ማስታወሻ፤ ለክቡር ጠ/ሚኒስትሬ
ክቡርነትዎ እርግጥ ነው፤ ያነሱት የወንድማማች እሴት አስፈላጊነት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ግን ወንድማማችነት ማለት የእኔ ለሚሉት ወገን ሌት ተቀን መስራት ሌላውን መንፈግ ወይንም ማግለል አይደለም። ወንድማማችነት እስከሚገባኝ ድረስ ተካፍሎ መብላት ነው። የእኩል ተጠቃሚነትን መርህን መተግበር ነው።
ክቡርነትዎ፤ ስለአዲስአበባ የመሬትና የኮንደምኒየም ዝርፊያ እንደአገር ብቻ ሳይሆን እንደብልፅግና ፓርቲ መሪነትዎ በግልፅ ወጥተው አንድ ነገር ይላሉ ብዬ ትላንትና እና ዛሬ እየጠበኩኝ ነበር። መልስዎ ግን ዝምታ ሆነ። ጉዳዩ እኮ በእኔ ግምት ከከተማው ነዋሪ ከ80 በመቶ በላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚመለከተው ነው። በአጭሩ የተፈፀመው ከፍተኛ የወንጀል ድርጊት ጥቂት የማይባል የከተማውን ህዝብ አስቆጥቷል። ህዝቡ ቁጣውን ውጦ በከፍተኛ ትግእስትና ጨዋነት መልስዎን እየጠበቀ ነው።
በግሌ ለአንገብጋቢ የህዝብ አጀንዳ ተገቢውን ምላሽ መንፈግ ትክክል አይመስለኝም። የተፈፀመው ወንጀል ጉዳዩ የኦሮሞን ህዝብ የመካስና ያለመካስ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ ሽፋን ነው። በስሙ ጥቂቶችን በአንድ ጀንበር ሚልየነር ያደረገ ቁማር ሲሰራ እንደነበር የሚወጡት መረጃዎች ጠቋሚ ናቸው። ደሀው ለዓመታት ቆጥቦ የሰራው ቤት በካሳ ስም ተዘርፏል። የኦሮሞ ገበሬ አይካስ አልወጣኝም።
ባለፉት የህወሓት/ኦህዴድ የስልጣን ዘመን የተሰራው ግዙፍ የማፈናቀል ችግር ግን በዚህ መንገድ ይፈታል ተብሎ ከታመነ መሞከሩ አይከፋም። ግን አንዱን ተጎጂ ለመካስ የአዲስአበባ ደሀ ህዝብ በወር ቆጥቦ የሰራውን ቤት መንጠቅና ከብዙሃኑ ጋር ፊት ለፊት መላተም በምንም አመክንዮ ፍትሀዊነትን አያሳይም። ደግሞስ ዛሬም ድረስ የምትረግሙት ህወሓት በ27 አመት ያልሞከረውን ግፍ በሁለት አመት በወረራ መልክ ለማሳካት መጋጋጥ ምን የሚሉት ስልጣኔ ነው?
ክቡርነትዎ ይህን የህዝብ አጀንዳ በምንም መልኩ በዝምታ ሊዘሉት አይችሉምና አሁንም በጉዳዩ እንዲያስቡበትና እርምጃዎን ይፋ እንዲያደርጉ እንደአንድ ኢትዮጵያዊ የምጠይቅዎ በፍፁም ቅንነት ነው።
በግሌ በእርስዎ ያለኝ እምነት አሁንም ቢሆን ከውስጤ ተሟጦ አልጠፋም። ቢረፍድም በቀጣይ ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አለኝ።
አዎ ስህተት ለምን ተሰራ አይባልም። ስህተቱን ባላየ በማለፍ ግን ሌላ ስህተት መስራት ከህዝብ ልብ እንደሚያርቅ ለእርስዎ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል። ደህና ሰንብቱልኝ!!
አክባሪዎ – ጫሊ በላይነህ