ዘንድ እምነቱ ተሰብሯልና እምነቱን ያድስ ዘንድ ቃሉን ይመርምር።
አሁንም እደግመዋለሁ፤ በሃይማኖትም ቢሆን ይቅርታ ያለ ንስሃ ትርጉም የለውም። እድልም ሁሌ የይቅርታን በር አታንኳኳም! አሁንም፣ ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገ ወዲያም ከይቅርታ በፊት ንስሃና ተግባር ይቅድሙ?!
—
የአ/አ ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ የይቅርታ ቃል!
ለመላው የከተማችን ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች በከተማዋ አስተዳደር አማካኝነት ለተፈጠሩ ስህተቶችና የአስተዳደር ግድፈቶች የምህረት ወር ተብላ በምትታወቀው በወርሃ ጳጉሜ የመጀመሪያዋ ቀን ላይ ከፊታችሁ ቆሜ ይቅርታ እንድታደርጉልኝ በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ። #ይቅርታ_እላለሁ_ይቅር_እላለሁ!
—
“ይቅርታ ይሁንልን!” ታከለ ኡማ (የቀድሞ የአ/አ ም/ከንቲባ)
“ውድ የከተማችን ነዋሪ ወገኖቼ፦
የኢትዮጵያውያን ሁሉ መዲና የሆነችውን ታላቅ ከተማ የማስተዳደርን ዕድል ላለፉት ሁለት ዓመታት በማግኘት ለማገልገል በመቻሌ ትልቅ ክብር ይሰማኛል።
ወደዚህ ኃላፊነት አከራካሪ በሆነ መንገድ ብመጣም፤ በወሬ ሳይሆን በሥራ፣ በብሔር ሳይሆን በኢትዮጲያዊነት የሚያምነው መልካምና ሰው ወዳድ ሕዝብ ጋር በፍቅር አብሮኝ ስለሠራና ስላሠራኝ ምስጋናዬ ሁልጊዜም ከፍ ያለ ነው።
አሁን በሥራ ላይ ያለው በእህቴ በወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው አስተዳደር የዛሬውን ቀን (ጷግሜ 1, 2012) “የይቅርታ ቀን ” ብሎ በሰየመው መሠረት፣ እኔም እንደከተማው ነዋሪና የቀድሞ አገልጋያችሁ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ ይቅርታ ይሁንልን እላለሁ።
ከተማዋን በማስተዳደር ኃላፊነቴ ወቅት እንዲሁም እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ባለማወቅ ለበደልኩት ለማንኛውም በደል ይቅርታን በትህትና እጠይቃለሁ።
እኔንም ለበደሉኝ፤ ያለበደሌ ለከሰሱኝ፣ ያለ ተግባሬ መጥፎን ስም ሰጥተው ላሳጡኝ፤ ሕዝብን ለማገልገል በምተጋበት ወቅት አላስፈላጊ ጦርነትን በመክፈት ሲያደክሙኝና አላሠራ ሲሉኝ ለነበሩት ሁሉ ከልብ የሆነ ይቅርታን አድርጊያለሁ።
የአዲሱ አመት የምህረት፣ የፍቅርና የአንድነት አመት ይሁንልን። ከስህተታችን የምንታረምበት፣ ካለፈው ተምረን ወደፊታችንን የምናሳምርበት ይሁንልን።”