የኛ ነገር የሚፈታው – በናይጄሪያው- ቢያፋራ ወይስ በስፔኗ ካታሎኒያ መንገድʔ
(እስክንድር ከበደ)
የኢሳቱ ጋዜጠኛ ግዛው ከተወያዮቹ በእድሜ ጠና ያሉ ይመስላሉ፡፡ ደጋግመው እምቢ ያለ ክልል የበጀት ጫና እንዲደረግበት ይመክራሉ፡፡ የበጀት ጫና የባዕድ አገር ቅጣት እንጂ የሀገርህን” እንቢተኛ ” እቀጣለሁ ብለህ የምታደርገው ማዕቀብ አይደለም፡፡
ሰውየው ከድህረ ነጻነት ወቅት የናይጄሪያውን የሶስት አመቱን የእርስበእርስ ጦርነት ቢያነቡ እንዲህ አይመክሩም፡፡ በምግብ እጥረት ለረሀብ የተዳረጉት ፖለቲከኞቹ ወይም አዋጊዎቹ ሳይሆኑ የናይጄሪያ ህጻናትና ታዳጊዎች መሆናቸውን ይረዱ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ 1967 በደቡብ ምሥራቃዊ ናይጀሪያ የሚገኘው የቢያፍራ ግዛት ከሀገሪቱ መገንጠሉን ይፋ አደረገ፡፡ ከጥቂት ጊዚያት በኋላ በሀገሪቱ የርስበርስ ጦርነት ተጀመረ፡፡ ሀምሌ ስድስት፣ 1967 ዓም የተጀመረው የርስበርስ ጦርነት እስከ እ.ኤ.አ ጥር፣ 1970 ዓም የቀጠለ ሲሆን፣ የ2 ነጥብ 5 ሚልዮን ሰው ሕይወት አጥፍቷል።በናይጄሪያ የቢያፍራ ግዛት መገንጠል ውዝግብ በሚሊዮን ሰዎች እልቂት የተስተናገደው የሁለት አመት ተኩል የእርስበእርሰ ጦርነት አሰቃቂ ጠባሳውን ለመረመረ ለሀገራችንም ለወቅቱ ቀውስ እንደፈውስ ይማርበታል፡፡
ከአፍሪካ ወጣ ስንል ደግሞ በስፔን በምትገኘው የራስገዟ የካታሎኒያ የመገንጠል አቀንቃኞች እንቅስቃሴ በስፔን ህገ መንግስት አንቀጽ 155 መሰረት የተፈታ ነበር፡፡የስፔን ካታሎኒያ የራስገዝ ግዛት እ.ኤ.አ በ2017 ከስፔን ማአከላዊ መንግስት የመገንጠል ህዝበ ውሳኔ አካሂዳ ነበር፡፡ ካታሎኒያ በሰሜን ምስራቅ ስፔን የምትገኝ ከፊል ራስገዝ ስትሆን፤የራሷ 1ሺህ አመታት ልዩ ታሪክ እንዳላት ይነገራል፡፡ በሀብት የበለጸገችው ክልል 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ነዋሪዎች ሚኖሩባት የራሷ ቋንቋ፣ፓርላማ፣ባንዲራና የህዝብ መዝሙር አላት፡፡ ካታሎኒያ የራሷ ፖሊሲ ኃይል አላት፡፡
የካታሎኒያ በሔርተኞች ክልላቸው ለስፔን ማዕከላዊ መንግስት ብዙ ገንዘብ በግብር መልክ ተሰብስቦ ለሌሎች የሀገሪቱ ደሃ ክልሎች እንደሚልክ በመግለጽ ለአመታት ቅሬታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ 2010 ይባስ ብሎ የስፔን ማአከላዊ መንግስት የካታሎኒያን ከፊል ራስገዥ ፍጥረት በመቀየር ማንነታችንን አልጠበቀልንም ሲሉ የካታሎኒያ በሔርተኞች ማድሪድን በመክሰስ ከስፔን ለመነጠል እንቅስቃሴ ጀመሩ ፡፡
ካታሎኒያ እ.ኤ.አ በኦክቶበር 1 ቀን 2017 ህዝበ ውሳኔ አድርጋ 90 በመቶ ከስፔን መነጠልን ህዝቡ ወስነዋል ብላ ብታውጅም ፤የስፔን መንግስት መራጮች ቁጥር 43 ነጥብ 3 በመቶ እንደሆነ በመጥቀስ የስፔን ህገ መንግስታዊ ፍርድቤት ህዝበውሳኔውን ህገወጥ እንደ ሆነ በመግለጽ ውድቅ አደረገው፡፡ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በጥቅምት 2019 ጠቅላይ ፍርድ ቤት የካታሎኒያ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶችን የፍርድ ብያኔ ሰጠ፡፡ ጠቅላይ ፍርድቤቱ የግዛቲቱን ከፊል ራስገዝነት በማገድ ቁንጮዎቹን አቀንቃኞቹን 9 ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ምርጫ ባካሄዱ 2 አመታት በኋላ ከ9 እስከ 13 ዓመት እስራት ፈረደባቸው፡፡ ሌሎች 3ቱን ደግሞ ቀላል ቅጣት ጣለባቸው፡፡
***
የፌዴራል መንግስት በክልል ጣልቃ የሚገባበት ሥርዓት ለመደንገግ የወጣ አዋጅ 359/1995 አለ፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች መካከል የሚጠቀሱት
1. እንደ ችግሩ ክብደት አደጋውን ለማስወገድ የሚያስችል የፌዴራል ፖሊስን ወይም የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ወይም ሁለቱንም በክልሉ እንዲያሰማራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ የመስጠት፣
2. የክልሉን ምክር ቤት እና የክልሉን ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚ አካል በማገድ ለፌዴራል መንግስቱ ተጠሪ የሆነ ጊዚያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም መወሰን ይችላል። ጊዚያዊ አስተዳደሩ በክልሉ ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚ አካል የተሰጡት ስልጣንና ተግባራት የሚኖሩት ሆኖ በክልሉ የሚቆየው ከሁለት አመት ላልበለጠ ጊዜ ነው። ሆኖም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመቆያ ጊዜውን ከ 6 ወር ለማራዘም ይችላል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ምን ምን እርምጃዎች መውሰድ ይችላል?
ጊዚያዊ አስተዳደሩ፦
1. ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ በመጣል የተሳተፉ የክልሉ መንግስት ባለ ስልጣኖች ፣ ተሿሚዎች ተመራጮች፣ የፖሊስና የፀጥታ ኃይል አባላት፣ እና ሌሎች ሰዎችን ለፍርድ እንዲቀርቡ የማድረግ፣
2. በክልሉ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ተጠብቆ የክልሉ መንግስት መደበኛ ስራውን የሚጀምርበትን ሁኔታ በአፋጣኝ የማመቻቸት ስራ ይሰራል።
ያም ሆነ ይህ ጋዜጠኞችና በሚዲያ የሚጋበዙ የአደባባይ ምሁራን እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ላይ በደንብ ዙሪያ ገባውን ቃኝተው ወደ መድረክ ቢወጡ መልካም ይሆናል፡፡ “ምርጫ አደርጋለሁ” የሚለው ክልልም ይሁን የፌደራል መንግስቱ ከእናንተ ክብርና ሥልጣን በላይ ሀገርና ህዝብ ይበልጣልና በዚህ ዘመን “ዘራፌዋ” ሽለላ እንደማያዋጣ አውቃችሁ ኳስ በመሬት አድርጉልን፡፡
እንደምትሉት “ህገ መንግስት ይከበር!”…..”ህገመንግስት ተጥሷል! ” በሚል ግትር አቋማችሁ ከቀጠላችሁ ከጳጉሜ ጀምሮ አዲሱን አመት በመታመስ መጀመራችን አይቀርልንም፡፡