Connect with us

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል የጉዞ ክፍያ አገልግሎት ጀመረ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል የጉዞ ክፍያ አገልግሎት ጀመረ
Photo: Social Media

ኢኮኖሚ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል የጉዞ ክፍያ አገልግሎት ጀመረ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶልጌት ትራቭል ከተሰኘ ኃላፊነቱ የተወሰነ የኦን ላይን የጉዞ ወኪል ጋር በመተባበር ዲጂታል የጉዞ ክፍያ አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ ።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ የሐንስ ጊሎ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የዲጂታል አገልግሎት የክፍያ አማራጭ ደንበኞች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል።የዲጂታል ክፍያ መተግበሪያው ከሞባይል ኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ጋር ይተሳሰራል።

እንደ አቶ ዮሐንስ ገለጻ፤ በሶልጌት ትራቭል የተዘጋጀው የጉዞ መተግበሪያ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር እንዲሰራ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።መተግበሪያው በአምስት ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን አራቱ የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ናቸው።

አማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና እንግሊዘኛ መተግበሪያው የተዘጋጀባቸው ቋንቋዎች መሆናቸውን ያስታወቁት ኃላፊው፤ ደንበኞች በአቅራቢያቸው ከሚገኝ የትኛውም የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በመሄድ አስፈላጊውን መረጃ በመሙላት አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል ፡፡

በቀጣይ ተቀዳሚ ደንበኞች የበረራ ትኬት በብድር መግዛት የሚችሉበት የአሰራር አማራጭ እንደሚዘረጋ ያመለከቱት አቶ ዮሐንስ፤ አዲሱ የዲጂታል የክፍያ አገልግሎት በረራ የመሰረዝና በድጋሚ ቦታ የማስያዝ አሰራር ያለው መሆኑን አመልክተዋል።

አገልግሎቱ ትኬት ይጠፋብኛል ከሚል ስጋት የሚያድን መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው ፤ ተጓዦች በአንድ አየር መንገድ የቆረጡትን ትኬት በመሰረዝ በወረቀት የታተመ ማረጋገጫ ሳያስፈልግ ወደ ሌላ አየር መንገድ መቀየር እንደሚችሉም አስታውቀዋል።

ከደህንነት አኳያ የትኬት መግዣ የወረቀት ገንዘብ መያዝን እንደሚያስቀር ጠቁመው፤ አገልግሎቱ ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ያማከለ በመሆኑ የቱሪዝም ዘርፉን እንደሚያሳድግና የባንኮችን ተቀማጭ ገንዘብ እንደሚጨምር ገልጸዋል።

የጉዞ ጎ/ የሞባይል መተግበሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በሱፈቃድ ጌታቸው እንደገለጹት፤ ዲጂታል የጉዞ ሥርዓቱ የተዘጋጀው በኢትዮጵያውያን ነው፤ ጥገና የሚደረግለትም በኢትዮጵያውያን ነው።የመተግበሪያው የዘመን አቆጣጠሩ እና የሰዓት አቆጣጠር በኢትዮጵያ የሚሰራ መሆኑ አስታውቀዋል።

መተግበሪያው በዘርፉ ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ከማሳየት ባሻገር አገሪቱ የራሷ የዘመንና የሰዓት አቆጣጠር እንዳላት ያሳያል ብለዋል ።መተግበሪያው ለተመረጡት አሥር አገራት ከየትኛውም አገር ወደየትኛውም አገር ለመብረር እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡ ከመተግበሪያው በተጨማሪም 7473 የጥሪ ማዕከል ያለው ሲሆን፤ ለመንገደኛው ከጉዞው ሁለት ሰዓት አስቀድሞ በመደወል መረጃ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል ፡፡

‹‹መተግበሪያው ከእንግሊዘኛ ውጪ ባሉ ሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችም አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል›› ያሉት አቶ በሱፈቃድ፤ የሆቴሎች አገልግሎቶችንም በዚሁ መተግበሪያ ማግኘትና ማዘዝ እንደሚቻል አመልክተዋል።

መተግበሪያው አገልግሎት የሚሰጥባቸው አገራት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኤመሬትስ፣ ሉፍታንዛ፣ ኳታር፣ ተርኪሽ፣ ኬንያ፣ ዱባይ፣ ገልፍ፣ ግብጽ እና ሳውዲ አየር መንገዶች መሆናቸውም በወቅቱ ተገልጿል ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ25 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ አንድ ሺ 600 ቅርንጫፎችእንዳሉትም ከባንኩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል ።
(አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2012)

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top